የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w12 1/1 ገጽ 12-15
  • ድንበር ያልበገረው አንድነት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ድንበር ያልበገረው አንድነት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በተከፈለ ሸለቆ ውስጥ የሚታይ አንድነት
  • የአንድነቱ መሠረት
  • አምልኳችንን የምናከናውንባቸው ቦታዎች
    የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
  • ለመንግሥት አዳራሻችሁ አክብሮት ታሳያላችሁ?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2011
  • ሥራው እየተስፋፋ ስለሄደ ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች አስፈልገዋል
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1993
  • ይህ የአምልኮ ቦታችን ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
w12 1/1 ገጽ 12-15

ድንበር ያልበገረው አንድነት

የይሖዋ ምሥክሮች በሰዎች መካከል መከፋፈል የሚፈጥሩ መሰናክሎችን ለማለፍ ይጥራሉ። ኢየሱስ “እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ከተናገረው ሐሳብ ጋር በሚስማማ መንገድ ይኖራሉ። (ማቴዎስ 23:8) በፖርቱጋልና በስፔን በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የአምልኮ ቦታዎች ያለው ሁኔታ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል።

ቫሌንሳ ዶ ሚንዮ የተባለችው በሰሜናዊ ፖርቱጋል የምትገኝ በግንብ የታጠረች ከተማ የተሠራችው አደገኛ በሆነ ዘመን ነበር። ከከተማዋ የመጠበቂያ ማማ ላይ ሆኖ ስፔንንና ፖርቱጋልን የሚያዋስነውን የሚንዮን ወንዝ ቁልቁል ማየት ይቻላል። ከወንዙ ማዶ ቱኢ የተባለችው የስፔን ከተማ የምትገኝ ሲሆን በዚያ ያለው ካቴድራል ምሽግ ይመስላል። የቱኢና የቫሌንሳ ዋነኛ ምሽጎች ስፔንና ፖርቱጋል ይዋጉ በነበረበት በ17ኛው መቶ ዘመን የተሠሩ ናቸው።

በ1995 በእነዚህ ሁለት የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት መካከል የነበሩት የድንበር ምልክቶችና የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ተነሱ። ይሁን እንጂ ሕዝቦች አንድነት እንዲኖራቸው ለማድረግ የድንበር መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችን ከማስወገድ ያለፈ ነገር ያስፈልጋል። የሰዎች አእምሮና ልብ መለወጥ ይኖርበታል። በቫሌንሳ የሚገኝ አንድ አነስ ያለ ውብ ሕንፃ በድንበር በተለያዩ ሕዝቦች መካከል አንድነት ሊኖር እንደሚችል ማስረጃ ይሆናል። ይህ ሕንፃ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ወይም የአምልኮ ቦታ ሲሆን በስፔንና በፖርቱጋል ያሉ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በጋራ ይጠቀሙበታል።

ታሪኩ የጀመረው በ2001 ነው። በወቅቱ በቱኢ፣ ስፔን ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ የመንግሥት አዳራሽ አስፈልጓቸው ነበር። የተከራዩትን የመሰብሰቢያ ቦታ መልቀቅ የነበረባቸው ሲሆን አዲስ አዳራሽ ለመሥራት ደግሞ በቂ ገንዘብ አልነበራቸውም። ጉባኤው አነስተኛ ስለነበረ የአምልኮ ቦታ መከራየትም እንኳ ከአቅማቸው በላይ ነበር። ስለዚህ እነዚህ ስፔናውያን የይሖዋ ምሥክሮች በቫሌንሳ ያሉትን ፖርቱጋላዊ ወንድሞቻቸውን በአዳራሻቸው እንዲጠቀሙ ይፈቅዱላቸው እንደሆነ ጠየቋቸው፤ አዳራሹ የሚገኘው ከማዕከላዊ ቱኢ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ነው።

በስፔን ያለው የቱኢ ጉባኤ አባል የሆነው ኤድዋርዶ ቪላ “ምን መደረግ እንዳለበት በታኅሣስ 2001 ባደረግነው ስብሰባ ላይ ተወያየን” በማለት ያስታውሳል። “ከዚያ ስብሰባ ስወጣ ይሖዋ የፖርቱጋል ወንድሞቻችን ልባቸውን እንዲከፍቱልን እንዳደረገ ተገነዘብኩ። የሚያምር የመንግሥት አዳራሽ ለመሥራት ትልቅ መሥዋዕትነት ከፍለዋል፤ ያላቸውን ነገር ለማካፈል ፈቃደኞች መሆናቸውን ማየቴ እምነቴን አጠናክሮልኛል።”

በዚያ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ የነበረ አሜሪኩ አልሜዳ የሚባል ፖርቱጋላዊ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብሏል፦ “የስፔን ወንድሞቻችን በመንግሥት አዳራሻችን እንዲጠቀሙ በደስታ ፈቀድንላቸው። ይሖዋ ይህን ዝግጅት እንደሚባርከው ስለተማመንን ውሳኔውን ያሳለፍነው በአንድ ድምፅ ነበር።” በሁለቱም አገሮች የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች ተስማምተው በዚህ የመንግሥት አዳራሽ ይሰበሰባሉ። በቫሌንሳ የሚኖረው ፓውሎ “ለሌሎች እንግዳ ነገር ቢመስልም እኛ ግን የሁለት አገሮች ሕዝቦች መሆናችን እንኳ ትዝ አይለንም። መንፈሳዊ ወንድማማቾች ነን” በማለት ተናግሯል።

እንግዶች ወደ መንግሥት አዳራሹ ሲገቡ መጀመሪያ ከሚያስተውሏቸው ነገሮች መካከል በአዳራሹ ግድግዳ ላይ የተሰቀሉት ሁለት ሰዓቶች ይገኙበታል፤ እነዚህ ሰዓቶች አንድ ዓይነት ቢሆኑም ስፔን ከፖርቱጋል አንድ ሰዓት ስለምትቀድም የሚያሳዩት ሰዓት የተለያየ ነው። በዚህ የመንግሥት አዳራሽ በሚጠቀሙት ወንድሞች መካከል የሚታየው ልዩነት ግን ይህ ብቻ ነው ማለት ይቻላል። አዳራሹ እድሳት ባስፈለገው ጊዜ ከሁለቱም ጉባኤዎች የመጡትን ቀናተኛ የሆኑ ሠራተኞች በበላይነት የተቆጣጠረው በስፔን የሚገኘው የአካባቢ የግንባታ ኮሚቴ ነበር። ፓውሎ “በሥራው እኛን ለመርዳት ከስፔን ብዙ የግንባታ ባለሙያዎች የመጡ ሲሆን አንዳንዶቹ የሚኖሩት ከ160 ኪሎ ሜትር በላይ በሚርቅ አካባቢ ነበር” በማለት ያስታውሳል። “የእድሳቱ ሥራ በሁለቱ ጉባኤዎች መካከል ያለውን አንድነትና ፍቅር ይበልጥ አጠናክሮታል።”

ድንበር ያልበገረው አንድነት የታየበትን ሁለተኛ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት።

በተከፈለ ሸለቆ ውስጥ የሚታይ አንድነት

ፕዊግሴርዳ የስፔን ከተማ ስትሆን አገሪቱ ከፈረንሳይ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ ትገኛለች። ከተማዋ የተቆረቆረችው በረጃጅሞቹ የፒረኒዝ ተራሮች ተከቦ በሚገኘው ለምለም ሸለቆ እምብርት ላይ ነው። ሴርዳንያ በመባል የሚታወቀው ጠቅላላው ሸለቆ በአንድ ወቅት የስፔን ክፍል ነበር። ይሁንና ስፔንና ፈረንሳይ በ1659 የፒረኒዝ ውል የተባለ የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ስፔን የሸለቆውን ግማሽ ለፈረንሳይ ለቀቀች።

በዛሬው ጊዜ የፈረንሳይ ሰዎች የሸለቆው ቁልፍ ከተማ በሆነችው በፕዊግሴርዳ ይገበያያሉ። ከ1997 ወዲህ ደግሞ በፕዊግሴርዳ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሻቸውን ለፈረንሳይ ወንድሞቻቸው ከፍተውላቸዋል። በዚያ ዓመት የፈረንሳይ የይሖዋ ምሥክሮች የተከራዩትን አዳራሽ ለመልቀቅ ተገድደው ነበር። በፈረንሳይ የሚገኘው ለእነዚህ ወንድሞች የሚቀርባቸው የመንግሥት አዳራሽ በመኪና የአንድ ሰዓት መንገድ ያስኬዳል፤ በቅዝቃዜው ወቅት ደግሞ መንገደኞች ወደዚህ አዳራሽ ለመሄድ የሚያቋርጡት በተራራው ላይ ያለው መንገድ ብዙውን ጊዜ በበረዶ ይዘጋል።

የፈረንሳይ የይሖዋ ምሥክሮች የመሰብሰቢያ ቦታ በጣም እንደሚያስፈልጋቸው በገለጹ ጊዜ የስፔን ወንድሞች በእነሱ የመንግሥት አዳራሽ እንዲጠቀሙ ወዲያውኑ ፈቀዱላቸው። በአካባቢው የሚኖረው ፕሬም የተባለ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉም የስፔን ወንድሞች የመንግሥት አዳራሹን በጋራ ለመጠቀም ጓጉተው ነበር። እንደዚህ ዓይነቱ መንፈስ ሊኖር የቻለው ለዓመታት ቅዱስ ጽሑፋዊ ሥልጠና በማግኘታችን እንደሆነ ግልጽ ነው። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የመንግሥት አዳራሻችንን በጋራ መጠቀም የጀመርን ሲሆን ላለፉት 13 ዓመታት አብረን ስንጠቀምበት ቆይተናል።”

በፈረንሳይ ባለው ጉባኤ የበላይ ተመልካች የሆነው ኤሪክ “በፕዊግሴርዳ የሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ለእኛ በጣም አመቺ ቦታ ላይ ነበረ” በማለት ተናግሯል። “የስፔን ጉባኤ አባላት ያደረጉልንን ሞቅ ያለ አቀባበል እስከ ዛሬ ድረስ አስታውሰዋለሁ። የመንግሥት አዳራሻቸውን ውብ በሆኑ አበቦች ያስጌጡት ከመሆኑም ሌላ ‘ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ እንኳን ደህና መጣችሁ’ የሚል ጽሑፍ አዘጋጅተው ነበር።”

“በፈረንሳይ የነበረው የመንግሥት አዳራሻችን ሲዘጋ ሰዎች ጉባኤው የተበተነ መስሏቸው ነበር” በማለት ኤሪክ አክሎ ይናገራል። “ይሁን እንጂ በአካባቢው ዘወትር የምናከናውነው የስብከት እንቅስቃሴና በስፔን በምናደርጋቸው የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ሰዎችን የሚያበረታቱ የመጋበዣ ወረቀቶችን ማሰራጨታችን ጉባኤያችን እንዳልተበተነ በግልጽ አሳይቷል። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በስፔን ወዳለው አዳራሽ በደስታ ይመጡ ነበር። ከዚህም በላይ በስፔን ካሉ ወንድሞቻችን ጋር በአንድ አዳራሽ የምንጠቀም መሆናችን እርስ በርስ አቀራርቦናል። እርግጥ ነው፣ ከዚያ ቀደም ከድንበሩ ባሻገር ባለው የስፔን ክልል ውስጥ ጉባኤ እንዳለ ብናውቅም እምብዛም አንገናኝም ነበር። አሁን ግን ዘወትር ስለምንገናኝ በዚህ ርቆ በሚገኘው ተራራማ ሸለቆ ውስጥ ብቻችንን እንዳለን አይሰማንም።”

በመካከላቸው ያለው የባሕል ልዩነት ምን ዓይነት ስሜት ፈጥሮ ይሆን? አንዲት በ80ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ፈረንሳዊት እህት “ስብሰባዎቻችንን ድንበሩን ተሻግረን በስፔን እንደምናደርግ በሰማሁ ጊዜ በተወሰነ መጠን አሳስቦኝ ነበር” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። “ይሁን እንጂ የፕዊግሴርዳ ወንድሞች ጥሩ አድርገው ስለተቀበሉንና ወዳጃዊ መንፈስ ስላሳዩን ስብሰባችንን እዚያ ማድረጋችን ምንም ዓይነት ችግር አላስከተለም፤ ለዚህም ሊመሰገኑ ይገባል። ይህ ሁኔታ የይሖዋ ሕዝቦችን ዓለም አቀፋዊ አንድነት የሚያሳይ አጋጣሚ ከፍቷል።”

የአንድነቱ መሠረት

የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት፣ “በአውሮፓ ሕዝቦች መካከል ከምንጊዜውም ይበልጥ የጠበቀ አንድነት እንዲኖር የሚያደርግ መሠረት ለመጣል እንደቆረጡ” የኅብረቱ መሥራቾች ተናገረው ነበር። በ1980ዎቹና በ1990ዎቹ ዓመታት የድንበር ምልክቶች የተወገዱት ይህን ሂደት ለማፋጠን ታስቦ ነበር። ይሁን እንጂ ልዩነቶች ከሕዝቡ አእምሮም መወገድ አለባቸው።

የይሖዋ ምሥክሮች ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻንና አለመተማመንን ከሥሩ ነቅለው ለማጥፋት ጥረት ያደርጋሉ። ከተለያየ ዘር የተውጣጡ መሆናቸው ጥቅም እንዳለው የሚገነዘቡ ከመሆኑም ሌላ “አምላክ እንደማያዳላ” ያምናሉ። (የሐዋርያት ሥራ 10:34) በብሔራት አቀፍ ስብሰባዎቻቸውና በመንግሥት አዳራሾቻቸው ውስጥ አንድ ላይ በሚሆኑበት ጊዜ “ወንድሞች ተስማምተው በአንድነት ሲኖሩ፣ እንዴት መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!” የሚለውን ጥቅስ እውነተኝነት መመልከት ችለዋል። (መዝሙር 133:1) በቫሌንሳና በፕዊግሴርዳ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች በአጎራባች አገሮች ካሉት ወንድሞቻቸው ጋር የፈጠሩት አንድነት ለዚህ ሕያው ምሥክር ነው።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ለሌሎች እንግዳ ነገር ቢመስልም እኛ ግን የሁለት አገሮች ሕዝቦች መሆናችን እንኳ ትዝ አይለንም። መንፈሳዊ ወንድማማቾች ነን”

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የእድሳቱ ሥራ በሁለቱ ጉባኤዎች መካከል ያለውን አንድነትና ፍቅር ይበልጥ አጠናክሮታል”

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ወንድሞች ተስማምተው በአንድነት ሲኖሩ፣ እንዴት መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!” መዝሙር 133:1

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቱኢ እና የሚንዮ ወንዝ ዙሪያዋን በግንብ ከታጠረችው ከቫሌንሳ ዶ ሚንዮ ሲታዩ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመንግሥት አዳራሹ ሲታደስ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፒረኒዝ ተራሮችና የሴርዳንያ ሸለቆ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በፕዊግሴርዳ በሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚሰበሰቡት የስፓንኛና የፈረንሳይኛ ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ሁለት ሽማግሌዎች

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ