“ሁሉም ሰው ሊደሰትበት የሚገባ ነው”
በደቡባዊ ፓስፊክ የምትገኘውና ዘጠኝ ደሴቶችን ያቀፈችው ውቧ ቱቫሉ 10,500 የሚደርስ ሕዝብ አላት። ይሁንና የአምላክ ፈቃድ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ መሆኑን በመገንዘብ በአገሪቱ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች በራሳቸው ቋንቋ የታተሙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የማግኘት ጉጉት ነበራቸው። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ሆኖም በአገሪቱ ቋንቋ የተዘጋጀ መዝገበ ቃላት አለመኖሩ ሁኔታውን አስቸጋሪ አድርጎት ነበር። በ1979 ግን በቱቫሉ ተመድቦ የሚያገለግል አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ሚስዮናዊ ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመወጣት ወሰነ። ሚስዮናዊውና ሚስቱ ከአንድ የአገሩ ተወላጅ የሆነ ቤተሰብ ጋር አብረው በመኖር ቋንቋውን ከተማሩ በኋላ ሚስዮናዊው ቀስ በቀስ የቱቫሉን ቃላት ዝርዝር ከነትርጉማቸው አዘጋጀ። በ1984 ኒው ዮርክ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማሕበር በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ በቱቫሉ ቋንቋ አሳተመ።
የቀድሞው የቱቫሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ቲ ፑዌፑወ ዘላለም መኖር ለተባለው መጽሐፍ ያላቸውን አድናቆት የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፈዋል። እንዲህ ብለዋል:- “ይህ መጽሐፍ ቱቫሉ ካሏት ‘ቅርሶች’ የሚደመር በጣም ወሳኝ የሆነ ተጨማሪ ቅርስ ነው። የዚህን አገር ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት በመገንባት ረገድ በተጫወታችሁት ከፍተኛ ሚና እጅግ ደስ ሊላችሁ ይገባል። ይህ ሥራ ትምህርታዊ ጽሑፎችን ከማተም ጋር በተያያዘ በቱቫሉ የታሪክ መዝገብ ውስጥ እንደሚሰፍር አምናለሁ። . . . ይህ [የሥራ ውጤት] ሁሉም ሰው ሊደሰትበት የሚገባ ነው።”
ተርጓሚው ያሰባሰባቸው ቃላት በ1993 ቱቫሉ—እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት እንዲታተም መንገድ ጠርጓል። ይህ መዝገበ ቃላት በቱቫሉ ቋንቋ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ የቀረበ የመጀመሪያው መዝገበ ቃላት ነው። በቅርቡ ደግሞ የቱቫሉ ብሔራዊ የቋንቋዎች ቦርድ የቋንቋቸውን የመጀመሪያ መዝገበ ቃላት ለማዘጋጀት በዚህ መዝገበ ቃላት ለመጠቀም ፈቃድ ጠይቋል።
ከጥር 1, 1989 ጀምሮ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት በቱቫሉ ቋንቋ እየተዘጋጀ በየወሩ ሲታተም ቆይቷል። ይህንን መጽሔት በሁለተኛ ቋንቋህ የምታነብብ ከሆነ በገጽ 2 ላይ በሚገኘው መጠበቂያ ግንብ የሚታተምባቸው ቋንቋዎች ዝርዝር ውስጥ የአንተ የመጀመሪያ ቋንቋ ይገኝ እንደሆነ ለምን አታይም? መጽሔቱን በራስህ ቋንቋ ማንበብህ ተጨማሪ ደስታ እንደሚያመጣልህ አያጠራጥርም።