አምላክን የምታገለግለው ለምንድን ነው?
በአንድ ወቅት አንድ አምላክን የሚፈራ ንጉሥ ለልጁ የሚከተለውን ምክር ሰጥቶት ነበር:- “የአባትህን አምላክ እወቅ። በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም [“በደስተኛ ነፍስ፣” NW ] አምልከው።” (1 ዜና መዋዕል 28: 9) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ይሖዋ አገልጋዮቹ በአመስጋኝነት ስሜትና በአድናቆት ተገፋፍተው እንዲያገለግሉት ይፈልጋል።
የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን የመጽሐፍ ቅዱስን ተስፋዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ስንሰማ ልባችን በአመስጋኝነት ስሜት ተሞልቶ እንደነበር አይካድም። በየቀኑ ስለ አምላክ ዓላማዎች አንድ አዲስ ነገር እንማር ነበር። ስለ ይሖዋ ይበልጥ በተማርን ቁጥር እርሱን “በሙሉ ልብና በደስተኛ ነፍስ” ለማገልገል ያለን ፍላጎት እያደገ መጥቷል።
የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ብዙዎች ይሖዋን በታላቅ ደስታ ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ክርስቲያኖች ጥሩ ጅምር የነበራቸው ቢሆንም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አምላክን እንዲያገለግሉ የሚያንቀሳቅሳቸው ውስጣዊ ግፊት እየጠፋ ሄዷል። አንተስ ተመሳሳይ ሁኔታ ገጥሞሃልን? ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ያጣኸውን ደስታ መልሶ ማግኘት ይቻላል። እንዴት?
ያገኘሃቸውን በረከቶች አስብ
በመጀመሪያ በየቀኑ ከአምላክ በምታገኛቸው በረከቶች ላይ አሰላስል። ስለ ይሖዋ ጥሩ ጥሩ ስጦታዎች አስብ። በሁሉም ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች በቀላሉ ሊያገኟቸው የሚችሉ ባለ ብዙ ዘርፍ የፍጥረት ሥራዎቹ፣ ከእርሱ ያገኘናቸው የሚበሉና የሚጠጡ ነገሮች፣ ያለህ መጠነኛ ጤንነት፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያገኘኸው እውቀትና በዋነኛነት ደግሞ የልጁ ስጦታ ናቸው። የልጁ ሞት አምላክን በንጹህ ህሊና እንድታገለግል መንገድ ጠርጎልሃል። (ዮሐንስ 3:16፤ ያዕቆብ 1:17) ስለ አምላክ ጥሩነት ይበልጥ ባሰላሰልክ መጠን ለእርሱ ያለህ አድናቆት በዚያው መጠን ይጨምራል። ልብህ ይሖዋ ባደረጋቸው ነገሮች በአመስጋኝነት ስሜት ስለሚሞላ እርሱን ለማገልገል ይገፋፋሃል። አንተም እንዲህ በማለት የጻፈው መዝሙራዊ ዓይነት ስሜት እንደገና እንደሚሰማህ ምንም ጥርጥር የለውም:- “አቤቱ አምላኬ፣ ያደረግኸው ተአምራት ብዙ ነው፣ አሳብህንም ምንም የሚመስለው የለም፤ . . . ከቍጥር ሁሉ በዛ።”—መዝሙር 40:5
እነዚህ ቃላት ሕይወቱ ከችግር ነጻ ሆኖ የማያውቀው ዳዊት የጻፋቸው ናቸው። ክፉ የሆነው ንጉሥ ሳኦልና ጠባቂዎቹ እርሱን ለመግደል ያሳድዱት ስለነበር አብዛኛውን የወጣትነት ጊዜውን ያሳለፈው በሽሽት ነበር። (1 ሳሙኤል 23:7, 8, 19-23) በተጨማሪም ዳዊት ሊታገላቸው የሚገቡ የግል ድክመቶችም ነበሩት። ይህንንም በ40ኛው መዝሙር ላይ ገልጾታል:- “ቍጥር የሌላት ክፋት አግኝታኛለችና፤ ኃጢአቶቼ ያዙኝ፣ ማየትም ተስኖኛል፤ ከራሴ ጠጕር ይልቅ በዙ።” (መዝሙር 40:12) አዎን፣ ዳዊት ችግሮች ነበሩበት። ሆኖም ሙሉ በሙሉ በችግሮቹ አልተዋጠም። ይልቁንም ችግሮች እያሉበት እንኳ ይሖዋ እርሱን በሚባርክባቸው መንገዶች ላይ ትኩረት አድርጎ ነበር። በተጨማሪም ከችግሮቹ ይልቅ በረከቶቹ እንደሚያመዝኑ ተገንዝቦ ነበር።
በግል ችግሮችህ ስትዋጥ ወይም ብቁ አይደለሁም የሚል ስሜት ሲሰማህ ልክ እንደ ዳዊት ቆም ብለህ ያገኘኻቸውን በረከቶች መቁጠርህ ጠቃሚ ነው። ሕይወትህን ለይሖዋ እንድትወስን የገፋፋህ እንዲህ ላሉት በረከቶች ያለህ አድናቆት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲህ ያሉት ሐሳቦች ያጣኸውን ደስታ መልሰህ እንድታገኝና አምላክን በአመስጋኝነት በተሞላ ልብ ተገፋፍተህ እንድታገለግለው ሊረዱህ ይችላሉ።
የጉባኤ ስብሰባዎች ሊረዱህ ይችላሉ
በግላችን ስለ ይሖዋ ጥሩነት ከማሰላሰላችን በተጨማሪ ከክርስቲያን ባልንጀሮች ጋር አንድ ላይ መሰብሰብም ያስፈልገናል። አምላክን ከሚወዱና እርሱን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ ካደረጉ ወንዶች፣ ሴቶችና ወጣቶች ጋር መሰብሰብ ያበረታታል። የእነርሱ ምሳሌ በይሖዋ አገልግሎት በሙሉ ነፍስ እንድንካፈል ሊያነሳሳን ይችላል። የእኛ በመንግሥት አዳራሽ መገኘት እነርሱንም ሊያበረታታቸው ይችላል።
እርግጥ ነው፣ ቀኑን ሙሉ ስንሠራ ውለን ደክሞን ወይም በአንድ ችግር ወይም ድክመት ምክንያት ተስፋ ቆርጠን ከነበረ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ለመገኘት ማሰብ ቀላል ላይሆን ይችላል። እንዲህ በመሳሰሉት ጊዜያት በራሳችን ላይ ጥብቅ መሆን ይኖርብን ይሆናል። ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር እንድንሰበሰብ የተሰጠንን ትእዛዝ ለመፈጸም ‘ራሳችንን መጎሰም’ ይኖርብናል።—1 ቆሮንቶስ 9:26, 27፤ ዕብራውያን 10:23-25
ይህን ማድረጉን አስፈላጊ ሆኖ ካገኘነው ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር የለንም ማለት ነው ብለን መደምደም ይኖርብናልን? በፍጹም። ለአምላክ የጠበቀ ፍቅር የነበራቸው የቀድሞዎቹ የጎለመሱ ክርስቲያኖች የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አስፈልጓቸዋል። (ሉቃስ 13:24) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ካሉት ክርስቲያኖች መካከል አንዱ ነበር። ስሜቱን እንዲህ በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፣ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም። የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም።” (ሮሜ 7:18, 19) በተጨማሪም በቆሮንቶስ ለሚገኙት ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏቸዋል:- “ወንጌልን ብሰብክ እንኳ የምመካበት የለኝም፤ ግድ ደርሶብኝ ነውና፤ . . . ይህን በፈቃዴ ባደርገው ደመወዝ አለኝና፤ ያለ ፈቃዴ ግን ባደርገው መጋቢነት በአደራ ተሰጥቶኛል።”—1 ቆሮንቶስ 9:16, 17
ልክ እንደ አብዛኞቻችን ጳውሎስም ትክክለኛውን ነገር እንዳያደርግ እንቅፋት የሆኑበት የኃጢአተኝነት ዝንባሌዎች ነበሩት። ይሁን እንጂ ጳውሎስ እነዚህን ዝንባሌዎች ለመዋጋት ከፍተኛ ጥረት አድርጎ የነበረ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜም ውጊያውን በአሸናፊነት ተወጥቷል። እርግጥ፣ ጳውሎስ ይህንን ሁሉ ያደረገው በራሱ ኃይል አልነበረም። ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” በማለት ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 4:13) ለጳውሎስ ኃይል የሰጠው ይሖዋ አንተም እንዲረዳህ ከጠየቅኸው ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚያስችል ኃይል ይሰጥሃል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ‘ለእምነት ከተጋደልክ’ ይሖዋ ይባርክሃል።—ይሁዳ 3
በዚህ ውጊያ ብቻህን አይደለህም። በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ እነርሱ ራሳቸው ‘ለእምነት በሚያደርጉት ውጊያ’ የጸኑ የጎለመሱ ክርስቲያን ሽማግሌዎች አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው። እርዳታ ለማግኘት ወደ አንድ ሽማግሌ ከቀረብክ አንተን ‘በሚያጽናና ቃል’ ለማነጋገር ይጥራል። (1 ተሰሎንቄ 5:14) ግቡ “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ” መሆን ነው።—ኢሳይያስ 32:2
‘እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ’ አገልጋዮቹም በፍቅር ተገፋፍተው እንዲያገለግሉት ይፈልጋል። (1 ዮሐንስ 4:8) ለአምላክ ያለህ ፍቅር እንደገና መቀጣጠል እንደሚያስፈልገው ከተገነዘብክ ከላይ የተዘረዘሩትን አስፈላጊ እርምጃዎች ውሰድ። እንዲህ በማድረግህ ትደሰታለህ።