የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 7/1 ገጽ 28-29
  • መለኮታዊው ስም በእስራኤል ተጠራ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መለኮታዊው ስም በእስራኤል ተጠራ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአምላክን ስም ማወቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
    ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም
  • አምላክን በስም ልታውቀው የምትችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2004
  • መለኮታዊው ስም—አስፈላጊነቱና ትርጉሙ
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • የአምላክ ስም
    ንቁ!—2017
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 7/1 ገጽ 28-29

መለኮታዊው ስም በእስራኤል ተጠራ

ባሕላዊው የአይሁድ እምነት፣ ተከታዮቹ ይሖዋ የሚለውን መለኮታዊ ስም እንዳይጠሩ ለዘመናት አጥብቆ ሲከለክል ቆይቷል። እንደ ሚሽና አገላለጽ ከሆነ የአምላክን ስም የሚጠራ ሁሉ “ከሚመጣው ዓለም ዕድል ፈንታ አይኖረውም።”​—⁠ሳን​ሄድሪን 10:​1a

ጥር 30, 1995 ቀን የቀድሞው የሴፋርዲክ አለቃና የእስራኤል ዋና ረቢ የሆኑት ሰው ሆን ብለው መለኮታዊውን ስም ተጠቅመዋል። ይህንን ያደረጉት አምላክ ነገሮችን እንዲያስተካክል በሚቀርበው የካባሉ የቲኩን የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ነበር። በአምላኪዎቹ እምነት መሠረት ይህ ጸሎት በክፉ ኃይሎች ለሚታወከው አጽናፈ ዓለም ስምምነትን ይሰጥ ዘንድ አምላክን ለመለማመን የሚቀርብ ነው። ዬዲኦዝ አሃሮኖዝ የተባለው ጋዜጣ የየካቲት 6, 1995 እትም እንዲህ ብሏል:- “ይህ ለሕዝብ ይፋ በማይሆን ልዩ ቡክሌት ላይ ብቻ የሚታተምና አስገራሚ ኃይል ያለው ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው።” በዚህ ጸሎት ውስጥ የአምላክ ስም መግባቱ ለቀረበው ልመና ልዩ ኃይል ይጨምርለታል ተብሎም ይታሰባል።

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋ የሚለውን መለኮታዊ ስም እንዲጠቀሙ የሚያዝዝ መሆኑ ልብ ልንለው የሚገባ ነገር ነው። (ዘጸአት 3:​15፤ ምሳሌ 18:​10፤ ኢሳይያስ 12:​4፤ ሶፎንያስ 3:​9) በመጽሐፍ ቅዱሱ የመጀመሪያ የዕብራይስጥ ጽሑፍ ውስጥ ይህ ስም 7,000 ጊዜ ገደማ ተጠቅሶ ይገኛል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ስሙን አላግባብ መጠቀም እንደማይኖርብንም ያስጠነቅቃል። ከአሥሩ ትእዛዛት ሦስተኛው እንዲህ የሚል ነው:- “የአምላክህን የእግዚአብሔር ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና።” (ዘጸአት 20:​7) የአምላክን ስም በከንቱ መጥራት የሚባለው ምን ሊሆን ይችላል? በአይሁዳውያን የጽሑፍ ማኅበር የቀረበ አንድ ሐተታ እንደገለጸው “በከንቱ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “በሆነው ባልሆነው” ማንሳት ማለት ብቻ ሳይሆን “አላስፈላጊ በረከቶችን መድገም” የሚልም ትርጉም ሊኖረው ይችላል።

ታዲያ አምላክ ነገሮችን እንዲያስተካክል የሚቀርበውን የካባል የቲኩን ጸሎት እንዴት ልንመለከተው ይገባል? ምንጩስ ምንድን ነው? በ12ኛውና በ13ኛው መቶ ዘመን ካባላ በመባል የሚታወቅ ምሥጢራዊ የአይሁድ እምነት ዘርፍ መስፋፋት ጀመረ። በ16ኛው መቶ ዘመን ይስሐቅ ሉሪያ የተባለ ረቢ ‘ቲይኩኒም’ የካባል ሃይማኖታዊ ሥርዓት ክፍል እንዲሆን አደረገ። የአምላክን ስም ምትሐታዊ ኃይል እንዳለው ገድ በመጠቀም የካባሊስት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ክፍል እንዲሆን አደረጉ። ይህ የአምላክን ስም በትክክል መጠቀም እንደሆነ ይሰማሃልን?​—⁠ዘዳግም 18:​10-12

ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ ምንም ይሁን ምን የአምላክ ስም እስራኤል ውስጥ በአደባባይ መጠራቱ እንግዳ ነገር እንደሆነ ትስማማለህ። ይሁንና አምላክ ራሱ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናግሯል:- “በዚያም ቀን እንዲህ ትላላችሁ:- እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ ስሙንም ጥሩ፤ በአሕዛብም መካከል ሥራውን አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ያለ እንደሆነ ተናገሩ። ታላቅ ሥራ ሠርቶአልና ለእግዚአብሔር ተቀኙ፤ ይህንም በምድር ሁሉ ላይ አስ​ታውቁ።”​—⁠ኢሳይያስ 12:4, 5

ደስ የሚለው ነገር ግን በዓለም ዙሪያ ከ230 በሚበልጡ አገሮች እንደሚደረገው በእስራኤል ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ጎረቤቶቻቸው ስለ ይሖዋ ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ በመርዳት ላይ ናቸው። ብዙ ተጨማሪ ሰዎች “በእኔ [በይሖዋ] ተማምኗልና አስጥለዋለሁ፤ ስሜንም አውቋልና እጋርደዋለሁ” የሚሉትን የመዝሙር 91:​14 ቃላት ይገነዘባሉ የሚል ተስፋ አላቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ሚሽና በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ የሰፈረውን ሕግ የተሟላ ለማድረግ የተጨመሩ አስተያየቶች ስብስብ ሲሆን ታናይም (አስተማሪዎች) በሚባሉት ረቢዎች ማብራሪያ ላይ የተመሠረተ መጽሐፍ ነው። በጽሑፍ የሰፈረው በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ ማብቂያና በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ መጀመሪያ ላይ ነው።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዚህ በኔጌብ የይሖዋ አገልጋዮች ስሙንና ቃሉን ለሰዎች እያወጁ ነው

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መለኮታዊውን ስም የያዘ ፖስተር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ