ጤናማ አስተሳሰብ ይዞ በጽድቅ መኖር
1 የምንኖረው ኃጢአት እንድንሠራ የሚገፋፋ ከፍተኛ ተጽዕኖ በሚያሳድር ዓለም ውስጥ ነው። የዚህ ሥርዓት የአቋም ደረጃዎች እየተበላሹ መሄዳቸውን ቀጥለዋል። (2 ጢሞ. 3:3) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ትክክለኛ የሆኑ ነገሮችን መደገፍ ይኖርብናል፤ እንዲሁም ትክክለኛ የሆኑ ነገሮችን ማድረጋችንን መቀጠል የሚገባን ለምን እንደሆነ መረዳት አለብን። ነገር ግን ምን ዓይነት አመራርና መመሪያ ልናገኝ እንችላለን? ምን ዓይነት የአቋም ደረጃዎችንስ መከተል ይኖርብናል? በ1993 የአገልግሎት ዓመት ለሚኖረን የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም የተመረጠው የሚያበረታታ አጠቃላይ መልዕክት “ጤናማ አስተሳሰብ ይዞ በጽድቅ መኖር” የሚል ነው። — ቲቶ 2:12
2 ኃጢአተኝነትን ለመቋቋምና ዓለማዊ ምኞቶችን ለማስወገድ እንችል ዘንድ ራሳችንን እንዴት ልናጠነክር እንደምንችል በንግግሮች፣ በትዕይንቶችና በተሞክሮዎች አማካኝነት እንማራለን። በተጨማሪም በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ ትክክለኛ አስተሳሰብ ይዞ በጽድቅ መኖር እንዴት እንደሚቻል እናያለን። የማሰብ ኃይላችንን ለመጠበቅ እንድንችል እኛን ለመርዳት የተደረጉልን ዝግጅቶች ይዘረዘራሉ። (1 ጴጥ. 4:7) በተለይ ወላጆችና ወጣቶች በከሰዓት በኋላው ፕሮግራም ላይ የሚኖሩትን ንግግሮችና ቃለ ምልልሶች ትኩረት ሰጥተው ሊከታተሏቸው ይገባል። እነዚህ ንግግሮችና ቃለ ምልልሶች አምላካዊ ጥበብና ልምድ የማግኘትንና አስደሳች ለሆነ ቲኦክራቲካዊ የወደፊት ሕይወት መሠረት ለመጣል ተባብሮ የመሥራትን አስፈላጊነት አጥብቀው ይገልጻሉ።
3 ኃጢአተኛ በሆነ ዓለም ብንከበብም የአምላክ ቃል ልንከተለው የሚገባንን ከሁሉ የተሻለ መንገድ ያስተምረናል። “ደስታ ባጣ ዓለም ውስጥ ያገኛችኋቸውን በረከቶች በእንክብካቤ ጠብቁ” የሚል ርዕስ ያለው ንግግር የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች በጥንቃቄ መከተል የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች አጉልቶ ይገልጻል። ስብሰባውን ለመካፈል በምንዘጋጅበት ጊዜ ለፕሮግራሙ ትኩረት ሰጥተን መከታተልና ምክሮቹን በሥራ ላይ ማዋል ለይሖዋ በምናቀርበው አገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን እንደሚያስችለን በአእምሮአችን መያዝ አለብን። — ፊል. 3:15, 16