የአምላክን ቃል በቤተሰብ መልክ አዘውትራችሁ አጥኑ
“ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም።”—ማቴዎስ 4:4
1. የቤተሰብ ራሶች የይሖዋን መንገዶች ለልጆቻቸው እንዲያስተምሩ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ይሖዋ አምላክ የቤተሰብ ራሶች ያለባቸውን ልጆቻቸውን የማስተማር ኃላፊነት በተመለከተ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። ልጆች እንዲህ ያለውን መመሪያ ማግኘታቸው ለአሁኑ ሕይወት ያስታጥቃቸዋል፤ ወደፊት ለሚመጣው ሕይወትም እንዲዘጋጁ ሊረዳቸው ይችላል። አምላክን ወክሎ የመጣ አንድ መልአክ “የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ” ቤተሰቡን የማስተማር ኃላፊነት እንዳለበት ለአብርሃም ጠቁሞታል። (ዘፍጥረት 18:19) እስራኤላውያን ወላጆች አምላክ እስራኤልን ከግብፅ እንዴት እንዳወጣና ኮሬብ በሚገኘው የሲና ተራራ ላይ ሕጉን እንዴት እንደሰጣቸው ለልጆቻቸው እንዲያብራሩ ተነግሯቸው ነበር። (ዘጸአት 13:8, 9፤ ዘዳግም 4:9, 10፤ 11:18-21) ክርስቲያን የቤተሰብ ራሶች ልጆቻቸውን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” እንዲያሳድጉ ምክር ተለግሷቸዋል። (ኤፌሶን 6:4) ይሖዋን የሚያገለግለው አንደኛው ወላጅ ብቻ ቢሆንም እንኳ ይኸው ግለሰብ የይሖዋን መንገዶች ለልጆቹ ለማስተማር መትጋት ይኖርበታል።—2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:14, 15
2. በቤት ውስጥ ልጆች ከሌሉ የቤተሰብ ጥናት ማድረጉ አስፈላጊ ነው? አብራራ።
2 እንዲህ ሲባል ግን የአምላክን ቃል በቤተሰብ መልክ ማጥናት የሚኖርባቸው ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች ብቻ ናቸው ማለት አይደለም። አንድ ባልና ሚስት የሚያሳድጓቸው ልጆች ባይኖሯቸውም እንኳ የቤተሰብ ጥናት ማድረጋቸው ለመንፈሳዊ ነገሮች ከፍተኛ አድናቆት እንዳላቸው የሚያሳይ ነው።—ኤፌሶን 5:25, 26
3. የቤተሰብ ጥናት ቋሚ መሆኑ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?
3 ይሖዋ በምድረ በዳ ለነበሩት እስራኤላውያን “ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት [አይኖርም]” በማለት ከሰጠው ትምህርት ጋር በሚስማማ መንገድ ያለማሰለስ መመሪያ መስጠቱ ከሁሉ የተሻለ ጥቅም ያስገኛል። (ዘዳግም 8:3) የአንዱ ቤተሰብ ሁኔታ ከሌላው የሚለይ በመሆኑ አንዳንድ ቤተሰቦች አንድ ቀን መድበው የቤተሰብ ጥናታቸውን ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ በየቀኑ አጠር አጠር ያሉ የጥናት ጊዜያት እንዲኖራቸው ያደርጉ ይሆናል። የቤተሰብ ጥናታችሁን ለማድረግ ያወጣችሁት ዝግጅት ምንም ዓይነት ይሁን ምን እንዲያው ሲመች ብቻ የሚደረግ መሆን የለበትም። ለጥናት የሚሆን ጊዜ ‘ዋጁ።’ ለዚህ ሲባል የሚከፈለው ዋጋ ምንም አያስቆጭም። ይህ የቤተሰባችሁን አባላት ሕይወት የሚመለከት ጉዳይ ነው።—ኤፌሶን 5:15-17፤ ፊልጵስዩስ 3:16
በአእምሮአችሁ ልትይዙት የሚገባ ዓላማ
4, 5. (ሀ) ወላጆች ልጆቻቸውን በሚያስተምሩበት ጊዜ በአእምሮአቸው ሊይዙት የሚገባውን ዓላማ በሚመለከት ይሖዋ ለሙሴ ምን ብሎታል? (ለ) ይህስ በዛሬው ጊዜ ምን ማድረግን ያጠቃልላል?
4 የቤተሰባችሁን ጥናት በምትመሩበት ጊዜ ግልጽ የሆኑ ዓላማዎችን በአእምሮአችሁ መያዛችሁ የተሻለ ውጤት ላይ እንድትደርሱ ይረዳችኋል። ጥቂት ምሳሌዎችን ተመልከቱ።
5 በእያንዳንዱ የጥናት ወቅት ቤተሰቡ ለይሖዋ አምላክ ያለውን ፍቅር ለመገንባት ጥረት አድርጉ። የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባቱ በፊት በሞአብ ሜዳ ተሰብስቦ በነበረበት ወቅት ሙሴ ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ‘ከሕግ ሁሉ የሚበልጥ ትእዛዝ’ ብሎ የጠቀሰውን ነገር ተናግሮ ነበር። ይህ ምንድን ነው? “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” የሚለው ትእዛዝ ነው። (ማቴዎስ 22:36, 37፤ ዘዳግም 6:5) እስራኤላውያን ይህን ትእዛዝ በልባቸው ውስጥ እንዲያኖሩትና ለልጆቻቸውም እንዲያስተምሩት ሙሴ አጥብቆ መክሯቸዋል። ይህንንም ለማድረግ ይሖዋን ለምን መውደድ እንዳለባቸው፣ ይህ ዓይነቱ ፍቅር በተግባር እንዳይገለጽ የሚያግዱት ዝንባሌዎችና ጠባዮች የትኞቹ እንደሆኑና ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር በራሳቸው ሕይወት እንዲያሳዩ በተደጋጋሚ ጊዜ መግለጽ ያስፈልጋል። የእኛስ ልጆች ይህን የመሰለ መመሪያ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል? እንዴታ! እነርሱም ቢሆኑ ‘የልባቸውን ሸለፈት መገረዝ’ በሌላ አባባል ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር እንዳያሳዩ ጋሬጣ የሚሆንባቸውን ማንኛውንም እንቅፋት እንዲያስወግዱ እርዳታ ማግኘት ይኖርባቸዋል። (ዘዳግም 10:12, 16, 17፤ ኤርምያስ 4:4) በዓለም ላሉት ቁሳዊ ነገሮች ምኞት ማዳበርና በእንቅስቃሴዎቹ ሙሉ በሙሉ መዋጥ ከእነዚህ እንቅፋቶች መካከል ሊሆኑ ይችላሉ። (1 ዮሐንስ 2:15, 16) ለይሖዋ ያለን ፍቅር ሕያውና ሰማያዊ አባታችንን የሚያስደስቱ ነገሮችን እንድናደርግ የሚገፋፋን ሊሆን ይገባዋል። (1 ዮሐንስ 5:3) ከቤተሰብ ጥናታችሁ ዘላቂ ጥቅሞችን ማግኘት እንድትችሉ እያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ ይህን ፍቅር ሊያጠነክር በሚያስችል መንገድ መከናወን ይኖርበታል።
6. (ሀ) ትክክለኛ እውቀት ለማስጨበጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ትክክለኛ እውቀት የማግኘትን አስፈላጊነት ቅዱሳን ጽሑፎች ጠበቅ አድርገው የሚገልጹት እንዴት ነው?
6 የአምላክን የአቋም ደረጃዎች በተመለከተ ትክክለኛ እውቀት ማስጨበጥ። ይህ ምን ማድረግን ይጠይቃል? ይህ በአንድ መጽሔት ወይም በአንድ መጽሐፍ ላይ የሚገኝ መልስ ከማንበብ የበለጠ ነገር ይጠይቃል። ቁልፍ የሆኑት ቃላትና ዋና ዋናዎቹ ሐሳቦች ግልጽ እስኪሆኑ ድረስ መወያየትን ይጨምራል። አዲሱን ሰው ለመልበስ፣ በሕይወት ውስጥ ችግሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ላይ ለማተኮርና አምላክ የሚደሰትባቸውን ነገሮች ለማድረግ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት የግድ አስፈላጊ ነው።—ፊልጵስዩስ 1:9-11፤ ቆላስይስ 1:9, 10፤ 3:10
7. (ሀ) ቤተሰቡ የሚጠናውን ትምህርት ተግባራዊ ጠቀሜታ እንዲያስተውል ለማድረግ የትኞቹን ጥያቄዎች መጠቀሙ ሊረዳ ይችላል? (ለ) ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲህ ዓይነቱን ዓላማ ማድረግ ያለውን ጥቅም የሚያጎሉት እንዴት ነው?
7 የተጠናው ትምህርት ያለውን ተግባራዊ ጠቀሜታ እንዲገነዘቡ መርዳት። ይህን ዓላማ በመያዝ በእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ:- ‘ይህ ትምህርት ሕይወታችንን እንዴት ሊነካው ይገባል? አሁን እያደረግን ካለነው ለውጥ እንድናደርግ ይጠብቅብናል? ማስተካከያ ለማድረግ መፈለግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?’ (ምሳሌ 2:10-15፤ 9:10፤ ኢሳይያስ 48:17, 18) የሚጠኑት ትምህርቶች ባላቸው ተግባራዊ ጠቀሜታ ላይ በቂ ትኩረት መስጠቱ የቤተሰቡ አባላት ለሚያደርጉት መንፈሳዊ እድገት ከፍተኛ ድርሻ ሊኖረው ይችላል።
የማስተማሪያ መሣሪያዎችን በጥበብ ተጠቀሙባቸው
8. የባሪያው ክፍል መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚያገለግሉ ምን መሣሪያዎችን አቅርቧል?
8 “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለጥናት የሚያገለግሉ ብዙ መሣሪያዎችን አቅርቧል። መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት እገዛ የሚያበረክተው የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት በ131 ቋንቋዎች ይገኛል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ መጻሕፍት በ153 ቋንቋዎች፣ ብሮሹሮች በ284 ቋንቋዎች፣ የቴፕ ክሮች በ61 ቋንቋዎች፣ የቪዲዮ ክሮች በ41 ቋንቋዎች ይገኛሉ። ሌላው ቀርቶ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምርምር ለማድረግ የሚረዳ የኮምፒዩተር ፕሮግራም በ9 ቋንቋዎች ይገኛል!—ማቴዎስ 24:45-47
9. በቤተሰብ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወቅት በዚህ አንቀጽ ውስጥ የሚገኙት ጥቅሶች የሚሰጡትን ምክር እንዴት ልንሠራበት እንችላለን?
9 ብዙ ቤተሰቦች በቤተሰብ ጥናታቸው ወቅት በጉባኤ የሚያጠኑትን የመጠበቂያ ግንብ ርዕሶች ይዘጋጃሉ። ይህ ምንኛ ጠቃሚ ነው! መጠበቂያ ግንብ በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን የይሖዋ ሕዝቦች የሚገነባ መንፈሳዊ ምግብ ይዞ ይወጣል። በቤተሰብ አንድ ላይ ሆናችሁ መጠበቂያ ግንብ ስታጠኑ አንቀጾችን አንብባችሁ በመጽሔቱ ላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ከመስጠት የበለጠ ነገር አድርጉ። ማስተዋል ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት አድርጉ። ምዕራፋቸውና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱ ጥቅሶችን አውጥታችሁ አንብቡ። የቤተሰቡ አባላት ጥቅሶቹ እየተጠና ባለው አንቀጽ ውስጥ ከተዘረዘሩት ሐሳቦች ጋር የሚዛመዱት እንዴት እንደሆነ እንዲናገሩ ጋብዟቸው። የሁሉንም ልብ ለማግኘት ሞክሩ።—ምሳሌ 4:7, 23፤ ሥራ 17:11
10. ልጆች በጥናቱ ውስጥ ተካፋይ እንዲሆኑና ደስታ የሚያገኙበት ወቅት እንዲሆንላቸው ምን ሊደረግ ይችላል?
10 በቤተሰባችሁ ውስጥ ልጆች ካሉ ጥናታችሁ እንዲያው በዘልማድ የሚደረግ ሳይሆን የሚያንጽ፣ የሚስብና የሚያስደስት እንዲሆን ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? ሁሉም በሚጠናው ጽሑፍ ላይ ትኩረት ማድረግ ይችሉ ዘንድ ሁሉንም በተገቢው መንገድ ለማሳተፍ ጥረት አድርጉ። በተቻለ መጠን እያንዳንዱ ልጅ የራሱ መጽሐፍ ቅዱስና የሚጠናው መጽሔት ቅጂ እንዲኖረው ዝግጅት አድርጉ። ኢየሱስ ያሳይ የነበረውን ፍቅራዊ ስሜት በመኮረጅ አንድ አባት ሕፃን ልጁን አጠገቡ ሊያስቀምጠው ምናልባትም ሊያቅፈው ይችላል። (ከማርቆስ 10:13-16 ጋር አወዳድር።) የቤተሰቡ ራስ በሚጠናው ጽሑፍ ላይ ያለውን ሥዕል አንዱ ትንሽ ልጅ እንዲያብራራ ሊያደርግ ይችላል። ሌላው ልጅ ደግሞ አንድ ጥቅስ እንዲያነብ አስቀድሞ ሊመደብ ይችላል። በዕድሜ ከፍ ያለው ልጅ ደግሞ እየተጠና ያለው ትምህርት በየትኞቹ ወቅቶች ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ማብራሪያ እንዲሰጥ ሊመደብ ይችላል።
11. ሌሎች የቀረቡልን የማስተማሪያ መሣሪያዎች ምንድን ናቸው? እነዚህን መሣሪያዎች ማግኘት የምንችል ከሆነ ከቤተሰብ ጥናት ጋር በተያያዘ በጥሩ ሁኔታ እንዴት ልንጠቀምባቸው እንችላለን?
11 በቤተሰብ ጥናታችሁ ወቅት መጠበቂያ ግንብ ልታጠኑ የምትችሉ ቢሆንም በተለያዩ ቋንቋዎች ሌሎች የማጥኛ መሣሪያዎች እንዳሉም አትዘንጉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኝ አንድ መግለጫ መሠረታዊ አመጣጥ ወይም ሌላ ማብራሪያ ማግኘት ቢያስፈልጋችሁ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ መልሱን ሊሰጣችሁ ይችላል። ለሌሎች ጥያቄዎችም ከመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ በመመልከት ወይም ምርምር ለማድረግ በማኅበሩ በተዘጋጀው የኮምፒዩተር ፕሮግራም በመጠቀም መልስ ማግኘት ይቻላል። በቋንቋችሁ የሚገኙ ከሆነ በእነዚህ መሣሪያዎች እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ማወቁ ለቤተሰብ ጥናታችሁ የላቀ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። የትንንሽ ልጆችን ፍላጎት ለመቀስቀስ ስትሉ ማኅበሩ ካዘጋጃቸው ትምህርት ሰጭ የቪዲዮ ፊልሞች መካከል ከአንዱ የተወሰነውን ክፍል ለማየት ወይም በቴፕ ክር ተቀርጸው ከሚገኙት ድራማዎች መካከል የአንዱን ክፍል ለመስማትና ከዚያም ውይይት ለማድረግ የተወሰነውን የጥናታችሁን ጊዜ ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ። እነዚህን የማጥኛ መሣሪያዎች ጥሩ አድርጎ መጠቀም የቤተሰብ ጥናታችሁን አስደሳች ያደርገዋል እንዲሁም መላው ቤተሰብ ሊጠቀም ይችላል።
ለቤተሰባችሁ እንደሚያስፈልግ ተጠቀሙበት
12. በአፋጣኝ የቤተሰቡን ትኩረት የሚሻ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ የቤተሰብ ጥናት እንዴት ያለ ሚና ሊጫወት ይችላል?
12 ቤተሰባችሁ አዘውትሮ የሚያጠናው በሳምንቱ ውስጥ የሚጠናውን የመጠበቂያ ግንብ ትምህርት ሊሆን ይችላል። ሆኖም የቤተሰቡን የልብ ትርታ ለማዳመጥ ሞክሩ። እናትየው ተቀጥራ የማትሠራ ከሆነ ልጆቹ ከትምህርት ቤት በሚመለሱበት ጊዜ በየቀኑ ከልጆቿ ጋር ጊዜ ልታሳልፍ ትችላለች። አንዳንድ ሁኔታዎች ወዲያው ሊፈቱ ይችሉ ይሆናል፤ ሌሎች ደግሞ ተጨማሪ ትኩረት የሚያሻቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ቤተሰቡ በአፋጣኝ የሚያስፈልገው ነገር ካለ ችላ ብላችሁ አትለፉ። (ምሳሌ 27:12) ይህ በትምህርት ቤት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሁኔታዎችም ሊያጠቃልል ይችላል። ተስማሚ የሆነ ጽሑፍ ምረጡና የሚጠናው ምን እንደሆነ አስቀድማችሁ ለቤተሰቡ ንገሩ።
13. ድህነትን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል በቤተሰብ መልክ መወያየቱ ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?
13 በምሳሌ ለማስረዳት ያህል አብዛኛው የምድር ክፍል በድህነት የተጠቃ ነው። ስለዚህ በብዙ ቦታዎች ድህነትን እንዴት ተቋቁሞ መኖር እንደሚቻል መወያየቱ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። የቤተሰብ ጥናቱ በተጨባጭ ሁኔታዎችና በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ እንዲያነጣጥር ቢደረግ ቤተሰቡ ይጠቀም ይሆን?—ምሳሌ 21:5፤ መክብብ 9:11፤ ዕብራውያን 13:5, 6, 18
14. ይሖዋ ስለ ዓመፅ፣ ጦርነትና ክርስቲያናዊ ገለልተኝነት ያለውን አመለካከት በቤተሰብ መልክ አንድ ላይ ሆኖ መወያየቱን አስፈላጊ እንዲሆን ሊያደርጉት የሚችሉት የትኞቹ ሁኔታዎች ናቸው?
14 ውይይት ማድረግ የሚጠይቀው ሌላው ርዕሰ ጉዳይ ደግሞ ዓመፅ ነው። ሁላችንም የይሖዋ አመለካከት በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ እንዲሰርጽ ማድረግ ይኖርብናል። (ዘፍጥረት 6:13፤ መዝሙር 11:5) በቤተሰብ ጥናት ላይ ይህን ርዕስ አንስቶ መወያየቱ በትምህርት ቤት የሚገኙ ጉልበተኞችን በሚመለከት ምን ማድረግ እንደሚቻል፣ ካራቴ መማር አስፈላጊ ስለመሆን አለመሆኑ እንዲሁም ተስማሚ የሆነ መዝናኛ እንዴት መምረጥ እንደሚቻል መወያየት የሚያስችል መድረክ ይከፍታል። ወታደራዊ ግጭቶች ተስፋፍተዋል፤ በሁሉም አገሮች ለማለት ይቻላል የእርስ በርስ ጦርነት፣ የፖለቲካ ወይም የጎሳ ግጭት ወይም ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጥቃት አለ። በዚህም የተነሳ ቤተሰባችሁ እርስ በርሳቸው በሚጋጩ ቡድኖች ተከብቦ ክርስቲያናዊ ጠባይ ማሳየትን በሚመለከት ውይይት ማድረግ ያስፈልገው ይሆናል።—ኢሳይያስ 2:2-4፤ ዮሐንስ 17:16
15. ፆታንና ጋብቻን በሚመለከት ለልጆች መመሪያ መሰጠት የሚኖርበት እንዴት ነው?
15 ልጆች እያደጉ ሲሄዱ እንደየዕድሜያቸው ፆታንና ጋብቻን የሚመለከት ትምህርት ማግኘት ይኖርባቸዋል። በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ አብዛኞቹ ወላጆች ፆታን በሚመለከት ከልጆቻቸው ጋር ፈጽሞ ውይይት አያደርጉም። ስለ ፆታ በቂ እውቀት የሌላቸው ልጆች ሌሎች ወጣቶች የተጣመመ አመለካከት እንዲይዙ ሊያደርጓቸውና በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ችግር ላይ ሊወድቁ ይችላሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ቀጥተኛ ሆኖም ማራኪ ምክር የሚሰጠውን ይሖዋን መምሰሉ የተሻለ አይሆንም? ልጆች አምላካዊ ምክር ማግኘታቸው ለራሳቸው አክብሮት እንዲኖራቸውና ተቃራኒ ፆታ ያላቸውን በአክብሮት እንዲይዙ ይረዳቸዋል። (ምሳሌ 5:18-20፤ ቆላስይስ 3:5፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3-8) እነዚህን ጉዳዮች አንስተህ ከልጆችህ ጋር ተወያይተህ የነበረ ቢሆንም እንኳ እንደገና ለመወያየት ፈጽሞ አታመንታ። አዳዲስ ሁኔታዎች ሲከሰቱ በድጋሚ ውይይት ማድረጉ የግድ አስፈላጊ ይሆናል።
16. (ሀ) የተለያዩ ቤተሰቦች የቤተሰብ ጥናታቸውን የሚያደርጉት መቼ መቼ ነው? (ለ) ቋሚ የቤተሰብ ጥናት ለማድረግ መሰናክሎችን ያሸነፋችሁት እንዴት ነው?
16 የቤተሰብ ጥናት መቼ መቼ ሊደረግ ይችላል? በርካታ ቤተሰቦች በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን የቤቴል ቤተሰቦች ምሳሌ በመኮረጅ የቤተሰብ ጥናታቸውን ሰኞ ምሽት ላይ ለማድረግ ፕሮግራም አውጥተዋል። ለሌሎች ደግሞ ይህ ሰዓት አያመቻቸውም። ዘጠኝ ልጆችን ጨምሮ 11 አባላት ያሉት በአርጀንቲና የሚገኝ አንድ ቤተሰብ የቤተሰብ ጥናታቸውን ለማድረግ ጠዋት ጠዋት ሁልጊዜ በአሥራ አንድ ሰዓት ከመኝታ ይነሳሉ። የሥራ ሰዓታቸው የተለያየ በመሆኑ ጥናታቸውን በሌላ ጊዜ ማድረግ አልቻሉም። ሁኔታው ቀላል ባይሆንም የቤተሰብ ጥናትን አስፈላጊነት በልጆቹ አእምሮና ልብ ውስጥ በጥልቅ ተክሏል። በፊሊፒንስ የሚኖር አንድ ሽማግሌ ሦስት ልጆቹ ገና ልጅ ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ ከእነርሱና ከባለቤቱ ጋር ያልተቋረጠ የቤተሰብ ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል። እያንዳንዱ ልጅ እውነትን የራሱ ማድረግ ይችል ዘንድ በሳምንቱ መካከል ወላጆቹ ከእያንዳንዱ ልጅ ጋር የግል ጥናት ያደርጉ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ምሥክር ያልሆነ ባል ያላት አንዲት እህት ጠዋት ጠዋት ከልጆቿ ጋር ትምህርት ቤት የሚያደርሳቸው አውቶቡስ የሚጠብቁበት ቦታ ድረስ ትሄዳለች። አውቶቡሱን እየጠበቁ ከሁኔታው ጋር የሚስማማ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ በማንበብና በመወያየት አሥር ደቂቃ ያሳልፋሉ። ከዚያም እናትየው ልጆቹ አውቶቡሱ ላይ ከመሳፈራቸው በፊት አጭር ጸሎት ታቀርባለች። በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ የምትኖርና እርሷንም ሆነ ልጆቿን ጥሏቸው የሄደ የማያምን ባል የነበራት አንዲት እህት ደግሞ ከነበራት አነስተኛ የትምህርት ደረጃ የተነሣ በጥናት ረገድ ከፍተኛ ችግር ይገጥማት ነበር። ትልቁ ወንድ ልጅዋ በየሳምንቱ ወደ ቤተሰቡ በመምጣት ለእናቱና ለታናናሽ ወንድሞቹ የቤተሰብ ጥናት በመምራት ይረዳት ጀመር። እናትዬዋ በትጋት በመዘጋጀት ጥሩ ምሳሌ ሆነች። በእናንተ ቤትስ ውስጥ ዘወትር የቤተሰብ ጥናት እንዳታደርጉ እንቅፋት የሚሆኑ ሁኔታዎች አሉ? ከሆነ ተስፋ አትቁረጡ። የማይቋረጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማካሄድ በምታደርጉት ጥረት የይሖዋን በረከት ለማግኘት ከልብ ጣሩ።—ማርቆስ 11:23, 24
መንፈሰ ጠንካራ ከመሆን የሚገኙ በረከቶች
17. (ሀ) ቋሚ የቤተሰብ ጥናት ለማድረግ ምን ነገር አስፈላጊ ነው? (ለ) ዘወትር ስለ ይሖዋ መንገዶች በቤተሰብ ደረጃ መመሪያ ማግኘት ያለውን ዋጋማነት የሚያሳየው የትኛው ተሞክሮ ነው?
17 አስቀድሞ እቅድ ማውጣትና መንፈሰ ጠንካራ መሆን አስፈላጊ ነው። ሆኖም ዘወትር ከሚደረግ የቤተሰብ ጥናት የሚገኘው ጥቅም ቢደከምለትም የሚያስቆጭ አይሆንም። (ምሳሌ 22:6፤ 3 ዮሐንስ 4) በጀርመን የሚኖሩት ፍራንዝ እና ሂልዳ የሚያሳድጓቸው 11 ልጆች ነበሯቸው። ከብዙ ዓመታት በኋላ ማግዳሌና የተባለችው ሴት ልጃቸው እንዲህ ብላለች:- “እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ትልቅ ነገር የማየው መንፈሳዊ መመሪያ ሳናገኝ የምናሳልፈው አንድም ቀን አለመኖሩን ነው።” በአዶልፍ ሂትለር ግዛት ዘመን የብሔረተኝነት ስሜት አይሎ በነበረበት ወቅት የማግዳሌና አባት ቤተሰቡን ይመጣል ብሎ ለጠበቀው ፈተና ለማዘጋጀት በመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቀም ነበር። ከጊዜ በኋላ በዕድሜ ትንንሽ የሆኑት የቤተሰቡ አባላት ተያዙና ወደ አንድ የጠባይ ማረሚያ ተከተቱ። ሌሎቹም የቤተሰቡ አባላት ተያዙና ወደ ማጎሪያ ካምፕ ተወሰዱ። አንዳንዶቹ ተገደሉ። ከፍተኛ ስደት በነበረባቸው ጊዜያት ብቻ ሳይሆን ከስደቱ በኋላ በነበሩት ጊዜያትም ሁሉም ጠንካራ እምነት አሳይተዋል።
18. ነጠላ ወላጆች ያደረጉት ጥረት መልሶ የካሳቸው እንዴት ነው?
18 በተመሳሳይም በርካታ ነጠላ ወላጆችና እምነታቸውን የማይጋሩ የትዳር ጓደኛ ያላቸው ወላጆች ለልጆቻቸው ያልተቋረጠ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ይሰጣሉ። ባሏ የሞተባት በሕንድ የምትኖር አንዲት ነጠላ እናት በሁለት ልጆቿ ልብ ውስጥ የይሖዋን ፍቅር ለመትከል ከፍተኛ ጥረት አደረገች። ሆኖም ወንድ ልጅዋ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር መተባበር ባቆመ ጊዜ ልቧ በሃዘን ተሰበረ። ልጅዋን ታሠለጥን በነበረበት ወቅት አንድ ዓይነት ስህተት ፈጽሜ ይሆናል በማለት ይቅር እንዲላት ይሖዋን ተማጸነችው። ሆኖም ልጅዋ የተማረውን ነገር ፈጽሞ አልረሳም። ከአሥር ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ተመልሶ፣ ጥሩ መንፈሳዊ እድገት በማድረግ የጉባኤ ሽማግሌ ሆነ። አሁን እርሱና ባለቤቱ የሙሉ ጊዜ አቅኚ ሆነው ያገለግላሉ። በቤተሰባቸው ክልል ውስጥ ያልተቋረጠ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ እንዲሰጡ ከይሖዋና ከድርጅቱ የሚያገኙትን ምክር ከልባቸው የተቀበሉ ወላጆች ምንኛ አመስጋኞች ናቸው! እናንተስ በቤታችሁ ውስጥ ይህንን ምክር ተግባራዊ እያደረጋችሁ ነው?
ልታብራራ ትችላለህ?
◻ ቋሚ የቤተሰብ ጥናት ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ በእያንዳንዱ የቤተሰብ ጥናት ወቅት ግባችን ምን መሆን ይኖርበታል?
◻ ለማስተማሪያ የሚያገለግሉ ምን መሣሪያዎች አሉልን?
◻ ጥናቱ ለቤተሰቡ እንደሚያስፈልግ ሆኖ ሊቀርብ የሚችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ግልጽ የሆነ ዓላማ በመያዝ የቤተሰብ ጥናት መምራት ጥናቱን ለማጎልበት ይረዳል