አምላክ ሰላምና ደኅንነት ስለሚያመጣበት መንገድ ስበኩ
1 ሰዎች ሰላምና ደኅንነትን ለማምጣት ብዙ ሐሳቦችን አቅርበዋል። ይሁን እንጂ ከነዚህ ውስጥ የትኛውም ቢሆን በዓለም ዙሪያ ያሉት ሰዎች የሚያስፈልጓቸውን ዋና ዋና ነገሮች አላሟላም። የሃይማኖት፣ የዘርና የብሔር ጥላቻዎች ከፖለቲካዊ ምኞትና ከስስት ጋር ተጣምረው ዋስትና ያለውና ሰላማዊ ዓለም እንዳይመጣ የሚያግዱ ዋና ዋና መሰናክሎች ቢሆኑም እውነተኛ ክርስቲያኖች እውነተኞቹ እንቅፋቶች ሰይጣን ዲያብሎስና ሰዎች ለይሖዋ አምላክ አንገዛም ማለታቸው እንደሆነ ያውቃሉ። — መዝ. 127:1፤ ኤር. 8:9፤ 1 ዮሐ. 5:19
2 በጥር ወር ጎረቤቶቻችን ብቸኛው የሰላምና የደኅንነት መንገድ የአምላክ መንገድ መሆኑንና ለሰው ዘር ችግሮች ሁሉ የመጨረሻው መፍትሔ ይሖዋ መሆኑን እንዲያስተውሉ ለመርዳት እንጥራለን።
3 በአዳዲስ ትራክቶች ተጠቀሙ፦ ይህን ገንቢ መልእክት “ብርሃን አብሪዎች” በተባለው የወረዳ ስብሰባችን ላይ በወጡት አዳዲስ ትራክቶች በመጠቀም ልናካፍል እንችላለን። ይህ ዓለም ከመጥፋት ይተርፍ ይሆንን? በተባለው ትራክት ቁጥር 19 ተጠቅመን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚያመራ ውይይት እንዴት ለመጀመር እንደምንችል በአንድ ቀለል ያለ ትዕይንት አይተናል። ስለዚህ ዓለም መጨረሻ የተነገረው የኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜ መታየቱ የብዙዎችን ትኩረት ሊስብ ይገባል።
4 በዛሬው ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የመንፈስ ጭንቀት አለባቸው። ፈውስ፣ እውነተኛ ሰላም፣ ደኅንነት እንዲሁም የተረጋጋ ሁኔታ የሚመጣበትን ጊዜ ይናፍቃሉ። ለተጨነቁት የሚሆን መጽናኛ (ትራክት ቁጥር 20) ለብዙዎች እውነተኛ የማበረታቻ ምንጭ ሊሆንላቸው ይችል ይሆናል።
5 በቤተሰብ ኑሮ ተደሰት የተባለው ትራክት ቁጥር 21 የአምላክን የወደፊት ግሩም የሆነ አዲስ ዓለም እየተጠባበቅን በምንገኝበት በአሁኑ ጊዜም እንኳን የቤተሰብን ኑሮ ለማሻሻል ምን ሊደረግ እንደሚቻል ተግባራዊ የሆነ ምክር ይሰጠናል።
6 ትራክት ቁጥር 22 በእርግጥ ዓለምን የሚገዛው ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ይሰጣል። የብዙ ሰዎች ፍላጎት ሰላማዊና ዋስትና ያለው ሕይወት ሆኖ ሳለ ሰዎች እርስ በእርሳቸው አሰቃቂ በሆነ መንገድ ለምን እንደሚተራረዱና አንዱ ሌላውን የሚያሰቃየው ለምን እንደሆነ ያብራራል። በሰማያዊ ሥፍራ ክፉ የሆኑ መንፈሳዊ ኃይላት አሉ፤ የሰይጣን እጅግ መሠሪ የሆነ ማታለያም ብዙ ሰዎች እሱና አጋንንቱ በእውን እንደሌሉ እንዲያምኑ አድርጎ ማሳወር ነው።
7 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን አስጀምሩ፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በትራክት፣ በብሮሹር፣ በመጽሔት ወይም በመጽሐፍ በመጠቀም ሊጀመር ይችላል። የቤቱ ባለቤት ከጽሑፎቻችን አንዱ ያለው መሆኑን ካወቃችሁ በእርሱ አማካይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት ሊካሄድ እንደሚችል በዘዴ አሳዩት። አዲሶቹ ትራክቶችና አምላክ በእርግጥ ያስብልናልን? የተባለው አዲስ ብሮሹር የቤቱን ባለቤት ፍላጎት መጠን ለማወቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚጠቅሙ በጣም ጥሩ መሣሪያዎች ናቸው። በተጨማሪም ሰዎች ለእውነት ፍላጎት ሲያሳዩ በ1980 ወይም ከዚያ በፊት የታተሙ የማኅበሩ መጻሕፍት በመስክ አገልግሎት ሊበረከቱ ይችላሉ። ጉባኤያችሁ የቤተሰብ ኑሮ፣ “መንግሥትህ ትምጣ፣” እውነት ወይም ወጣትነትህ የተባሉት መጻሕፍት ካሉት በአገልግሎት በጥሩ ሁኔታ ልትጠቀሙባቸው እንድትችሉ እቅድ አውጡ።
8 እውነተኛ ደኅንነት ሊመጣ የሚችለው ከፈጣሪያችን ከይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። ብዙ ሰዎች ልባቸውንና አእምሮአቸውን ለአምላክ ቃል እውነት እንዲከፍቱና እኛ ያለንን ተስፋ አጥብቀው እንዲይዙ የቻልነውን ያህል ልንረዳቸው እንፈልጋለን። ያሉንን የማስተማሪያ መሣሪያዎች የአምላክን የሰላምና የደኅንነት መንገድ ለመስበክ በጥሩ ሁኔታ እንጠቀምባቸው። — ኢሳ. 2:3, 4