አንዲትን ደሴት ያስደሰተ ታሪካዊ ጉብኝት
በካረቢያን ባሕር ላይ የምትገኘው ውብ ደሴት ኩባ በቅርቡ እጅግ ከፍተኛ በሆነ መንገድ በመንፈሳዊ የሚያነቃቃ ወቅት አሳልፋለች። በዚህች በዌስት ኢንዲያን አገር የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በ1998 መገባደጃ ላይ ለረዥም ጊዜ ሲጓጉለት የቆዩትን በረከት አግኝተዋል። ከ30 ከሚበልጡ ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባላት ይህችን አገር ጎበኙ። ከእነርሱም ጋር ሌሎች 15 ልዑካን ነበሩ። ጎብኚዎቹ የአውስትራሊያ፣ የኦስትሪያ፣ የቤልጅየም፣ የታላቋ ብሪታንያ፣ የኢጣሊያ፣ የኒው ዚላንድ እና የፖርቶ ሪኮ ዜጎች ነበሩ።
ይህ ወቅት 82,258 ለሚሆኑት የመንግሥቱ አስፋፊዎችና በ1998 በሚያዝያ ወር ላይ ተከብሮ በነበረው የጌታ ራት በዓል ላይ አብረዋቸው ለተገኙት 87,890 ሰዎች ሊረሳ የማይችል ታሪካዊ ክንውን ነበር።
ከታኅሣሥ 1 እስከ 7, 1998 ሎይድ ቤሪ፣ ጆን ባር እና ጌሪት ሎሽ ሃቫና የሚገኘውን የቤቴል ቤት የጎበኙ ሲሆን “የአምላክ የሕይወት መንገድ” በሚል ጭብጥ በኩባ ከተደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች በአንዳንዶቹ ላይ ተገኝተዋል። ከተጓዥ ሽማግሌዎች ጋር መገናኘት በመቻላቸውና ከኩባ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር በተሻለ መንገድ በመተዋወቃቸው ተደስተዋል።
“ይህ እኔም ሆንኩ ባለቤቴ ምንጊዜም የማንረሳው ከፍተኛ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴ ነው” በማለት ጆን ባር ተናግሯል። “በኩባ ያሉ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለእውነት ከፍተኛ ቅንዓት አላቸው! ዓለም አቀፋዊው የወንድማማች ማኅበራችን በእርግጥም ውድ እንደሆነ አስገንዝቦኛል!” “ይህ ታሪካዊ ሳምንት በዚያ አገር የሚኖሩ ወንድሞቻችን ያሉበትን ሁኔታ ይበልጥ እንድገነዘብ አስችሎኛል” በማለት ሎይድ ባሪ ጨምሮ ተናግሯል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በኩባ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ የአምልኮ ነፃነት ያገኙ ሲሆን ይኸው ነፃነታቸው ቀጣይነት እንዲኖረው የኩባ ባለ ሥልጣናት ምኞት መሆኑን ባለ ሥልጣናቱ ከሰጡት አስተያየት ለመረዳት ይቻላል።
መስከረም 1994 ሃቫና በሚገኘው የቤቴል ቤት የኅትመት ሥራ ተጀምሮ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች እንደገና በይፋ መሰብሰብና ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበክ ችለው ነበር። ከዚያም በ1998 ባለ ሥልጣናቱ ሦስት የአስተዳደር አካል አባላትን ጨምሮ 18 የይሖዋ ምሥክሮችን ያቀፈ አንድ ዓለም አቀፍ ልዑክ ይህን ጉብኝት እንዲያደርግ ፈቀዱ።
ዳግም መገናኘት ያስገኘው ደስታ
ልዑካኑ ሃቫና በሚገኘው ጆሴ ማርቲ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ተወካዮችና አንድ የቤቴል ቤተሰብ ቡድን በአውሮፕላን ማረፊያው በመገኘት ሞቅ ያለ አቀባበል አድርገውላቸዋል። የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ሚልተን ሄንሸል በ1961 ለመጨረሻ ጊዜ በኩባ ያደረገውን ጉብኝት የተመለከተ አንድ ወንድምም ከእነዚህ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ጋር የነበረ ሲሆን በዚያን ወቅት የ12 ዓመት ልጅ ነበር። አሁን ተጓዥ የበላይ ተመልካች ነው።
ልዑካኑ ወደ ቤቴል ቤት ሲደርሱ ለዚህ ወቅት አንድ ወንድም አሳድጓቸው በነበሩት ግራዲዮለስ፣ ጽጌረዳ፣ ጋስሚን በሚባል አበባና ቢጫና ቀይ ቀለም ባላቸው አበቦች ከፍተኛ አቀባበል ተደረገላቸው። የቤቴል ቤተሰቦች ልዑካኑን በሚቀበሉበት ጊዜ እንባቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው ነበር። ከዚያም የኩባ የአሳማ ጥብስ፣ ሩዝና ባቄላ፣ ሰላጣ፣ ዩካ በሞኮ (ከነጭ ሽንኩርትና ከወይራ ዘይት የተዘጋጀ ስጎ) እና ፍራፍሬ በአንድነት ተመገቡ። ከምግብ ግብዣው በኋላ እያንዳንዱ የአስተዳደር አካል አባል የቤቴልን አገልግሎት ከፍ አድርጎ መመልከትን የሚያበረታታ ገንቢ የሆነ ንግግር አቀረቡ። በተለይ ደግሞ ወንድም ሎሽ ንግግሩን በስፓንኛ ማቅረቡ የሰጠው ሐሳብ ይበልጥ ቀስቃሽ እንዲሆን አድርጎታል። የቤቴል ቤተሰቡ 48 ቋሚ ፈቃደኛ ሠራተኞችንና 18 ጊዜያዊ ረዳት ሠራተኞችን ያቀፈ ነው።
ምንም እንኳ ኩባ ለሚገኙ ወንድሞች መጻሕፍትና መጽሐፍ ቅዱሶች የሚታተሙት በኢጣሊያ ቢሆንም ጥቁርና ነጭ ቀለም መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ግን በሁለት የማባዣ ማሽኖች አማካኝነት እዚያው አገር ይታተማሉ። የሚፈለጉትን ያህል መጽሔቶች አትሞ ለማውጣት በጣም ጠባብ በሆኑ ክፍሎች ውስጥ ረዥም ሰዓታት የሚፈጅ ተደጋጋሚ የጉልበት ሥራ ማከናወንን ይጠ ይቃል። ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ለይሖዋ የሚያቀርቡትን ይህን ውድ አገልግሎት በጣም ከፍ አድርገው ይመለከቱታል።—2 ቆሮንቶስ 4:7
የአውራጃ ስብሰባ ጎላ ያሉ ገጽታዎች
አሥራ ስምንቱ ልዑካን በሃቫና፣ በካማጉዌ እና በሆልፊን በሚደረጉት ሦስት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይችሉ ዘንድ በሦስት ቡድን ተከፈሉ። በርካታ ሽማግሌዎችንና አቅኚዎችን ጨምሮ ብዙ ወንድሞችንና እህቶችን ያቀፈ አንድ ቡድን በእያንዳንዱ የስብሰባ ቦታ ላይ ለአንድ ቀን ብቻ እንዲገኝ ተጋብዞ ነበር። በዚያው አገር ያሉ ወንድሞች ይህ ወቅት ልዩ እንደሚሆን ተነግሯቸው የነበረ ቢሆንም የአስተዳደር አካል አባላት በስብሰባው ላይ እንደሚገኙ ግን ፈጽሞ አያውቁም ነበር። እነዚህ የተወደዱ ወንድሞችና ሚስቶቻቸው ዓርብ ዕለት ጠዋት ተኮናትረው ከመጡበት አውቶቡስ ሲወርዱ ወንድሞች የተሰማቸውን ስሜት ልትገምቱ ትችላላችሁ!
ወንድሞች ባለ ሥልጣናትን ካስፈቀዱ በኋላ ለስብሰባ ምቹ አድርገው ባዘጋጁት ሜዳ ላይ ተሰበሰቡ። በሃቫናው የመሰብሰቢያ ቦታ በአንደኛው መግቢያ ድንጋይ ላይ “መዝሙር 133:1” ተቀርጾ ነበር። ይህም “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፣ እነሆ፣ መልካም ነው፣ እነሆም፣ ያማረ ነው” የሚለውን ጥቅስ ወንድሞች እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል። በእርግጥም በዚያ ቦታ ስብሰባው በተካሄደበት ወቅት ጥሩና አስደሳች የሆነ ክርስቲያናዊ ኅብረትና አንድነት ይታይ ነበር።
ጎብኚዎቹ ግሩም ሆነው በቀረቡት ንግግሮችና ቃለ ምልልሶች እንደተደነቁ የተናገሩ ሲሆን ስለ ጥንቷ ባቢሎን በሚተርከው በዳንኤል ምዕራፍ 3 ላይ በሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ላይ ተመሥርቶ በቀረበው ድራማ በጣም ተነክተዋል። አንዲት እህት አስተያየቷን ስትሰጥ “ተዋንያኑ በሙሉ በሚያስደንቅ መንገድ ተክነውታል፤ የድምፅ ቅንብሩ በሚገባ የተዋጣ ከመሆኑ የተነሳ ድምፁ የቴፕ እንደሆነ ለማወቅ እንኳ ያዳግት ነበር። . . . ጨካኙ ባቢሎናዊ በትክክል ጨካኝ ተደርጎ ተሥሏል፤ እንዲሁም ሦስቱ ዕብራውያን ጽኑና ከአቋማቸው ፍንክች የማይሉ ነበሩ” በማለት ተናግራለች።
ስብሰባዎቹን ለመመልከት የመጡ የሃይማኖት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ተወካዮችና ሌሎች የመንግሥት ባለ ሥልጣናት የወንድሞችን ቅንጅትና ጥሩ ምግባር አድንቀዋል። ወንድም ቤሪ ለጉብኝት ለመጡት ልዑካን የኩባ ባለ ሥልጣናት ላደረጉላቸው ጥሩ አቀባበል የተሰማውን ደስታ ገልጿል። ለቀረቡት ንግግሮችና በመጨረሻም ስብሰባው እንዲደረግ ፈቃድ ለሰጡት ባለ ሥልጣናት ያላቸውን አድናቆት የገለጹት ቆመው ለረዥም ደቂቃ በቆየ ጭብጨባ ነበር። “ይህ ከጠበቅነው በላይ ነው። መለስተኛ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ነው!” በማለት አንድ ክርስቲያን ቤተሰብ ተናግሯል። “ይሖዋ የገባውን ቃል ለመፈጸም ታላቅ ኃይል እንዳለው የሚያረጋግጥ እጅግ አስደናቂ የሆነ ስብሰባ ነበር።”
ከዚህም በተጨማሪ ስብሰባዎቹ ሌሎች ሰዎች ምሥክሮቹን በተሻለ መንገድ እንዲያውቋቸው ጥሩ አጋጣሚ ከፍተዋል። አንድ የአውቶቡስ ሾፌር ቅዳሜና እሁድ በስብሰባው ላይ ተገኘ። ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ነገሮችን የሰማ መሆኑን የገለጸ ሲሆን አሁን ግን የይሖዋ ምሥክሮች ጥሩና ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውን አውቋል።
“ፈጽሞ ልንዘነጋቸው የማንችላቸው ነገሮች”
የኩባ ሕዝብ የሚያሳየው ሞቅ ያለ ስሜትና የወዳጅነት መንፈስ ልዑካኑን በጣም ነክቷቸዋል። ኩባውያን ታታሪ፣ ሥርዓታማና ደጎች ናቸው። “ፈጽሞ የማያውቁን ቢሆኑም እንኳ በተደጋጋሚ ረድተውናል” በማለት አንድ ልዑክ ተናግሯል።
ልዑካኑ በኩባ ያሉት ምሥክሮች ባሳዩት እምነት፣ ደስታና ፍቅር በጥልቅ ተነክተዋል። ከፍተኛ እንቅፋቶች ያሉባቸው ቢሆንም እንኳ ይሖዋን መሸሸጊያቸው አድርገውታል። (መዝሙር 91:2) “በኩባ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረግሁት በዚህ ጉብኝት የአገሪቷ ውበት፣ ያገኘኋቸው ሰዎች የሚያሳዩት ጥሩ ጠባይ ከሁሉም በላይ ደግሞ የኩባ ምሥክሮች ያላቸው ብሩህ አመለካከት ስሜቴን በጥልቅ ነክተውታል። የመንግሥት መዝሙራችን እንዲህ ባለ ከልብ በመነጨ ስሜት ሲዘመርና መንፈሳዊ ትምህርቶች ልባቸውን የነካቸው ሰዎች እንዲህ ባለ ረዥም ጭብጨባ ስሜታቸውን ሲገልጹ ፈጽሞ ዓይቼ አላውቅም! እነዚህ ፈጽሞ ልንዘነጋቸው የማንችላቸው ትዝታዎች ናቸው። ሁልጊዜ ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን” በማለት ጆን ባር ተናግሯል።
መዝሙር 97:1 “ብዙ ደሴቶችም ደስ ይበላቸው” ይላል። በእርግጥም በደሴቲቷ ኩባ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን ለማምለክ የሚያስችል እየጨመረ የሚሄድ ነፃነት በማግኘታቸውና ታሪካዊ በሆነው በዚህ ዓለም አቀፍ የልዑካን ቡድን ጉብኝት ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸዋል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የአስተዳደር አካል አባላት ለባለ ሥልጣናት ስጦታ አድርገው በሚሰጧቸው መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ ሲፈርሙ
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በርካታ ቤተሰቦች በኩባ በተደረጉት “የአምላክ የሕይወት መንገድ” በተባሉት ልዩ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተዋል
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1994 እንደገና የተከፈተው ሃቫና የሚገኘው የቤቴል ቤት