የምትመራው በምን ዓይነት መሠረታዊ ሥርዓት ነው?
በመሠረታዊ ሥርዓት የምትመራ ሰው ነህ? ወይስ ግብረገብነትን ጊዜ እንዳለፈበት አድርገህ ነው የምትመለከተው? እንደ እውነቱ ከሆነ፣ እያንዳንዱ ሰው በግል ይጠቅመኛል ብሎ በሚያምንበት አንድ ዓይነት መሠረታዊ ሥርዓት ይመራል። ዘ ኒው ሾርተር ኦክስፎርድ ኢንግሊሽ ዲክሽነሪ እንዳስቀመጠው መሠረታዊ ሥርዓት “አንድ ሰው ትክክል ነው ብሎ የሚመራበት ደንብ” የሚል ፍቺ ሊሰጠው ይችላል። መሠረታዊ ሥርዓቶች በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ተጽዕኖ ከማሳደራቸውም በላይ የምንከተለውን የሕይወት አቅጣጫ ይወስናሉ። መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደ ኮምፓስ ሊያገለግሉ ይችላሉ።
ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ተከታዮቹ በማቴዎስ 7:12 ላይ የሚገኘውን “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” የሚለውን ወርቃማውን ሕግ እንዲጠብቁ አሳስቧቸዋል። የኮንፊሽየስ ተከታዮች እንደ ደግነት፣ ትሕትና፣ አክብሮትና ታማኝነት የመሳሰሉ ባሕርያትን የሚያካትቱትን የሊን እና የጄንን መሠረታዊ ሥርዓቶች ይጠብቃሉ። ሃይማኖተኛ ያልሆኑ ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ወይም አኗኗራቸውን የሚወስኑላቸው አንዳንድ መመሪያዎች አሏቸው።
መከተል ያለብን የትኛውን መሠረታዊ ሥርዓት ነው?
የሆነ ሆኖ ጥሩም መጥፎም መሠረታዊ ሥርዓቶች መኖራቸውን መዘንጋት አይኖርብንም። ለምሳሌ ያህል ላለፉት አሥርተ ዓመታት ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ጊዜያት ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎች እኔ ልቅደም (me-ism) ተብሎ በሚታወቅ መንፈስ ሲመሩ ቆይተዋል። ብዙዎች እኔ ልቅደም የሚለውን ስያሜ የማያውቁት ወይም በእነርሱ ላይ እንደማይሠራ አድርገው የሚያስቡ ቢሆንም እንኳ ለሥነ ምግባር የአቋም ደረጃዎች ጀርባቸውን ሰጥተው የሕይወታቸው ደንብ አድርገው በደመ ነፍስ የሚከተሉት መሠረታዊ ሥርዓት ነው። ትርጉሙ ምንም ይሁን ምን እኔ ልቅደም የሚለው መንፈስ ብዙውን ጊዜ ከፍቅረ ነዋይ ጋር ተያይዞ የሚገለጥ የራስ ወዳድነት ባሕርይ መግለጫ ነው። በቻይና አንድ የቴሌቪዥን አስተዳዳሪ “የምንመራባቸው ሁለት መሠረታዊ ሥርዓቶች አሉን። አንደኛው የሌሎችን ፍላጎት ማርካት ሲሆን ሌላው ደግሞ ገንዘብ በገፍ ማግኘት ነው” በማለት ተናግረዋል።
እኔ ልቅደም የሚለው መንፈስ ከማግኔት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ታዲያ አንድ ማግኔት በኮምፓስ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? ሁለቱም ጎን ለጎን ሲቀመጡ የኮምፓሱ ቀስት ወደተሳሳተ አቅጣጫ ይጠቁማል። በተመሳሳይም እኔ ልቅደም የሚለው መንፈስ አንድ ግለሰብ ሁሉንም ነገር ከራሱ ፍላጎት ቀጥሎ እንዲያስቀምጥ በማድረግ የሥነ ምግባር ኮምፓሱን ወይም የሚመራበትን ትክክለኛ ደንብ ሊያዛባበት ይችላል።
እኔ ልቅደም የሚለው መንፈስ በዚህ በእኛ ዘመን የተፈጠረ እንዳልሆነ ብታውቅ ትገረም ይሆን? እንዲህ ዓይነቱ መንፈስ የተጠነሰሰው የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ፈጣሪያችን ያወጣላቸውን የሥነ ምግባር መስፈርቶች ችላ ባሉበት በዔድን ገነት ውስጥ ነው። ይህም የሥነ ምግባር ኮምፓሳቸውን አዛባባቸው። መላው የሰው ዘር የአዳምና የሔዋን ዘር እንደመሆኑ መጠን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “እኔ ልቅደም” የሚል ስያሜ በተሰጠው በዚህ መንፈስ እየተጠቃ ነው።—ዘፍጥረት 3:6-8, 12
በስፋት የተዛመተው ይህ ባሕርይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ‘የመጨረሻ ቀን’ ብሎ በሚጠራው በዚህ ‘አስጨናቂ ዘመን’ ውስጥ ጎልቶ ይታያል። ብዙ ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ” ናቸው። እኛም ይህንን እኔ ልቅደም የሚለውን ባሕርይ እንድንኮርጅ ተጽዕኖ ቢደርስብን ሊያስደንቀን አይገባም።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
ኦላፍ የሚባል አንድ ወጣት እንደሚከተለው በማለት አውሮፓ ለሚገኝ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ከጻፈው ሐሳብ ጋር ትስማማ ይሆናል:- “በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆኖ መመላለስ በተለይ ለእኛ ለወጣቶች በጣም አስቸጋሪ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ መከተል አስፈላጊ መሆኑን ማሳሰባችሁን ግፉበት።”
ኦላፍ አስተዋይነት የተንጸባረቀበት ሐሳብ ሰንዝሯል። አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ወጣትም ሆንን አዛውንት ባሕርይን በሚመለከት ከፍተኛ የሥነ ምግባር መስፈርቶችን እንድንጠብቅ ይረዱናል። በተጨማሪም እኔ ልቅደም የሚል ስያሜ ተሰጠውም አልተሰጠው እንዲህ ያለውን መንፈስ እንድንቋቋም ይረዱናል። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት ሊጠቅሙህ እንደሚችሉ ይበልጥ ማወቅ የምትፈልግ ከሆነ የሚቀጥለውን ርዕስ አንብብ።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬ ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ስለ ሌሎች ደንታ የላቸውም