“በየደብሮቻችን ቅስቀሳ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
”በፈረንሳይ የሚታተመው ፋሚይ ክሬቲየን (የክርስቲያን ቤተሰብ) የተባለው የካቶሊክ መጽሔት ከላይ ያለውን በማለት ጥያቄ ቢያቀርብም ጉዳዬ ብሎ የሰማው ማንም አልነበረም። እንዲያውም የብሪታንያው ካርዲናል ሃም የቤተ ክርስቲያኒቱን ደብሮች “የእንቅልፍ ድባብ ያጠላባቸው” ሲሉ ገልጸዋቸዋል። የተኙትን ለመቀስቀስ በየደብሩ የሰበካ ጉባኤዎች እንዲደራጁ ሐሳብ ቀርቦ ነበር። አንድ ኢጣሊያዊ ቄስ ይህንን እንቅስቃሴ “አዲስ ዘዴ የተቀየሰለት ቀጥተኛ የወንጌላዊነት ሥራ” በማለት ጠርተውታል። ጳጳሱ እንዲህ ያለውን ጅምር ቢያበረታቱም እምነታቸውን ለሌሎች ማካፈል አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማቸው ግን ሁሉም አይደሉም።
በሚላን የሚኖሩ ፒጂ ፔሪኒ የተባሉ አንድ የደብር አለቃ በቅርቡ በአፍሪካ ጉብኝት አድርገው በነበረበት ወቅት ያገኟት አንዲት መነኩሲት “እንግዲህ እዚህ ከመጣሁ አሁን 40 ዓመት ሆኖኛል። የአፍሪካን ባሕል ላለመበረዝ ስል የኢየሱስን ስም ፈጽሞ ላለመጥራት ያደረኩት ጥረት ሙሉ በሙሉ ተሳክቶልኛል” ብላቸዋለች። የደብር አለቃውም ሲደመድሙ:- “ስለ ኢየሱስ አንናገርም፣ ኢየሱስን ለሌሎች አናካፍልም፣ ወንጌል አንሰብክም!” በሌላው በኩል ደግሞ ስብከት በሕይወታቸው ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ የሚይዝና በመንፈሳዊ ንቁ ሆነው ለመኖር የሚያስችላቸው መንገድ እንደሆነ የሚሰማቸው በርካታ ሰዎች አሉ። ፒጂ ፔሪኒ “በገበያ መካከል እየተዘዋወሩ ስለ ክርስቶስ የሚናገሩ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው የሚሄዱ ሁለት ሰዎች ብትመለከቱ ወዲያው እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው ብላችሁ እንደምታስቡ የታወቀ ነው!” በማለት ሳይሸሽጉ ተናግረዋል።
በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስለ አምላክ ቃል መነጋገር ያስደስታቸዋል። አንተም በምትኖርበት መንደር ውስጥ ምሥክሮቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት እንደሚያደርጉ ጥርጥር የለውም። እነዚህ ቀናተኛ ክርስቲያኖች በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ እምነታቸውን ለሌሎች ለማካፈል እርስ በርስ ይበረታታሉ። ስብሰባ የሚያደርጉባቸው ቦታዎች (የመንግሥት አዳራሾች ተብለው ይጠራሉ) ሞቅ ያለና የወዳጃዊነት መንፈስ የሚንጸባረቅባቸው ቦታዎች ናቸው። ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች ባዘጋጁት በአንዱ ስብሰባ ላይ ተገኝተህ መንፈሳዊ ድብታን እንዴት መዋጋት እንደሚቻል ለምን አትማርም?