በጣም አስፈላጊ በሆኑት መሣሪያዎች በጥበብ መጠቀም
1 ከቤት ወደ ቤት በምትመሰክርበት ጊዜ ግብህ እያንዳንዱ የቤት ባለቤት መጽሐፍ ቅዱስን ወይም ሌሎች በጣም አስፈላጊ የሆኑ መሣሪያዎችን በመጠቀም በምታደርገው ጠቃሚ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት ውስጥ እንዲገባ ማድረግ መሆን ይኖርበታል። (ከ2 ቆሮንቶስ 6:1ና ከ2 ጢሞቴዎስ 2:15 ጋር አወዳድር።) በአሁኑ ጊዜ በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ያሳሰባቸው ነገር ምንድን ነው? ስለ ኢኮኖሚው ሁኔታና እያሽቆለቆለ ስለመጣው የቤተሰብ ኑሮ ተጨንቀዋልን? ከእነዚህ ርእሶች በአንዱ ላይ የቀረበ አጠር ያለ የመግቢያ ሀሳብ ጥሩ ወደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ይመራ ይሆናል።
2 እንዲህ ለማለት ትችላለህ፦
“በነዚህ ፈታኝ ጊዜያት ብዙ ሰዎች የኑሮ ወጪዎቻቸውን መሸፈን አስቸጋሪ ሆኖ አግኝተውታል። ገንዘብ ነክ ችግሮቻችን ለሁሉም ሰው ተስማሚ በሆነ መንገድ ይቃለሉልን ይሆናል ብለው ያስባሉን? [የሚሰጠውን መልስ አዳምጥ።] ይህን ሀሳብ በግሌ በጣም የሚያበረታታ ሆኖ አግኝቼዋለሁ . . .”
3 ከዚያም መዝሙር 72:12–14ን ልታነብና ምክንያቱን ማስረዳት ከተባለው መጽሐፍ ውስጥ ገጽ 228–229 ካሉት ጥቅሶች ውስጥ ተጨማሪ ጥቅስ በመምረጥ ውይይቱን ልታጠቃልል ትችላለህ። ወይም አንድ ጥቅስ ካነበብክ በኋላ ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሕይወት ከተባለው ትራክት ውስጥ አንድ አንቀጽ ልታሳየውና ልታነብለት ትችላለህ። ወጣቶችን ጨምሮ ብዙ አስፋፊዎች በአንዱ ትራክት ተጠቅመው አንድ አንቀጽ በማንበብና የቤቱ ባለቤት በተነበበው ነገር ላይ ያለውን አስተያየት በመጠየቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በተሳካ ሁኔታ እየጀመሩ ናቸው።
4 በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን አቀራረብ ለመጠቀም ትመርጥ ይሆናል፦
“ብዙ ሰዎች ባሕላዊው የቤተሰብ አያያዝና አመለካከት ተመልሶ ቢመጣ ደስ ይላቸዋል። እነዚያ አመለካከቶች ምን መሆን እንዳለባቸው መወሰኑ የእያንዳንዱ ሰው ጉዳይ ነው ወይስ ለእያንዳንዱ ሰው የሚሆን አንድ የአቋም ደረጃ ሊኖር ይገባል ብለው ያስባሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ጥበብ ያለበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ብንከተል ኖሮ በቤተሰብ የኑሮ ሁኔታ ላይ ጎላ ያለ መሻሻል ሊኖር ይችል እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ።”
5 በዚህ ነጥብ ላይ በቆላስይስ 3:12–14 ላይ ያለውን የሐዋርያውን አባባል አስተዋውቀህ ልታብራራ ትችላለህ። ወይም በቤተሰብ ኑሮ ተደሰት በተባለው ትራክት ውስጥ “መልካም ውጤት የሚያስገኘው የትኛው መንገድ ነው?” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ባለው ሀሳብ በመጠቀም በመጀመሪያ ጉብኝትህ ላይ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ጥረት አድርግ።
6 የቤቱ ባለቤት ፍላጎት ካሳየ በወሩ ውስጥ ከምታበረክታቸው ባለ 192 ገጽ የማኅበሩ መጻሕፍት መካከል የአንዱን ጠቃሚነት አሳየው። መጽሐፉን ለመውሰድ ካልፈለገ እንደ ትራክት፣ መጽሔት ወይም ብሮሹር ባሉት እጅግ ጠቃሚ በሆኑት ጽሑፎች ውስጥ ያሉትን ተስማሚ ነጥቦች በማካፈል በጥበብ ለመጠቀም ንቁ ሁን።
7 በመጀመሪያ ጉብኝትህ ላይ ጥናት ለማስጀመር ከቻልክ ውይይቱን ለመቀጠል በየትኛው ቀን እንደምትመጣ ቁርጥ ያለ ቀጠሮ ውሰድ። “አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ?” የሚለውን ብዙውን ጊዜ የሚጠየቅ ጥያቄ ለመመለስ ተመልሰህ እንደምትመጣ ለቤቱ ባለቤት በመንገር ለሚቀጥለው ጉብኝትህ መሠረት ለመጣል ትችላለህ። ከዚህ በታች ያለው ርዕሰ ትምህርት በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት ርዕሰ ጉዳዩን እንዴት ማብራራት እንደሚቻል ሀሳብ ይሰጣል።