መለኮታዊ እንቆቅልሾችና የአምላክ ዓላማ
ሳያውቁት ከቀሩ የሚያሰኝ ድንግርግር፤ ካወቁት በኋላ የማያመራምር ምንድን ነው? እንቆቅልሽ።
ከልክ በላይ ግልጽነት በሚያጠቃው በዚህ ኅብረተሰብ ውስጥ ሰዎች እንቆቅልሽን እንደ ልጆች ጨዋታ መመልከት ይቀናቸዋል። ይሁን እንጂ በጥንት ዘመን እንቆቅልሽ የሰዎች “ጥበብ የሚፈተንበት” ነገር ነበር ሲል ዚ ኢንተርፕሪተርስ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል ይገልጻል።—ከምሳሌ 1:5, 6 [NW] ጋር አወዳድር።
ይሖዋም ፈቃዱን ወይም ዓላማውን ፊት ለፊት ከመናገር ይልቅ ሆነ ብሎ ምሳሌዎችንና ‘ሰወር ያሉ አባባሎችን’ ወይም የሚያመራምሩ እንቆቅልሾችን በመጠቀም ትንቢታዊ መልእክቱን ዘወር ባለ መንገድ የገለጸባቸው ጊዜያት አሉ። (መዝሙር 78:2 ኪንግ ጀምስ ቨርሽን፤ ዘኁልቁ 12:8 ዚ ኢምፋሳይዝድ ባይብል) እንዲያውም እንቆቅልሽ የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት 17 ጊዜ ብቻ ቢሆንም ቅዱሳን ጽሑፎች ቃል በቃል በእንቆቅልሾችና በምሳሌዎች የተሞሉ ናቸው ለማለት ይቻላል።
ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንቆቅልሾች አሉ
ንጉሥ ሰሎሞን የሚቀርቡለትን በጣም ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎችና እንቆቅልሾች ሳይቀር የመፍታት ችሎታ እንደነበረው ይነገርለታል። (1 ነገሥት 10:1 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ይህን ማድረግ የቻለው አምላክ በሰጠው ጥበብ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ሰሎሞን ከጢሮሱ ንጉሥ ከኪራም ጋር ባደረገው የእንቆቅልሽ ውድድር የተሸነፈበት ጊዜ አለ የሚለው የጥንቶቹ ታሪክ ጸሐፊዎች ዘገባ እውነት ከሆነ ይህ ነገር የተፈጸመው ሰሎሞን ክህደት በመፈጸሙ ምክንያት የይሖዋን መንፈስ ካጣ በኋላ መሆን አለበት። መስፍኑ ሳምሶንም እንዲሁ እንቆቅልሽ ይወድድ ነበር። ከመንፈስ ቅዱስ ባገኘው ኃይል ተጠቅሞ በእንቆቅልሽ መዘዝ የአምላክን ጠላቶች የሚያርበደብድ እርምጃ የወሰደበትም ጊዜ ነበር።—መሳፍንት 14:12-19
ይሁንና ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ እንቆቅልሾች ከይሖዋ ዓላማ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል በዘፍጥረት 3:15 ላይ ያለውን ተመልከት። ለመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ መሠረት የሆነው ይህ ትንቢት ራሱ ሰወር ያለ ይዘት ያለው ‘ቅዱስ ምሥጢር’ ነው። (ሮሜ 16:25, 26) ሐዋርያው ጳውሎስ መለኮታዊ ራእይዎችን ከመቀበሉም ሌላ የአምላክን ዓላማ አንዳንድ ዘርፎች “በድንግዝግዝ” ወይም ቃል በቃል ከተወሰደ ደግሞ “በተሸፋፈነ መንገድ” ተመልክቷል። (1 ቆሮንቶስ 13:12፤ 2 ቆሮንቶስ 12:1-4) በራእይ 13:18 ላይ ድንገት በተጠቀሰውና ምንም ማብራሪያ ባልተሰጠው “ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት” በሚለው የአውሬው ምሥጢራዊ ቁጥር ዙሪያ የሚሰነዘሩትን መቋጫ የሌላቸው ግምታዊ ሐሳቦች በሚመለከትስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህን መለኮታዊ እንቆቅልሾች ሊፈታ የሚችለው ማን ነው? ደግሞስ ዓላማቸው ምንድን ነው?
ቅዱስ ምሥጢሮችን መፍታት
አብዛኞቻችን ከአምስቱ የስሜት ሕዋሶቻችን መካከል የላቀ ግምት የምንሰጠው ለማየት ችሎታችን ነው። ይሁን እንጂ ብርሃን ባይኖር የማየት ችሎታችን ምንም የሚፈይደው ነገር አይኖርም ነበር። የታወርን ያህል ይሆን ነበር። የሰው ልጅ አእምሮም እንዲሁ ነው። የማገናዘብና ምክንያት የማቅረብ አስገራሚ ችሎታ ስላለው ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎችን ለመፍታት ይችላል። ይሁን እንጂ ቅዱስ ምሥጢሮችን ለመፍታት ከዚያ የበለጠ ነገር ያስፈልጋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለቀረቡት እንቆቅልሾች መልስ ነው የሚሏቸውን ሐሳቦች የሚሰነዝሩ ሰዎች ሊኖሩ ቢችሉም የእንቆቅልሾቹ ዓላማ ምን እንደሆነ ሊገልጥልን የሚችለው የብርሃን አምላክና የእንቆቅልሾቹ ምንጭ የሆነው ይሖዋ ብቻ ነው።—1 ዮሐንስ 1:5
የሚያሳዝነው ግን ብዙውን ጊዜ ሰዎች ኩራተኛና በራሳቸው መመራት የሚፈልጉ በመሆናቸው ይሖዋ መልስ እስኪሰጣቸው ድረስ መጠበቅ አይፈልጉም። እውነትን ፍለጋ ሳይሆን በምሥጢራዊነቱ በመማረክ አእምሮአቸውን የሚያረካ እውቀት ለመቅሰም ሲሉ ብቻ ከአምላክ ቃል ውጭ ፍቺዎችን ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል በካባላ ላይ የሰፈረው የአይሁዳውያኑ ምሥጢራዊ ትምህርት የዕብራይስጥ ሆሄያትና ቁጥሮች ከጥንቆላ ጋር ስላላቸው ተዛምዶ ያትታል። በሌላ በኩል ደግሞ በሁለተኛው መቶ ዘመን የነበሩት ግኖስቲኮች የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን በመጠቀም ምሥጢራዊ ትርጉም ያላቸው ነገሮች ለመፍጠር ሞክረዋል።
ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ መማሰን ከመለኮታዊው እውነት ርቀው ወደ አረማዊ የአምልኮ ሥርዓቶችና አጉል እምነቶች እንዲሄዱ መርቷቸዋል። ግኖስቲኮች ‘ዓለም በክፉ ነገር የተሞላ ከሆነማ ፈጣሪው የሆነው ያህዌህም ጥሩ አምላክ ሊሆን አይችልም’ እስከ ማለት ደርሰዋል። ከዚህ የተሻለ መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ አይችሉም ነበርን? የሰው ልጅ ጥበብ እንዴት ከንቱ ነው! ሐዋርያው ጳውሎስ የግኖስቲክ ኑፋቄዎች አዳብረዋቸው የነበሩትን የክህደት ሐሳቦች በመቃወም “ከተጻፈው አትለፍ” ሲል በመልእክቱ አጥብቆ ማስጠንቀቁ ምንም አያስገርምም!—1 ቆሮንቶስ 4:6
‘ሰወር ያሉ አባባሎችን’ ግልጽ ማድረግ
ይሁንና የብርሃን አምላክ ‘ሰወር ያሉ አባባሎችን’ የሚጠቀመው ለምንድን ነው? እንቆቅልሽ ራሱ የሰዎችን ሐሳብና የማገናዘብ ችሎታ የሚፈትን ነገር ነው። ለአንድ ግሩም ምግብ ጣዕም እንደሚጨምር ቅመም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ጣል ጣል ብለው የሚገኙት እንቆቅልሾች የአንባብያንን ፍላጎት ለማነሳሳት ወይም ደግሞ መልእክቱን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ያገለገሉበት ጊዜ አለ። በእነዚህ አጋጣሚዎች ከእንቆቅልሾቹ በኋላ ወዲያውኑ ትርጉማቸው ይገለጻል።—ሕዝቅኤል 17:1-18፤ ማቴዎስ 18:23-35
ይሖዋ ጥበብን ያለምንም አድልዎ በልግስና ይሰጣል። (ያዕቆብ 1:5-8) የምሳሌን መጽሐፍ የወሰድን እንደሆነ አንዳንዶች እንደ እንቆቅልሽ ሊያዩአቸው የሚችሏቸው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ብዙ የሚያመራምሩ አባባሎች የያዘ ነው። እነዚህን አባባሎች መረዳት ጊዜም ማሰላሰልም ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ምን ያህሎቹ ሰዎች ይህንን ጥረት ለማድረግ ፈቃደኛ ይሆናሉ? በእነዚህ ምሳሌዎች ውስጥ የተንጸባረቀውን ጥበብ ማግኘት የሚችሉት ቁፈራ ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው።—ምሳሌ 2:1-5
ኢየሱስም እንዲሁ የአድማጮቹን የልብ ሁኔታ ለመገምገም ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ጎርፈዋል። የሚናገራቸው ታሪኮች ደስ ይሏቸው ነበር። ተዓምራቱንም ወድደዋቸዋል። ይሁንና አኗኗራቸውን ለውጠው እርሱን ለመከተል ፈቃደኛ የነበሩት ምን ያህሎቹ ናቸው? የኢየሱስን ትምህርቶች ለመረዳት በተደጋጋሚ ይጠይቁ የነበሩትና እርሱን ለመከተል ራሳቸውን የካዱት የኢየሱስ ተከታዮች ሁኔታ ከዚህ ምንኛ የተለየ ነበር!—ማቴዎስ 13:10-23, 34, 35፤ 16:24፤ ዮሐንስ 16:25, 29
ብርሃኑን በተስፋ መጠበቅ
አንድ ጽሑፍ “ለእንቆቅልሽ ጉጉት ማሳደር ለምሁራዊ ሥራዎች ንቁ መሆንን የሚያሳይ ይመስላል” ብሏል። ዛሬ ለአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ‘ብርሃን በበራበት’ ጊዜ መኖራችን ታላቅ መብት ነው። (መዝሙር 97:11፤ ዳንኤል 12:4, 9) አምላክ በቀጠረው ጊዜ ዓላማውን እስኪገልጽልን ድረስ በትዕግሥት እንጠብቃለን? ከሁሉ በላይ ደግሞ ከተገለጠው የአምላክ ዓላማ ጋር እንዴት ራሳችንን ማስማማት እንዳለብን ከተረዳን በኋላ በሕይወታችን ለውጥ ለማድረግ ፈጣኖች ነን? (መዝሙር 1:1-3፤ ያዕቆብ 1:22-25) እንደዚህ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ ጥረታችንን ስለሚባርክልን መነፅር ዓይናችን አጥርቶ እንዲያይ እንደሚረዳን ሁሉ መንፈስ ቅዱስም የመለኮታዊውን ዓላማ ውብ ንድፍ በዓይነ ሕሊናችን ቁልጭ ብሎ እንዲታየን ያደርጋል። ይህም መንፈሳዊ ዕይታችንን ያሻሽልልናል።—1 ቆሮንቶስ 2:7, 9, 10
እርግጥ ቅዱስ ጽሑፋዊ እንቆቅልሾች ይሖዋ ‘ምሥጢርን የሚገልጥ’ አምላክ መሆኑን ጎላ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው። (ዳንኤል 2:28, 29) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ልብን የሚመረምር አምላክ ነው። (1 ዜና መዋዕል 28:9) የመለኮታዊው እውነት ብርሃን የሚገለጠው ደረጃ በደረጃ መሆኑን ማወቃችን ሊያስገርመን አይገባም። (ምሳሌ 4:18፤ ሮሜ 16:25, 26) መጨረሻቸው ከንቱ በሆኑ ምሥጢራዊ ትምህርቶች ወይም ጥልቀት በሌለው የሰው ልጅ ጥበብ በመጠቀም ስለ አምላክ ጥልቅ ነገሮች ለማወቅ ከመሞከር ይልቅ ‘ሰወር ባሉ አባባሎቹ’ ላይ የእውነት ብርሃኑን በማብራት እርሱ በወሰነው ጊዜ ድንቅ ዓላማውን ለታመኑ አገልጋዮቹ እንደሚያሳውቅ ሙሉ ትምክህት በማሳደር ይሖዋ አምላክን በተስፋ እንጠባበቅ።—አሞጽ 3:7፤ ማቴዎስ 24:25-27
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Biblia Hebraica Stuttgartensia, Deutsche Bibelgesellschaft Stuttgart