የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 7/15 ገጽ 26-28
  • በናሚቢያ ሕያዋን የከበሩ ድንጋዮች አሉ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በናሚቢያ ሕያዋን የከበሩ ድንጋዮች አሉ!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • መንፈሳዊ ማዕድን የማውጣት ሥራ ተጀመረ
  • የሙሉ ጊዜ ሠራተኞች መጡ
  • የከበሩ ድንጋዮችን መቦረሽ
  • መንፈሳዊ ማዕድን ቆፋሪዎች ያስፈልጋሉ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 7/15 ገጽ 26-28

በናሚቢያ ሕያዋን የከበሩ ድንጋዮች አሉ!

ናሚቢያ በደቡብ ምዕራብ አፍሪካ የባሕር ዳርቻ ላይ ወደ 1,500 ኪሎ ሜትር ገደማ ርዝመት ያለው ቦታ ትይዛለች። የአገሪቱ የባሕር ዳርቻ ባጠቃላይ በአሸዋ ቁልሎች፣ ድንጋያማ በሆኑ ኮረብታዎችና ጠጠር በተላበሱ ሰፋፊ ሜዳዎች የተሸፈነ ነው። በናሚቢያ ጠጠራማ የባሕር ዳርቻዎች ከሚገኙ ድንጋዮች ጋር የተለያዩ ቀለማት ያሏቸው የከበሩ ድንጋዮች ይገኛሉ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ አልማዝ ጭምር ይገኛል። ይሁን እንጂ አገሪቱ ከእነዚህ ድንጋዮች ይበልጥ እጅግ የከበረ ነገር አላት። ናሚቢያ ከብዙ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጣ ሕዝብ ያቀፈ ሕያው የከበሩ ድንጋዮች አሏት።

ቀደምት የሆኑት የናሚቢያ ነዋሪዎች የተለያዩ ቋንቋዎችን ያቀፈ ኮይሳን የሚባል ቋንቋ ይናገሩ የነበረ ሲሆን ቋንቋቸው ሲናገሩ በሚያሰሙት ቀጭ ቀጭ የሚል ድምፅ ተለይቶ ይታወቃል። ዛሬ ከሚገኙት የኮይሳን ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው ዳማራዎች፣ አጭር ቁመናና ነጣ ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸው ናማዎች እንዲሁም አዳኝ የሆኑት የታወቁት የዱር ሰዎች (Bushman) ይገኙበታል። ከቅርብ ምዕተ ዓመታት ወዲህ በርካታ የጥቁር ዝርያ ያላቸው ጎሳዎች ወደ ናሚቢያ መጥተዋል። እነዚህ በሦስት ዋና ዋና የብሔረሰብ ቡድኖች ይከፈላሉ:- እነርሱም ኦቫምቦ (በናሚቢያ የሚገኘው ትልቁ ጎሳ ነው)፣ ሂሬሮ እና ካቫንጎ ናቸው። አውሮፓውያን ወደ ናሚቢያ መጥተው መስፈር የጀመሩት ከ19ኛው መቶ ዓመት አንስቶ ነው። አሸዋማ በሆኑት በረሐዎች አልማዝ መኖሩ ከታወቀ በኋላ ተጨማሪ የውጭ ዜጎች መጥተዋል።

የናሚቢያ ነዋሪዎች አምላክ ልጁን በመስጠት የዘላለም ሕይወት የሚያስገኘውን መንገድ የከፈተለት የሰው ዘር ዓለም ክፍል ስለሆኑ ክቡር ናቸው። (ዮሐንስ 3:​16) እስካሁን ድረስ ከብዙ ጎሳዎች የተውጣጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ናሚቢያውያን መዳን ለሚያስገኘው መልእክት አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ወደ ይሖዋ አምልኮ ቤት በመሰብሰብ ላይ ካሉ ‘ከአሕዛብ ሁሉ ከተመረጠው ዕቃ’ መካከል የሚገኙ ስለሆኑ ሕያው በሆኑ የከበሩ ድንጋዮች ሊመሰሉ ይችላሉ።​—⁠ሐጌ 2:​7

መንፈሳዊ ማዕድን የማውጣት ሥራ ተጀመረ

በናሚቢያ የሚገኙትን መንፈሳዊ የከበሩ ድንጋዮች ማውጣት የተጀመረው በ1928 ነበር። በዚያ ዓመት በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ በመላ አገሪቱ ተበታትነው ለሚገኙ ሕዝቦች 50,000 የሚያክሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በፖስታ ልኮ ነበር። በሚቀጥለው ዓመት ከደቡብ አፍሪካ የመጣች ሌኒ ቴሮን የምትባል አንዲት ቅቡዕ እህት ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች ተከታትላ መርዳት ጀመረች። በአራት ወር ውስጥ ከ6,000 የሚበልጡ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ በአፍሪካንስ፣ በእንግሊዝኛና በጀርመንኛ የተዘጋጁ ጽሑፎችን እያበረከተች ብቻዋን ያን ሰፊ አገር አካለለች። ይህ ሁሉ ጥረት እንዲሁ ከንቱ ሆኖ አልቀረም።

ለምሳሌ ያህል በርንሃርት ባዴ የተባለውን ጀርመናዊ ማዕድን ቆፋሪ እንመልከት። በ1929 አንድ ገበሬ ለዚህ ሰው እንቁላል ያመጣለት ነበር። ይህ ደንበኛው እንቁላሎቹን የሚያመጣለት እያንዳንዱን እንቁላል ከመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፍ በተገነጠሉ ገጾች ጠቅልሎ ነበር። በርንሃርት ማን እንደጻፋቸው በመገረም እያንዳንዱን ገጽ በጉጉት ያነብብ ነበር። ንባቡን ቀጥሎ የመጨረሻው ገጽ ላይ ሲደርስ በጀርመን የሚገኘውን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር አድራሻ አገኘ። በርንሃርት ተጨማሪ ጽሑፍ እንዲላክለት የጠየቀ ሲሆን እውነትን በመቀበል የመጀመሪያው ናሚቢያዊ ለመሆን በቅቷል።

የሙሉ ጊዜ ሠራተኞች መጡ

በ1950 በጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ ማኀበር የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የሠለጠኑ አራት ሚስዮናውያን ወደ ናሚቢያ መጡ። በ1953 የሚስዮናውያኑ ቁጥር ስምንት ደረሰ። ከእነርሱም መካከል እስካሁን በዚያ በታማኝነት እያገለገሉ ያሉት አውስትራሊያኑ ባልና ሚስት ዲክ እና ኮራሌ ዋልድረን ይገኙበታል። ከደቡብ አፍሪካና ከሌሎች አገሮች የመጡ ሌሎች በርካታ የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎችም የናሚቢያን መንፈሳዊ የከበሩ ድንጋዮች በመፈለጉ ሥራ የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል። ሌሎች ሚስዮናውያን እንዲሁም የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ምሩቃን ወደ ናሚቢያ ተልከዋል።

ናሚቢያ ውስጥ ለመንፈሳዊ እድገት አስተዋጽኦ ያበረከተው ሌላው ነገር በአገሪቱ በሚነገሩት እንደ ሂሬሮ፣ ክዋንጋሊ፣ ክዋንያማ፣ ናማ/ዳማራ እና ንዶንጋ የመሳሰሉ ዓበይት ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች መተርጎማቸውና መታተማቸው ነው። ከ1990 አንስቶ በዋና ከተማው በዊንድሆክ አንድ ምቹ የሆነ የትርጉም ሥራ ቢሮና የሙሉ ጊዜ ፈቃደኛ ሠራተኞች መኖሪያ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በተለያዩ የናሚቢያ ክፍሎች ከባለቤቷ ጋር በሙሉ ጊዜ የስብከቱ ሥራ የተካፈለችው ካረን ዴፒሽ እንዲህ ትላለች:- “በተለይ በቋንቋቸው የተዘጋጀ መጽሐፍ እምብዛም ከሌለ በዚያ ቋንቋ የተዘጋጀ ጽሑፍ ስናበረክትላቸው ብዙዎች በጣም ይገረማሉ።”

የከበሩ ድንጋዮችን መቦረሽ

በናሚቢያ የሚገኙ አንዳንድ የከበሩ ድንጋዮች በጊዜ ብዛት በባሕር ሞገድና በአሸዋ እንቅስቃሴ ሲቦረሹ ኖረዋል። ሆኖም እንዲህ ዓይነቶቹ የተፈጥሮ ሂደቶች ሕያው የከበሩ ድንጋዮች እንደማያስገኙ የታወቀ ነው። አለፍጽምና የወረሱ ሰዎች ‘አሮጌውን ሰው አስወግደው’ ክርስቶስን የሚመስለውን አዲሱን ሰው ለመልበስ ጥረት ይጠይቅባቸዋል። (ኤፌሶን 4:​20-24) ለምሳሌ ያህል ለሞቱ ቅድመ አያቶች የሚሰጥ አክብሮት በአብዛኞቹ የናሚቢያ ጎሳዎች ዘንድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ወግ ነው። ለቅድመ አያቶች የሚቀርብ አምልኮ የማያከናውኑ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ከቤተሰብ አባሎቻቸውና ከጎረቤቶቻቸው ስደት ይደርስባቸዋል። ሰዎች ሙታን ‘አንዳች እንደማያውቁ’ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሲማሩ ፈተና ይደቀንባቸዋል። (መክብብ 9:​5) በምን መንገድ?

የሂሬሮ ተወላጅ የሆነ አንድ ምስክር እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ለእውነት ተገዥ መሆን በጣም ፈታኝ ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፈቃደኛ ብሆንም እንኳ እየተማርኳቸው የነበሩትን ነገሮች በሥራ ለማዋል ጊዜ ወስዶብኛል። በመጀመሪያ ደረጃ ባሕላዊ እምነቶችን አለመከተሌ ጉዳት ያስከትልብኝ እንደሆነና እንዳልሆነ ማረጋገጥ ነበረብኝ። ለምሳሌ ያህል ናሚቢያ ውስጥ መኪና እየነዳሁ ስሄድ መቃብር ላይ ድንጋይ ለማስቀመጥ ከመኪናዬ ሳልወርድ ወይም ለሙታን ሰላምታ ለመስጠት ኮፍያዬን ሳላወልቅ አንዳንድ ቦታዎችን አልፌ እሄዳለሁ። ቀስ በቀስ የሞቱ ቅድመ አያቶቼን ባለማምለኬ ምንም ጉዳት እንደማይደርስብኝ እርግጠኛ ሆንኩ። ይሖዋ ቤተሰቦቼና ሌሎች ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እውነትን እንዲማሩ ለመርዳት ያደረኩትን ጥረት ስለባረከልኝ በጣም ደስተኛ ነኝ!”

መንፈሳዊ ማዕድን ቆፋሪዎች ያስፈልጋሉ

በ1950 ሚስዮናውያኑ ከመምጣታቸው በፊት ናሚቢያ ውስጥ አንድ የምሥራቹ አስፋፊ ብቻ ይገኝ ነበር። የአስፋፊዎቹ ቁጥር ያለማቋረጥ አድጎ 995 ደርሷል። ሆኖም ገና ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ። እንዲያውም አንዳንድ ክልሎች መልእክቱ ደርሷቸዋል ለማለት ያዳግታል። ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በጣም በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ሁኔታህ ይፈቅድልሃል? ከሆነ እባክህ ወደ ናሚቢያ መጥተህ ተጨማሪ በመንፈሳዊ የከበሩ ድንጋዮች በመፈለጉና በማጽዳቱ ሥራ ተባበረን።​—⁠ከሥራ 16:​9 ጋር አወዳድር።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች/ሣጥን]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

አፍሪካ

ናሚቢያ

[ሥዕሎች]

ናሚቢያ ማራኪ የከበሩ ድንጋዮች የሚገኙባት አገር ነች

[ምንጭ]

ካርታዎች:- Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc., አልማዝ:- Courtesy Namdek Diamond Corporation

[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ምሥራቹ በናሚቢያ ለሚገኙ ለሁሉም ጎሳዎች እየተሰበከ ነው

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገል ትችላለህ?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ