የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w06 12/15 ገጽ 8-11
  • ማራኪ በሆነችው ሄይቲ ምሥራቹን ማዳረስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ማራኪ በሆነችው ሄይቲ ምሥራቹን ማዳረስ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • ንዑስ ርዕሶች
  • በአንዲት የገጠር ከተማ መስበክ
  • ምሥራቹ በሥነ ጥበብ ሲገለጽ
  • ምሥራቹን በትምህርት ቤት መስበክ
  • በክሪኦል ቋንቋ መስበክ
  • ምሥራቹን በእስር ቤት መስበክ
  • ንቁ! ብዙዎች ምሥራቹን እንዲሰሙ አድርጓል
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
w06 12/15 ገጽ 8-11

ማራኪ በሆነችው ሄይቲ ምሥራቹን ማዳረስ

ሄይቲ እና ዶሚኒካን ሪፑብሊክ የሚባሉት አገሮች ሞቃታማ በሆነችው በሂስፓኒዮላ ደሴት ላይ ይገኛሉ፤ ይህች ደሴት በካሪቢያን አካባቢ በረጃጅም ተራሮቿ ትታወቃለች። በዚህች ደሴት ላይ የሚገኙት ብዙዎቹ ተራሮች ከ2,400 ሜትር በላይ ከፍታ አላቸው። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ቀዝቃዛ በሚባሉት ወራት በተራሮቹ አናት ላይ የሚገኙት ትናንሽ ኩሬዎች ስስ በሆነ በረዶ ይሸፈናሉ።

በደቡባዊ ሄይቲ የሚገኙት ተራሮችና ሸለቆዎች ልምላሜ የተላበሱና ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች የተሸፈኑ ናቸው። በሌሎቹ አካባቢዎች ግን ተራሮቹ በደን ጭፍጨፋ በመራቆታቸው ገላጣ ሆነዋል፤ ከሩቅ ሲታዩም የተጠረቡ ይመስላሉ። ወደ ሰሜንም ሆነ ወደ ደቡብ ብትጓዝ ሄይቲ ውብና ማራኪ እንደሆነች ትመለከታለህ። በተራራው ላይ በሚገኙት አንዳንድ ጠባብና ጠመዝማዛ መንገዶች ስትጓዝ፣ እጅግ ማራኪ የሆነውንና የተለያየ ገጽታ ያለውን መልከአ ምድራዊ አቀማመጥ እንዲሁም ባሕሩን እስከ ረዥም ርቀት መመልከት ትችላለህ። ዓይነታቸው ተዘርዝሮ የማያልቅና ደማቅ ቀለማት ያሏቸው አበቦችም እይታን ይጋብዛሉ።

ማራኪ በሆነችው በዚህች አገር ከሚኖሩት 8.3 ሚሊዮን ሕዝቦች መካከል አብዛኞቹ የአፍሪካ ዝርያ ያላቸው የገጠር ሰዎች ናቸው። ምንም እንኳ ብዙዎቹ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ድሆች ቢሆኑም ደጎችና እንግዳ ተቀባዮች ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች 60 ለሚያክሉ ዓመታት የአምላክን መንግሥት ምሥራች በዚህች አገር ሲሰብኩ የቆዩ ሲሆን ሕዝቡም በጥሩ ሁኔታ ተቀብሏቸዋል።—ማቴዎስ 24:14

በአንዲት የገጠር ከተማ መስበክ

ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ገጠራማ አካባቢ የሄደች አንዲት ሚስዮናዊት እህት የሰጠችው አስተያየት የብዙዎቹን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው። እንዲህ በማለት ጽፋለች:-

“በመጋቢት 2003፣ አንድ ቀን ካባሬ ከምትባለው ከተማ የግማሽ ሰዓት መንገድ በምትርቅ ካዛል በተባለች አነስተኛ መንደር ለመስበክ ሄድን። ካባሬ ከዋና ከተማው ከፖርቶፕራንስ በስተ ሰሜን 30 ኪሎ ሜትር ያህል የምትርቅ ሲሆን አሁን ያለንበት የሚስዮናውያን ቤት የሚገኘውም በዚያ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ካዛል ሄደው የሰበኩት በ1999 ስለነበር ጠዋት በ1:00 ጉዟችንን የጀመርነው በከፍተኛ ጉጉት ነበር። ሃያ ሁለት የምንሆን ሰዎች (የጉባኤያችን አባላት በጠቅላላ ማለት ይቻላል) አስቸጋሪ ለሆኑ መንገዶች በተሠሩ ሁለት መኪኖች ተሳፍረን ጉዟችንን ቀጠልን። እየተጨዋወትንና እየሳቅን ኮረኮንች በሆኑት ቁልቁለት መንገዶች ላይ ስንጓዝ ከቆየን በኋላ በርካታ ትላልቅ ዛፎች ወደሚገኙበት ሸለቆ ደረስን። በዚህ ሸለቆ ውስጥ የሚፈሰው ወንዝ የካዛልን መንደር ለሁለት ይከፍላታል።

“ጸጥታ የሰፈነባት ይህች መንደር የተቆረቆረችው በ1800ዎቹ ነው። በወቅቱ በሄይቲ ይኖሩ የነበሩትን ባሮች፣ ነጻነት እንዲያገኙ ለመርዳት የመጡ አንዳንድ ፖላንዳውያን ወታደሮች የደሴቲቱን ነዋሪዎች አግብተው ለም በሆነው በዚህ ሸለቋማ አካባቢ መኖር ጀመሩ። በመሆኑም ይህ ጥምረት ውብ የሆነ ድብልቅ ሕዝብ አስገኘ። ነጭ፣ ጠይምና ቡናማ የቆዳ ቀለም እንዲሁም አረንጎዴና ቡናማ የዓይን ቀለም ያላቸውን የገጠር ነዋሪዎች መመልከት በጣም ያስደንቃል።

“መጀመሪያ ያንኳኳነው ቤት ውስጥ ያገኘነው ሰው ፍላጎት አልነበረውም። እየተመለስን እያለ አንድ ሰው እኛን ለማግኘት ሲመጣ ተመለከትነው። በኢየሱስና በአምላክ መካከል ልዩነት መኖሩን እናምን እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ፈልጎ ነበር። እኛም መጽሐፍ ቅዱሱን እንዲያመጣ ከነገርነው በኋላ በቅዱስ ጽሑፉ ላይ የተመሠረተ ውይይት አደረግን፤ ከዚያም ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነና ይሖዋ ደግሞ ብቸኛው “እውነተኛ አምላክ” መሆኑን ተገነዘበ። (ዮሐንስ 17:3) ብዙ ሰዎች ቁጭ ብለን ከእነርሱ ጋር እንድንነጋገር ይጋብዙን ነበር። አንዳንዶቹም ‘ተመልሳችሁ መጥታችሁ መጽሐፍ ቅዱስን የምታስተምሩን መቼ ነው?’ ብለው ይጠይቁን ነበር።

“እኩለ ቀን ላይ ምሳችንን ለመመገብ የሚያመች ጥላ ያለበት ግሩም ቦታ አገኘን። ሁለት እህቶች በትልቅ ድስት በጣም ጣፋጭ የሆነ ዓሣ አዘጋጅተውልን ነበር! ምሳችንን እየበላንና እየተጨዋወትን በአጠገባችን ለሚያልፉ መንገደኞችም እንሰብክ ነበር። ከዚያም ከወንዙ ማዶ ወዳለው አካባቢ ሄድን። አነስተኛ ከሆኑት ቤቶቻቸው አጠገብ በሚገኙት ዛፎች ሥር ከሚቀመጡት ከእነዚህ ተግባቢ ሰዎች ጋር መወያየት እጅግ አስደሳች ነበር። ልጆች ሲጫወቱ፣ በወንዙ ዳርቻ ላይ ሴቶች ልብስ ሲያጥቡ እንዲሁም በዕድሜ የገፉ ሴቶች ቡና ሲፈጩ መመልከት እንዴት ያስደስታል!

“በውሏችን ሁላችንም ተደስተን ስለነበር ሳናስበው አሥር ሰዓት በመሆኑ መኪኖቻችን ውስጥ ገብተን ወደ ካባሬ ተመለስን። እኔና ባለቤቴ እንግዳ ተቀባይና ተግባቢ የሆኑ ሰዎች ወዳገኘንባት ወደ ካዛል ባደረግነው የመጀመሪያ ጉዞ በጣም ተደስተናል።”

በ1945 የመጀመሪያዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች ሚስዮናውያን በሄይቲ መስበክ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በዚህች አገር የሚገኙት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር ያለማቋረጥ እየጨመረ ነው። በአሁኑ ጊዜ ወደ 14,000 የሚጠጉ አስፋፊዎች በስብከቱ ሥራ እየተካፈሉ ሲሆን ከ22,000 የሚበልጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይመራሉ። በመጋቢት 2005 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ የተገኙትን 59,372 የሚያህሉ ሰዎችን ልብ መንካት የቻሉ ሲሆን አሁንም የአምላክን መንግሥት ምሥራች በይፋ በማወጅ ላይ ይገኛሉ። የይሖዋ ምሥክሮች እያከናወኑት ያለው ሥራ የሰዎችን ሕይወት እየለወጠ እንደሆነ የሚያሳዩ የተለያዩ ሁኔታዎችን እንመልከት።

ምሥራቹ በሥነ ጥበብ ሲገለጽ

አብዛኞቹ የሄይቲ ነዋሪዎች ደማቅ ቀለማትን ይወዳሉ። ይህ ደግሞ በሚለብሷቸው ልብሶች፣ ቤቶቻቸውን በሚቀቧቸው ቀለሞች፣ በግቢዎቻቸው ውስጥ በሚተክሏቸው የተለያዩ አበቦችና በሥነ ጥበብ ሥራዎቻቸው ላይ ይንጸባረቃል። በፖርቶፕራንስ ጎዳናዎች ላይ፣ ላር ኤስየን ተብሎ የሚጠራውን የአካባቢውን ስልት ተከትለው በሸራ ላይ የተሠሩ ደማቅ ቀለማት ያላቸው ሥዕሎች በብዛት ለገበያ ይቀርባሉ። እነዚህን ሥዕሎች ለመግዛት ከበርካታ የዓለም ክፍሎች የተለያዩ ሰዎች ይመጣሉ።

ደማቅ ቀለማት የሚታዩት በሸራዎች ላይ ብቻ አይደለም። በፖርቶፕራንስ ጎዳናዎች ላይ ካሚዮኔት ወይም ታፕ ታፕ ተብለው የሚጠሩ ለሕዝብ መጓጓዣነት የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎችም በብዛት ይታያሉ። በእነዚህ ተሽከርካሪዎች ላይ ውስብስብ የሆነ ንድፍ ያላቸው ሥዕሎች የተሳሉ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ሥዕሎቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው።

በመንገድ ላይ እየሄድክ በድንገት አንድ የምታውቀው ሥዕል፣ ለምሳሌ ያህል አዳምና ሔዋን በኤድን ገነት ውስጥ ሆነው የሚያሳይ ሥዕል ልትመለከት ትችላለህ። እንዲያውም አሁን ባለፈው ካሚዮኔት የኋላ መስተዋት ላይ ይህ ሥዕል ይታያል። አብዛኛውን ጊዜ በእነዚህ ተሽከርካሪዎች ላይ የይሖዋን ስም የያዙ ጥቅሶች ወይም አባባሎች የሚጻፉ ሲሆን ነጋዴዎችም የንግድ ድርጅቶቻቸውን ሲሰይሙ በመለኮታዊው ስም ይጠቀማሉ።

ምሥራቹን በትምህርት ቤት መስበክ

በሄይቲ የሚገኙ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች አብረዋቸው ለሚማሩት ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ጥሩ አጋጣሚ አላቸው። አሥራ ሰባት ዓመት የሆናት አንዲት ወጣት የይሖዋ ምሥክር ያጋጠማት ተሞክሮ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል።

“አንድ ቀን፣ በክፍል ውስጥ አብሮኝ የሚማር ልጅ ወደ እኔ መጣና ‘ምንዝር’ ምን ማለት እንደሆነ ጠየቀኝ። ሆነ ብሎ እኔን ለመቅረብ ሲል ያነሳው ጥያቄ ስለመሰለኝ ሳልመልስለት ቀረሁ። ይሁን እንጂ አብሮን ለሚማር ሌላ ልጅም ተመሳሳይ ጥያቄ ሲያቀርብለት በክፍሉ ውስጥ ያሉት ተማሪዎች በሙሉ መልሱን ለማወቅ ፈለጉ። በመሆኑም በቀጣዩ ሳምንት በርዕሱ ላይ ምርምር ካደረግሁ በኋላ ለክፍሉ በሙሉ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ሥነ ምግባራዊ፣ መንፈሳዊና አካላዊ ንጽሕናቸውን ለመጠበቅ የሚጥሩት ለምን እንደሆነ የሚገልጽ ንግግር አቀረብኩ።

“ተማሪዎቹም በርካታ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ በሰጠኋቸው መልሶችም ረክተዋል። በመጀመሪያ ላይ ሲያመነቱ የነበሩት የትምህርት ቤቱ ዲሬክተር እንኳ ሳይቀሩ በርካታ ጥያቄዎችን የጠየቁ ሲሆን ለሌሎች ክፍሎችም ንግግሩን እንዳቀርብ ዝግጅት አደረጉ። ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶችa የተባለውን መጽሐፍ ካሳየኋቸው በኋላ ብዙዎቹ መጽሐፉን ለማንበብ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ። በሚቀጥለውም ቀን አብረውኝ ለሚማሩት ልጆች 45 መጽሐፎችን አበረከትኩ። ብዙዎቹ መጽሐፉን በፍጥነት አንብበው የጨረሱ ሲሆን አንዳንዶቹ በአካባቢያቸው ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረዋል። በአካባቢዬ የሚኖር አንድ ተማሪ በአሁኑ ጊዜ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ይገኛል።”

በክሪኦል ቋንቋ መስበክ

የሄይቲ ሕዝብም ሆነ መልክአ ምድር ማራኪ ናቸው፤ የፈረንሳይኛ ቃላትን ከምዕራብ አፍሪካ ሰዋሰው ጋር አጣምሮ የያዘው የሄይቲ ክሪኦል የተባለው ቋንቋም ቢሆን ትኩረት የሚስብ ነው። የሄይቲ ነዋሪዎች አፍ መፍቻ ቋንቋ ይህ ሲሆን ልባቸው የሚነካውም በዚህ ቋንቋ ሲነገራቸው ነው። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎታቸውን በአብዛኛው የሚያከናውኑት በዚህ ቋንቋ ሲሆን በክሪኦል ቋንቋ ተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ ነው።

በ1987 በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው ብሮሹር በሄይቲ ክሪኦል ቋንቋ ተተረጎመ፤ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው መጽሐፍና አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለው ብሮሹር በክሪኦል ቋንቋ ተዘጋጅተዋል። እነዚህ ጽሑፎች ከአምላክ ቃል መሠረታዊ እውቀት ለማግኘት ለሚፈልጉ አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ከፍተኛ እገዛ አድርገዋል። ከመስከረም 1, 2002 ጀምሮ መጠበቂያ ግንብም በክሪኦል ቋንቋ መዘጋጀት ጀምሯል። በአሁኑ ጊዜ በሄይቲ በፈረንሳይኛ የተዘጋጁ ጽሑፎችን እየተጠቀሙ ቢሆኑም አብዛኞቹ ሰዎች ጽሑፎቹን በራሳቸው ቋንቋ ቢያነቡ ይመርጣሉ።

ምሥራቹን በእስር ቤት መስበክ

የይሖዋ ምሥክሮች ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ምሥራቹን በእስር ቤት ለሚገኙ ወንዶችና ሴቶች መስበክ ጀምረዋል። ምሥክሮቹ፣ በእስር ቤት ውስጥ በአሳዛኝ ሁኔታ ለሚገኙት ሰዎች ማጽናኛ የሚሰጣቸውን መልእክት በመንገራቸው ደስተኞች ናቸው። አንድ ወንድም እንዲህ በማለት ሪፖርት አድርጓል:-

“ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አንድ ወኅኒ ቤት በሄድንበት ወቅት እስረኞቹን እንድናነጋግራቸው ሰፊ ክፍል ውስጥ አስገቧቸው። ምን ምላሽ ሊሰጡን እንደሚችሉ እያሰብን ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማሩ ልንረዳቸው እንደመጣን ስንነግራቸው 50ዎቹም እስረኞች ጥሩ አቀባበል አደረጉልን። በክሪኦል ቋንቋ የተዘጋጁትን አፕላይ ዩርሰልፍ ቱ ሪዲንግ ኤንድ ራይቲንግ (ማንበብና መጻፍ መማር) እንዲሁም በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባሉትን ብሮሹሮች በማበርከት 26 ከሚያክሉት እስረኞች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርን። በቦታው ከነበሩት መካከል አሥር የሚሆኑት ማንበብና መጻፍ አይችሉም፤ ሆኖም በብሮሹሩ ላይ ያሉትን ሥዕሎች ተጠቅመው እንዴት ቃላቶቹን መረዳት እንደሚችሉ ስናሳያቸው ፍላጎት አሳዩ።”

እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ወኅኒ ቤቱ ተመልሰው ሲሄዱ አንድ እስረኛ እንዲህ ብሏል:- “ብሮሹሩን ደግሜ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ። ሁልጊዜ በትምህርቱ ላይ አሰላስላለሁ፤ የምትመለሱበትን ቀን በጉጉት እየተጠባበቅኩ ነበር።” በመሣሪያ አስፈራርቶ በመዝረፍ ወንጀል የታሰረ አንድ ሰው መለወጥ እንደሚፈልግ የገለጸ ከመሆኑም በላይ ባለቤቱን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናት ሰው እንዲላክላት ጠይቋል። የሁለት ልጆች አባት የሆነ አንድ እስረኛም ባለቤቱ በእውነተኛውና በሐሰተኛው እምነት መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ እንድትችል የሚያስጠናት ሰው እንዲላክላት ጠይቋል። ከቤተ ክርስቲያኑ አባላት በጣም ብዙ ገንዘብ በማጭበርበር ወንጀል የታሰረ አንድ የፕሮቴስታንት ቄስ፣ አሁን እውነትን እንዳገኘና ከእስር ቤት ሲወጣ የቤተ ክርስቲያኑን አባላት የይሖዋ ምሥክሮች መሆን እንዲችሉ እንደሚረዳቸው ተናግሯል።

ሌላ እስረኛም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን በክሪኦል ቋንቋ የተዘጋጀ ብሮሹር ስላልነበረው አብሮት ከታሰረው ሰው ብሮሹሩን ወስዶ ሁሉንም በእጁ ከገለበጠው በኋላ በቃሉ አጥንቶታል። አንዲት እስረኛ ደግሞ ዘጠኝ ለሚያህሉ አብረዋት ለታሰሩ ሴቶች የተማረችውን ማካፈል እንዲያውም ሁሉንም ማስጠናት ጀምራለች። አንድ ሌላም እስረኛ ብሮሹሩን ጨርሶ እውቀት መጽሐፍን እያጠና ሲሆን አብረውት ለታሰሩትም ይሰብካል። ብዙም ሳይቆይ በእስር ቤት ያሉ አራት ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመረ።

ሜርኮኒb የይሖዋ ምሥክሮች ዘመዶች ያሉት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስንም ያጠና ነበር። ዘመዶቹ የሚያመጡለትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አብረውት ለታሰሩት ሰዎች እንዲያነቡ ይሰጣቸው ነበር። እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “አብረውኝ ለታሰሩት ጽሑፎችን መስጠት ስጀመር የይሖዋ ምሥክር ብለው ይጠሩኝ ጀምር። እኔ ግን የይሖዋ ምሥክር መሆን ምን ማለት እንደሆነ ስለማውቅ የይሖዋ ምሥክር እንዳልሆንኩ እነግራቸዋለሁ። አሁን ግን ነገሩን በቁም ነገር ይዤ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና መጠመቅ እፈልጋለሁ። ወጣት በነበርኩበት ጊዜ የወንድሞቼን ዓይነት ጎዳና ተከትዬ ቢሆን ኖሮ እስር ቤት አልገባም ነበር።”

ከሜርኮኒ ጽሑፍ የወሰደ አንድ እስረኛ እየመጣ ለሚጠይቃቸው የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብሎታል:- “ባለፈው ሰኞ ከመምጣትህ በፊት በጣም ተጨንቄ ስለነበር ራሴን ለመግደል አስቤ ነበር። ሆኖም መጽሔቶቹን ካነበብኩ በኋላ ለሠራኋቸው መጥፎ ድርጊቶች ይቅር እንዲለኝና ትክክለኛውን መንገድ የሚያሳየኝ ሰው እንዲልክልኝ ወደ አምላክ ጸለይኩ። እስረኞቹን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ለመጋበዝ በሚቀጥለው ቀን ስትመጣ እጅግ ተደሰትኩ! ይሖዋን እንዴት ማገልገል እንደምችል እንድታስተምረኝ እፈልጋለሁ።”

ንቁ! ብዙዎች ምሥራቹን እንዲሰሙ አድርጓል

የኅዳር 8, 2000 ንቁ! መጽሔት (እንግሊዝኛ) ስለ ነርስነት ሙያ ይናገራል። አንዲት ሴት የዚህን እትም 2,000 ቅጂዎች ወስዳ በፖርቶፕራንስ በተደረገ ሴሚናር ላይ ለተገኙት ነርሶች አሰራጭታለች። ስለ ፖሊሶችና ስለ ሥራቸው የሚናገረው የነሐሴ 2002 ንቁ! መጽሔትም በፖርቶፕራንስ ለሚገኙ ፖሊሶች በሰፊው ተሰራጭቷል። ይህንን መጽሔት የወደዱት ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶች አሁንም ጭምር በመንገድ ላይ ወንድሞችን አስቁመው የመጽሔቱን ተጨማሪ ቅጂዎች ይጠይቃሉ።

በዓለም የጤና ድርጅት ውስጥ የሚሠሩ አንዲት ሴት ኤድስ ስለሚያስከትለው ችግር ሰዎችን ለማስተማር በቅርቡ ፕሮግራም አዘጋጅተው ነበር። እኚህ ሴት ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የተጋበዙ ሲሆን በዚህ ርዕስ ዙሪያ የተዘጋጀውን በንቁ! መጽሔት ላይ የሚገኝ ሐሳብ አሳዩዋቸው። ኤድስን ከሁሉ በተሻለ መልኩ ለመከላከልና በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለመርዳት ምን ማድረግ እንደሚቻል የሚያብራሩ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተውጣጡ ርዕሶችን ሲመለከቱ በጣም ተደነቁ። ግለሰቧ፣ ንቁ! በዚህ ርዕስ ዙሪያ ይህን የመሰለ ሐሳብ በማውጣት ረገድ ግንባር ቀደም መሆኑንም ተናግረዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች ማራኪ የሆነችውን ሄይቲ ጨምሮ በ234 አገሮችና ደሴቶች የመንግሥቱን ምሥራች በተለያዩ መንገዶች እያሰራጩ ናቸው። ብዙዎቹ ተስፋ ላዘለው ለዚህ መልእክት በጎ ምላሽ እየሰጡ ሲሆን አሁን በሕይወታቸው ውስጥ ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች ባሻገር ያለውን አዲስ ዓለም እንዲመለከቱ እርዳታ እያገኙ ነው። በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን የሚያመልኩ ሁሉ መጨረሻ የሌለው ፍጹም ሕይወት ያገኛሉ።—ራእይ 21:4

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በዚህ ርዕስ ውስጥ ስማቸው የተጠቀሱት ጽሑፎች በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ናቸው።

b ስሙ ተቀይሯል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከጀርባ ያለው ፎቶ:- ©Adalberto Rios Szalay/photodisc/age fotostock

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ