ክርስቲያን ጉባኤ የብርታት ምንጭ
በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል መጀመሪያ ላይ የምትገኘው ፖፒ ከወላጆቿ ጋር ግልጽ የሐሳብ ግንኙነት ባለመኖሩ ምክንያት በተከሰተው የቤተሰብ ችግር ተበሳጭታ ነበር።a ለአንድ ክርስቲያን ሽማግሌና ለሚስቱ የልቧን አውጥታ ከተናገረች በኋላ እንዲህ ስትል ጻፈችላቸው:- “ጊዜያችሁን ሠውታችሁ ስላነጋገራችሁኝ በጣም አመሰግናችኋለሁ። እንደ እናንተ ያለ አሳቢ ሰው ማግኘቴ ምን ያህል እንደሚያጽናናኝ ልነግራችሁ አልችልም። አሉኝ የምላቸውና ችግሬን የማወያያቸው ሰዎች ስለ ሰጠኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።”
በቅርቡ ባሏ የሞተባትና በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሁለት ልጆች ያሏት ቱላ የምትባል ሴት በከፍተኛ ጭንቀትና የኢኮኖሚ ችግር ተውጣ ነበር። በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ አንድ ክርስቲያን ባልና ሚስት እሷንም ሆነ ልጆቿን ዘወትር በመጠየቅ ያበረታቷቸው ነበር። ችግሯን በአሸናፊነት ከተወጣች በኋላ ለእነዚህ ባልና ሚስት የሚከተሉት ቃላት የተጻፈበት ካርድ ላከችላቸው:- “ሁልጊዜ በጸሎቴ አስታውሳችኋለሁ። ከጎኔ በመቆም ያደረጋችሁልኝን እርዳታና የሰጣችሁኝን ድጋፍ ምንጊዜም አልረሳውም።”
ይህ ዓለም የሚያሳድራቸው ተጽእኖዎች እየጨመሩ በመምጣታቸው ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ‘ከባድ ሸክም እንደ ተሸከምህ’ ሆኖ ይሰማሃልን? (ማቴዎስ 11:28) ‘ጊዜና አጋጣሚ’ ያመጧቸው ክስተቶች በሕይወትህ ላይ አሳዛኝ ትዝታ ጥለውብህ አልፈዋልን? (መክብብ 9:11 NW) እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በአንተ ላይ ብቻ የደረሰ አይደለም። ሆኖም ጭንቀት የነበረባቸው በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ጠቃሚ እርዳታ እንዳገኙ ሁሉ አንተም ልታገኝ ትችላለህ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ይኖር የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ በተለይ አንዳንድ መሰል አማኞች ‘የብርታት ምንጭ’ እንደሆኑለት ተናግሯል። (ቆላስይስ 4:10, 11) አንተም ተመሳሳይ የሆነ ተሞክሮ ሊያጋጥምህ ይችላል።
ድጋፍና እርዳታ
በግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ጉባኤ” የሚለው ቃል ኤክሊሲአ ከተባለው የግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ሲሆን አንድ ላይ የተሰባሰቡ ሰዎች ቡድን የሚል ትርጉም አለው። ቃሉ መተባበርና በጋራ መደጋገፍ የሚሉ ሐሳቦችን የሚያስተላልፍ ነው።
የክርስቲያን ጉባኤ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ይደግፋል፤ የመንግሥቱን ምሥራችም ያውጃል። (1 ጢሞቴዎስ 3:15፤ 1 ጴጥሮስ 2:9) ይህም ብቻ ሳይሆን ጉባኤው በሥሩ ለተሰባሰቡ ሰዎች መንፈሳዊ ድጋፍና እርዳታ ይሰጣል። በዚያም አንድ ሰው በአስቸጋሪ ጊዜያት ሌሎችን ለመርዳት እንዲሁም ለማጽናናት ዝግጁና ፈቃደኞች የሆኑ አፍቃሪ፣ አሳቢና ተንከባካቢ ወዳጆችን ማግኘት ይችላል።—2 ቆሮንቶስ 7:5-7
ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች ከጉባኤው የማያቋርጥ እንክብካቤና ጥበቃ ያገኛሉ። መዝሙራዊው በተሰበሰቡ የአምላክ ሕዝቦች መካከል በሚሆንበት ጊዜ ደስ እንደሚለውና የደኅንነት ስሜት እንደሚሰማው ተናግሯል። (መዝሙር 27:4, 5፤ 55:14፤ 122:1) በተመሳሳይም ዛሬ የክርስቲያን ጉባኤ አንዳቸው ሌላውን በሚያንጹና በሚያበረታቱ ሰዎች የተገነባ የመሰል አማኞች ስብስብ ነው።—ምሳሌ 13:20፤ ሮሜ 1:11, 12
የጉባኤው አባላት ‘ለሰው ሁሉ በተለይም ለእምነት መሰሎቻቸው መልካም እንዲያደርጉ’ ትምህርት ይሰጣቸዋል። (ገላትያ 6:10) የሚማሩት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት የወንድማማች መዋደድና የጠለቀ ፍቅር እንዲያሳዩ ያነሳሳቸዋል። (ሮሜ 12:10፤ 1 ጴጥሮስ 3:8) በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች ደጎች፣ ሰላማውያንና ከአንጀት የሚራሩ ለመሆን ይጥራሉ። (ኤፌሶን 4:3) ስሜት አልባ አምላኪዎች ከመሆን ይልቅ ለሌሎች ፍቅራዊ አሳቢነታቸውን ያሳያሉ።—ያዕቆብ 1:27
ስለዚህ ከባድ ሸክም የተጫናቸው ሰዎች በጉባኤው ውስጥ ሞቅ ያለ ቤተሰባዊ ሁኔታ ሊያገኙ ይችላሉ። (ማርቆስ 10:29, 30) የጠበቀ ትስስርና ፍቅር ባለው ቡድን ውስጥ የታቀፉ መሆናቸውን ማወቃቸው ያጠነክራቸዋል። (መዝሙር 133:1-3) “ታማኝና ልባም ባሪያ” በጉባኤው አማካኝነት ገንቢ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ “በጊዜው” ያቀርባል።—ማቴዎስ 24:45
አፍቃሪ ከሆኑ የበላይ ተመልካቾች የሚገኝ እርዳታ
የክርስቲያን ጉባኤው አባላት መንፈሳዊ ድጋፍና ማበረታቻ የሚሰጡ አፍቃሪ፣ የሰው ስሜት የሚገባቸውና ብቃት ያላቸው እረኞች በጉባኤ ውስጥ እንደሚያገኙ ሊጠብቁ ይችላሉ። ይህን የመሰለ ባሕርያት ያሏቸው እረኞች “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ” ናቸው። (ኢሳይያስ 32:1, 2) በመንፈስ የተሾሙ ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች የአምላክ ንብረት ለሆኑት በግ መሰል ሰዎች ያስባሉ፤ የታመሙትንና የተጨነቁትን ያበረታታሉ፤ እንዲሁም የተሳሳቱትን ለማረም ይጥራሉ።—መዝሙር 100:3፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3
እርግጥ የጉባኤው የሽማግሌዎች አካል መሰል አማኞች የሚያጋጥሟቸውን አካላዊ ወይም አእምሯዊ የጤና እክሎች የመፈወስ ብቃት ያላቸው የሠለጠኑ ቴራፒስቶችን ወይም የሕክምና ባለሞያዎችን ያቀፈ አይደለም። ይህ የነገሮች ሥርዓት እስካለ ድረስ በሽተኞች ‘ሐኪም ያስፈልጋቸዋል።’ (ሉቃስ 5:31 የ1980 ትርጉም) ሆኖም እንዲህ ያሉ እረኞች መንፈሳዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ሊረዱ ይችላሉ። (ያዕቆብ 5:14, 15) በተጨማሪም ሽማግሌዎች ከተቻለ ሌላ እርዳታም እንዲሰጥ ዝግጅት ያደርጋሉ።—ያዕቆብ 2:15, 16
ይህን ከመሰለው ፍቅራዊ ዝግጅት በስተጀርባ ያለው ማን ነው? ይሖዋ አምላክ ነው! ይሖዋ “በጎቼን እሻለሁ እፈልግማለሁ። . . . ከተበተኑት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ። . . . በጎቼን አሰማራለሁ አስመስጋቸውማለሁ” ብሎ እንደሚናገር ነቢዩ ሕዝቅኤል ገልጿል። በተጨማሪም አምላክ አቅመ ደካማ ለሆኑት በጎች ያስባል።—ሕዝቅኤል 34:11, 12, 15, 16
በተገቢው ጊዜ የሚቀርብ እውነተኛ እርዳታ
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እውነተኛ እርዳታ በእርግጥ ይገኛልን? አዎን፣ የሚከተሉት ምሳሌዎችም ጉባኤው እርዳታ ያበረከተባቸውን የተለያዩ ሁኔታዎች የሚያሳዩ ናቸው።
◆ የምንወደውን ሰው በሞት ማጣት። የአና ባለቤት በጠና ታመመና ሞተ። “ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የክርስቲያን ወንድሞች ሞቅ ያለ ፍቅር ተለይቶኝ አያውቅም” ትላለች። “የእምነት መሰሎቼ ከልብ በመነጨ ስሜት እቅፍ በማድረግ የሚያሳዩኝን ፍቅር ጨምሮ ዘወትር የሚሰነዝሯቸው የድጋፍና የማበረታቻ ቃላት በጭንቀት ከመዋጥ ይልቅ እንድበረታታ አድርጎኛል። ለዚህም ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። ያሳዩኝ ፍቅር የሚደግፈኝ፣ የሚያነቃቃኝና ከአንጀት የሚጨነቅልኝ ሰው እንዳለ እንዲሰማኝ አድርጎኛል።” አንተም የምትወደውን ሰው በሞት በማጣትህ ምክንያት በሐዘን እየተሰቃየህ ይሆናል። እንዲህ ባሉት ጊዜያት የጉባኤው አባላት እጅግ አስፈላጊ የሆነ ማጽናኛና ስሜታዊ ድጋፍ ሊሰጡ ይችላሉ።
◆ ሕመም። አርተር በፖላንድ የሚገኝ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሲሆን በመካከለኛው እስያ የሚገኙ ጉባኤዎችን አዘውትሮ በመጎብኘት በመንፈሳዊ ያጠነክራቸው ነበር። በአንድ ወቅት በጉብኝት ላይ እያለ በጠና ይታመማል፤ በቶሎ ለማገገምም አልቻለም ነበር። አርተር በጥልቅ አድናቆት ተሞልቶ “[በካዛክስታን ባለች አንዲት ከተማ] ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች እንዴት እንደተንከባከቡኝ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ” ይላል። “ጭራሽ የማላውቃቸው ወንድሞች፣ እህቶችና ሌላው ቀርቶ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ገንዘብ፣ ምግብና መድኃኒት ያመጡ ነበር። . . . ይህን በማድረጋቸው ደግሞ እጅግ ተደስተው ነበር።
“ጥቂት ገንዘብና የሚከተለውን ደብዳቤ የያዘ ፖስታ ሲደርሰኝ ምን እንደ ተሰማኝ ልትገምቱ ትችላላችሁ:- ‘ውድ ወንድም፣ ሞቅ ያለ ሰላምታዬ ይድረስህ። እማዬ አይስ ክሬም እንድገዛበት ገንዘብ ሰጥታኝ ነበር። ይሁን እንጂ ለመድኃኒት መግዣ እንዲሆንህ ለአንተ ልሰጠው ወሰንኩ። መቼም ቶሎ እንደምትድን ተስፋ አደርጋለሁ። ይሖዋ የሚፈልገን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ አይደለም። መልካሙን ሁሉ እመኝልሃለሁ። ድነህ ሌሎች ጥሩ ጥሩ ታሪኮችን ትነግረናለህ። ቮቫ።’” አዎን፣ በዚህ ሁኔታ ላይ እንደታየው በጉባኤው ውስጥ የሚገኙ በእድሜ የገፉም ሆኑ ልጆች የታመሙ ወንድሞችን ሊያበረታቱ ይችላሉ።—ፊልጵስዩስ 2:25-29
◆ ጭንቀት። ቴሪ አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ሆና ለማገልገል በጣም ትመኝ ነበር። ይሁንና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት አቅኚነቷን ለማቆም ተገደደች። “በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት በመሞከሬና አንድ ዓመት እንኳ ሳላገለግል በማቆሜ ከፍተኛ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማኝ” በማለት ትናገራለች። ቴሪ አንድ ሰው በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱ የተመካው ለእሱ በሚያቀርበው የአገልግሎት መጠን ነው የሚል የተሳሳተ አመለካከት ነበራት። (ከማርቆስ 12:41-44 ጋር አወዳድር።) ከፍተኛ ጭንቀት ስላደረባት ራሷን ከሰዎች አገለለች። ሆኖም ከጉባኤዋ የሚያነቃቃ እርዳታ አገኘች።
ቴሪ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች:- “አንዲት በእድሜ የገፋች አቅኚ እህት ረዳችኝ። የሆዴን ሁሉ ዝርግፍ አድርጌ ስነግራት አዳመጠችኝ። ከቤቷ ስወጣ ከባድ ሸክም ከላዬ ላይ የተነሣ ያህል ቅልል አለኝ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህች አቅኚ እህትና የጉባኤ ሽማግሌ የሆነው ባሏ ጠቃሚ የሆነ እርዳታ አበርክተውልኛል። ሁልጊዜ እየደወሉ ስለ ደኅንነቴ ይጠይቃሉ። . . . አንዳንድ ጊዜ በቤተሰብ ጥናታቸው ላይ እንድገኝ ያደርጉ የነበረ ሲሆን ይህም ቤተሰቦች ተቀራርበው መኖራቸው አስፈላጊ መሆኑን እንድገነዘብ አድርጎኛል።”
ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖችን ጨምሮ ብዙዎች የጭንቀት፣ የተስፋ መቁረጥና የብቸኝነት ስሜት የሚሰማቸው መሆኑ አዲስ ነገር አይደለም። በአምላክ ጉባኤ ውስጥ ፍቅራዊና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ እርዳታ የሚገኝ በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን!—1 ተሰሎንቄ 5:14
◆ የተፈጥሮና ድንገተኛ አደጋዎች። ቤቱ እንዳለ ከነንብረቱ በእሳት በተቃጠለበት አራት አባላት ባሉት አንድ ቤተሰብ ቦታ ራስህን አስቀምጥ። ወዲያውኑ “ለዘላለም ከአእምሯችን የማይጠፋና በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለውን እውነተኛ ፍቅር ቁልጭ አድርጎ ያሳየን አበረታች ተሞክሮ” አጋጥሞናል በማለት የሚከተለውን ተናግረዋል:- “አደጋው ከደረሰ በኋላ ምንም ያህል ሳይቆይ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከልብ ያዘኑ መሆናቸውንና ከጎናችን በመቆም እንደሚደግፉን የሚገልጹ በርካታ የስልክ ጥሪዎቻቸው ደረሱን። ስልኩ ያለማቋረጥ ይጠራ ነበር። ሁሉም ሰው ያሳየን በነበረው ከልብ የመነጨ አሳቢነትና ፍቅር በጥልቅ ከመነካታችን የተነሳ በአመስጋኝነት አለቀስን።”
ብዙም ሳይቆይ በጉባኤው ሽማግሌዎች አማካኝነት በርካታ ወንድሞችን ያቀፈ አንድ ቡድን ከተደራጀ በኋላ በጥቂት ቀናት ውስጥ ለቤተሰቡ አዲስ ቤት ተሠራለት። አንዲት ጎረቤት “ይህን ማየት አለባችሁ! ወንድ፣ ሴት፣ ጥቁር፣ ነጭ ሳይል ሁሉም ዓይነት ሰው በአንድነት ይሠራል!” ስትል በከፍተኛ አድናቆት ተናግራለች። ይህ የወንድማማች ፍቅር ጉልህ ማስረጃ ነው።—ዮሐንስ 13:35
በተጨማሪም መሰል ክርስቲያኖች ለቤተሰቡ ልብስ፣ ምግብና ገንዘብ ሰጥተዋል። አባትየው እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:- “ይህ የሆነው ሰዎች ስጦታ በሚለዋወጡበት የገና ወቅት ነበር፤ ሆኖም ይህን የመሰለ ልባዊና የተትረፈረፈ ልግስና የእኛን ያህል ያገኘ የለም ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን።” ቤተሰቡ አክሎም “የእሳት ቃጠሎው ትውስታዎች ቀስ በቀስ እየተረሱ አስደሳች በሆኑ የደግነት ተግባራት ትውስታዎችና ጥሩ ወዳጆቻችን ትተው ባለፏቸው ትዝታዎች እየተተኩ ነው። እንዲህ ያለ አስደናቂና አንድነት ያለው የወንድሞች ቤተሰብ በምድር ላይ ስላለን አፍቃሪውን የሰማዩ አባታችን ይሖዋን እናመሰግናለን፤ እኛም የዚህ ቤተሰብ አባላት በመሆናችን ደስተኞች ነን!”
እርግጥ እንዲህ የመሰለ ድንገተኛ አደጋ በደረሰ ጊዜ ሁሉ ይህን የመሰለ እርዳታ ማግኘትም ሆነ መጠበቅ አይቻልም። ይሁን እንጂ ይህ አጋጣሚ ጉባኤው ሊሰጠው የሚችለውን ድጋፍ ግሩም አድርጎ የሚያሳይ ነው።
ላይኛው ጥበብ
ብዙዎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የእርዳታና የብርታት ምንጭ የሚሆን ሌላ ነገር አግኝተዋል። ይህ ምንድን ነው? በ“ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚዘጋጁ ጽሑፎች ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ በዋነኛነት የሚጠቀሱት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ናቸው። እነዚህ ጽሑፎች ጥልቅ ማስተዋል የሚንጸባረቅባቸው ምክሮችንና ተግባራዊ መመሪያዎችን ለመስጠት በዋነኛነት የሚጠቀሙት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን መለኮታዊ ጥበብ ነው። (መዝሙር 119:105) የአእምሮ ጭንቀትን፣ በአካል ላይ ከሚደርስ ጥቃት ማገገምን፣ የተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን፣ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንዲሁም በታዳጊ አገሮች ውስጥ ብቻ የሚገኙ ችግሮችን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ኃላፊነት በሚሰማቸውና በታመኑ ሰዎች ከተደረገ ምርምር የተገኘ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት ይቀርባል። ከሁሉም በላይ ደግሞ እነዚህ ጽሑፎች የአምላክ መንገድ ከሁሉ የተሻለው የሕይወት መንገድ መሆኑን ይገልጻሉ።—ኢሳይያስ 30:20, 21
የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በየዓመቱ አድናቆታቸውን ለመግለጽ የሚፈልጉ ሰዎች የሚጽፏቸው በሺህ የሚቆጠሩ ደብዳቤዎች ይደርሱታል። ለምሳሌ ያህል ራስን ስለ መግደል የሚናገር በንቁ! መጽሔት ላይ የወጣ ርዕስን አስመልክቶ በሩሲያ የሚገኝ አንድ ወጣት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ጭንቀት ስለነበረብኝ . . . ራሴን ለመግደል ብዙ ጊዜ አስብ ነበር። ይህ ርዕስ አምላክ ችግሮቼን እንድወጣ እንደሚረዳኝ ያለኝን እምነት አጠንክሮልኛል። አምላክ እንድኖር ይፈልጋል። በዚህ ርዕስ አማካኝነት ለሰጠኝ ድጋፍ አመሰግነዋለሁ።”
በዚህ ዓለም ውስጥ ያሉ ችግሮች ልትቋቋመው እንደማትችለው ከባድ ማዕበል ቢሆኑብህ እንኳ የክርስቲያን ጉባኤ አስተማማኝ መሸሸጊያ እንደሚሆንህ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። አዎን፣ የዚህ ፍቅር አልባ ዓለም በረሃ ጉልበትህን እያሟጠጠው ከሆነ መልሶ ሊያበረታህ የሚችል በበረሃ ውስጥ ካለ ገነት ጋር የሚመሳሰል ነገር በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ልታገኝ ትችላለህ። በጠና የታመመ ባለቤቷን በማስታመም የተሳካላት አንዲት ክርስቲያን ሴት እንዲህ ያለውን ድጋፍ ካገኘች በኋላ የተናገረቻቸውን ቃላት አንተም ልታስተጋባ ትችላለህ:- “ወንድሞች ባሳዩን ፍቅርና እንክብካቤ ምክንያት ይሖዋ ከዚህ ችግር በእጁ ይዞ እንዳወጣን ያህል ይሰማኛል። ዕጹብ ድንቅ የሆነው የይሖዋ ድርጅት አባል በመሆኔ እጅግ አመስጋኝ ነኝ!”
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሞቹ ተቀይረዋል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ለታመሙ፣ የሚወዱት ሰው በሞት ለተለያቸውና ለሌሎችም የማበረታቻ ምንጭ ልንሆንላቸው እንችላለን