ከታሪክ ማኅደራችን
“ቀጣዩን ትልቅ ስብሰባ የምናደርገው መቼ ይሆን?”
ሜክሲኮ ሲቲ ውስጥ ኅዳር ወር 1932 መገባደጃ አካባቢ ነው። ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ነዋሪዎች ባሉባት በዚህች ሞቅ ያለች ከተማ ውስጥ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ የትራፊክ መብራቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ የጀመሩት ገና ከአንድ ሳምንት በፊት ነበር። አሁን ግን የትራፊክ መብራቶቹ ጉዳይ ጊዜ ያለፈበት ዜና ሆኗል። የከተማይቱ ጋዜጠኞች ትኩረታቸውን በዚህ ሳምንት በሚካሄድ አንድ ክንውን ላይ አድርገዋል። በባቡር ጣቢያው ውስጥ ካሜራቸውን ደቅነው አንድ ልዩ እንግዳ የሚመጣበትን ጊዜ እየተጠባበቁ ነው፤ ይህ እንግዳ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆነው ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ ነው። በከተማዋ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮችም በዚያ በሚደረገው የሦስት ቀን ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ለሚመጣው ለወንድም ራዘርፎርድ ሞቅ ያለ አቀባበል ለማድረግ በባቡር ጣቢያው ተገኝተዋል።
ወርቃማው ዘመን የተባለው መጽሔት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በሜክሲኮ ውስጥ እውነት ወደፊት ከሚያደርገው ግስጋሴ ጋር በተያያዘ ይህ የአውራጃ ስብሰባ በታሪክ ዘመን ሁሉ እንደሚታወስ ምንም ጥያቄ የለውም።” ለመሆኑ 150 ሰዎች ብቻ የተገኙበት ይህ የአውራጃ ስብሰባ ይህን ያህል ትኩረት የሳበው ለምንድን ነው?
ከዚህ ስብሰባ በፊት የመንግሥቱ እውነት በሜክሲኮ ውስጥ ብዙም ፍሬ አላፈራም ነበር ማለት ይቻላል። አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ያቀፉ ትላልቅ ስብሰባዎች ከ1919 ጀምሮ ይደረጉ የነበረ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት የጉባኤዎች ቁጥር እየቀነሰ ሄዶ ነበር። በ1929 በሜክሲኮ ሲቲ ቅርንጫፍ ቢሮ መቋቋሙ ተስፋ ሰጪ ይመስል የነበረ ቢሆንም የተለያዩ እንቅፋቶች አጋጠሙ። የንግድ ጉዳዮችን ከስብከቱ ሥራ ጋር መቀላቀል እንደሌለበት የተነገረው አንድ ኮልፖርተር በዚህ ቅር በመሰኘቱ አገልግሎቱን ያቋረጠ ከመሆኑም ሌላ የራሱን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን መሠረተ። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የቅርንጫፍ ቢሮው የበላይ ተመልካች ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ጋር የሚጋጭ ድርጊት በመፈጸሙ በሌላ ወንድም ተተካ። በሜክሲኮ የነበሩት ታማኝ ወንድሞች መንፈሳዊ ማነቃቂያ ያስፈልጋቸው ነበር።
ወንድም ራዘርፎርድ በጉብኝቱ ወቅት በአውራጃ ስብሰባው ላይ በሰጣቸው ሁለት ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮችና በሬዲዮ ባቀረባቸው ጠንካራ መልእክት ያዘሉ አምስት ንግግሮች አማካኝነት ለእነዚህ ታማኝ ወንድሞች ከፍተኛ ማበረታቻ ሰጣቸው። የሜክሲኮ የሬዲዮ ጣቢያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ምሥራቹን በመላው አገሪቱ አሰራጩ። ከስብሰባው በኋላ፣ አዲስ የተሾመው የቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች ሥራውን ማደራጀት የጀመረ ሲሆን ቀናተኛ የሆኑ ምሥክሮች እንደ አዲስ ኃይላቸውን በማጠናከር በሥራው ወደፊት ገፉበት፤ ይሖዋም ጥረታቸውን ባርኮላቸዋል።
በ1941 በሜክሲኮ ሲቲ የተደረገ የአውራጃ ስብሰባ
በቀጣዩ ዓመት በአገሪቱ ውስጥ ሁለት የአውራጃ ስብሰባዎች ተደርገዋል፤ አንደኛው ስብሰባ የተደረገው የወደብ ከተማ በሆነችው በቬራክሩዝ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሜክሲኮ ሲቲ ነው። ወንድሞች በመስክ የሚያከናውኑት ትጋት የተሞላበት አገልግሎት ግሩም ውጤት ማስገኘት ጀመረ። በ1931 በአገሪቱ ውስጥ የነበሩት አስፋፊዎች 82 ብቻ ነበሩ። ከአሥር ዓመት በኋላ ግን የአስፋፊዎች ቁጥር በአሥር እጥፍ ጨመረ! በ1941 በሜክሲኮ ሲቲ በተደረገው ቲኦክራሲያዊ ስብሰባ ላይ 1,000 ገደማ የሚያክሉ ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር።
“አውራ ጎዳናዎቹ ተወረዋል”
ወንድሞች፣ በ1943 በ12 የሜክሲኮ ከተሞች ውስጥ የሚደረገውን “የነፃ ብሔር” ቲኦክራሲያዊ ስብሰባ ለማስተዋወቅ እርስ በርሳቸው የተያያዙ ሁለት ሰሌዳዎችን ከፊታቸውና ከኋላቸው በኩል አንግበው ይጓዙ ነበር።a የይሖዋ ምሥክሮች ከ1936 ጀምሮ ይህን የማስተዋወቂያ ዘዴ ይጠቀሙበት ነበር።
በሜክሲኮ ሲቲ ውስጥ የተደረገውን የማስታወቂያ ሰልፍ የሚያሳይ በ1944 ከታተመ መጽሔት ላይ የተቆረጠ ፎቶግራፍ
ላ ናሲዮን የተባለው መጽሔት፣ በሜክሲኮ ሲቲ ውስጥ በዚህ መንገድ ሰዎችን ለመጋበዝ የተደረገው ጥረት ስላስገኘው ስኬት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “[በስብሰባው] የመጀመሪያ ቀን፣ [ምሥክሮቹ] ተጨማሪ ሰዎችን እንዲጋብዙ ተበረታተው ነበር። በቀጣዩ ቀን ግን የስብሰባው ቦታ ሊበቃቸው አልቻለም።” ይህ የስብከት እንቅስቃሴ ያስገኘው ውጤት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን አላስደሰታትም፤ በመሆኑም በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተቃውሞ ዘመቻ ማካሄድ ጀመረች። ደፋር የነበሩት ወንድሞችና እህቶች ተቃውሞ ቢኖርም በአውራ ጎዳናዎቹ ላይ ተሰልፈው ማስተዋወቃቸውን ቀጠሉ። ላ ናሲዮን አክሎም እንዲህ ብሎ ነበር፦ “[ምሥክሮቹን] የከተማው ሰው ሁሉ ያያቸው ነበር። . . . እነዚህ ወንዶችና ሴቶች፣ ማስታወቂያ ያነገቡ ‘ሳንድዊቾች’ ሆነው ነበር።” መጽሔቱ በአውራ ጎዳናዎቹ ላይ ሰሌዳ አንግበው የሚሄዱትን ወንድሞች ፎቶግራፍ ይዞ የወጣ ሲሆን ከፎቶግራፉ ሥር “አውራ ጎዳናዎቹ ተወረዋል” የሚል ጽሑፍ ሰፍሮ ነበር።
“ከሲሚንቶ ወለል ይልቅ የሚመቹና የሚሞቁ” አልጋዎች
በዚያን ወቅት አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች በሜክሲኮ በሚደረጉት ጥቂት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ከፍተኛ መሥዋዕትነት መክፈል ያስፈልጋቸው ነበር። በርካታ ተሰብሳቢዎች የሚመጡት ባቡር ከማይደርስባቸውና የመኪና መንገድ ካልተሠራባቸው በጣም ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች ነው። አንድ ጉባኤ “በዚህ አካባቢ ያለው ብቸኛ የመገናኛ መስመር የቴሌግራፍ መስመር ብቻ ነው” በማለት ጽፏል። በመሆኑም ተሰብሳቢዎቹ የአውራጃ ስብሰባው ወደሚደረግበት ከተማ የሚወስዳቸውን ባቡር ለመያዝ በበቅሎ ወይም በእግር ለቀናት መጓዝ ነበረባቸው።
አብዛኞቹ ወንድሞች ድሆች ስለነበሩ የአውራጃ ስብሰባው ወደሚደረግበት ቦታ የአንድ ጊዜ ጉዞ እንኳ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ይቸገሩ ነበር። ስብሰባው ወደሚደረግበት ከተማ ሲደርሱ አብዛኞቹ የሚያርፉት በዚያ በሚኖሩ ወንድሞች ቤት ነበር፤ እነዚህ ወንድሞች ከሌላ አካባቢ የመጡ ወንድሞቻቸውን በእንግድነት መቀበል በጣም ያስደስታቸው ነበር። በስብሰባ አዳራሾች ውስጥ የሚያርፉ እንግዶችም ነበሩ። በአንድ ወቅት ለስብሰባ የመጡ 90 የሚያክሉ እንግዶች በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ አርፈው ነበር፤ “እያንዳንዳቸው እንደ አልጋ የተጠቀሙት አንድ ላይ ተገጣጥመው የተደረደሩ 20 የመጽሐፍ ካርቶኖችን ነበር።” በዓመት መጽሐፍ ላይ የወጣው ዘገባ፣ አመስጋኝ የሆኑት እንግዶች እነዚህን “አልጋዎች ከሲሚንቶ ወለል ይልቅ የሚመቹና የሚሞቁ” ሆነው እንዳገኟቸው ገልጿል።
አድናቂ የሆኑት እነዚህ ወንድሞች፣ አስደሳች በሆኑት በእነዚህ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ ወደ አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚጠጉት በሜክሲኮ የሚኖሩ አስፋፊዎች አሁንም ተመሳሳይ የአድናቆት ስሜት አላቸው።b የሜክሲኮ ቅርንጫፍ ቢሮ በ1949 በዚያ ያሉትን ወንድሞች አስመልክቶ ያቀረበው ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “ወንድሞች ያጋጠማቸው ተፈታታኝ ሁኔታ ለእውነት ያላቸው ቅንዓት እንዲቀዘቅዝ አላደረገም፤ ምክንያቱም ትላልቅ ስብሰባዎች በተደረጉ ቁጥር ወንድሞች ከዚያ በኋላ ለረጅም ጊዜ የሚያወሩት ስለ እነዚህ ስብሰባዎች ነው፤ ሁልጊዜ ‘ቀጣዩን ትልቅ ስብሰባ የምናደርገው መቼ ይሆን?’ እያሉ ይጠይቃሉ።” በዛሬው ጊዜ ያሉት ወንድሞች ያላቸው ስሜትም በዚህ ሪፖርት ላይ ከተገለጸው ጋር ተመሳሳይ ነው።—በማዕከላዊ አሜሪካ ካለው የታሪክ ማኅደራችን
a የ1944 የዓመት መጽሐፍ እንደገለጸው ይህ ትልቅ ስብሰባ “የይሖዋ ምሥክሮች በሜክሲኮ ውስጥ በሰፊው እንዲታወቁ አድርጓል።”
b በ2016 በሜክሲኮ 2,262,646 የሚያክሉ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተዋል።