ሌሎች ሰዎች ስለ ታላቁ ሰው እንዲማሩ እርዷቸው
1 እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለውን መጽሐፍ ያነበቡ ብዙ ሰዎች መጽሐፉ አኗኗራቸውን የነካው በመሆኑ ያላቸውን ልባዊ አድናቆት ገልጸዋል። አንድ ሰው እንዲህ ሲል ጽፏል:- “መጽሐፉን አንብቤ ስጨርስ ኢየሱስ አብሬው እንድሆን፣ በአጠገቡ እንድኖር፣ መከራውና ስሜቱ እንድጋራው እንዲሁም በእያንዳንዱ የአገልግሎቱ ዘርፍ እንድካፈል ጋብዞኝ እንደነበረ ተሰማኝ። . . . መጽሐፉን ማንበብ ስለ ኢየሱስ አኗኗር የሚያሳይ ፊልም እንደመመልከት ያህል ነው።”
2 ታላቁ ሰው የተባለው መጽሐፍ ከኢየሱስ ጋር ብቻ ሳይሆን ከይሖዋም ጋር በተሻለ ሁኔታ እንድንተዋወቅ ይረዳናል። (ዮሐ. 14:9) አንድ የ12 ዓመት ልጅ መጽሐፉን በተመለከተ እንዲህ ብሏል:- “መጽሐፉ በጣም ስላጽናናኝ አንብቤው እንደጨረስኩ የደስታ እምባ እያነባሁ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። ይሖዋና ኢየሱስ እንደሚንከባከቡን ማወቄ በውስጤ የመተማመን ስሜት እንዲሰማኝ አድርጎኛል።” በዮሐንስ 17:3 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ይሖዋንና ልጁን ማወቃችን የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝልን ኢየሱስ ተናግሯል። ስለ ኢየሱስ ሕይወት የሚተርከውን ይህን መጽሐፍ ማጥናታችን የይሖዋን ባሕርይ በጥልቀት እንድናስተውል ያስችለናል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “ትክክለኛው የባሕርዩ ምሳሌ” ነው። — ዕብ. 1:3 አዓት
3 ታላቁ ሰው የተባለው መጽሐፍ ከ70 በሚበልጡ ቋንቋዎች ከ19 ሚልዮን ቅጂዎች በላይ ታትሟል። ይህም መጽሐፉ ምን ያህል ተቀባይነት እንዳገኘ የሚያሳይ ነው። ብዙ ሰዎች መጽሐፉ እንደደረሳቸው ሙሉውን አንብበው ጨርሰውታል። አንድ ፍላጎት ያሳየ ሰው መጽሐፉን ባገኘ በሁለት ሳምንት ውስጥ ከዳር እስከ ዳር አንብቦታል። መጽሐፉን የወሰዱ አንድ ቄስ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “መጽሐፉን ማስቀመጥ አልቻልኩም። እኔና ባለቤቴ ከመተኛታችን በፊት ሁልጊዜ ማታ ማታ የተወሰኑ ገጾች እናነባለን።”
4 መደበኛ ያልሆነ ምስክርነት፦ አንድ ወንድም ታላቁ ሰው የተባለውን መጽሐፍ በመሥሪያ ቤቱ ለሚገኙ ሰዎች አሳያቸው። ወንድም ይህ መጽሐፍ እንዳለውና መጽሐፉ ስለያዛቸው ነገሮች የሚገልጽ ወሬ በአካባቢው ተሰራጨ። የሥራ ባልደረቦቹ የመጽሐፉን ቅጂ የሚፈልጉ ሰዎችን ስም ዝርዝር አመጡ። ወንድም 461 መጽሐፎች አበረከተ! መጽሐፉን ከወሰዱት ሰዎች መካከል አምስቱ እያጠኑ ነው። አንዲት እህት በአውሮፕላን ስትጓዝ አዲስ ካርዲናል በሚሾምበት በዓል ላይ ለመገኘት ይሄዱ ለነበሩ ቄስ ታላቁ ሰው የተባለውን መጽሐፍ አበርክታለች። ቄሱ ለ40 ዓመታት በቫቲካን ውስጥ ያገለገሉ ነበሩ። ሁላችንም ባሉን አጋጣሚዎች ሁሉ ሌሎች ሰዎች መጽሐፉን እንዲያነቡት ማበረታታት ይገባናል።
5 ወጣቶች መጽሐፉን ይወዱታል፦ ወ ጣቶች ለመጽሐፉ ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው። አንድ የዘጠኝ ዓመት ልጅ እንዲህ ብሎ ጽፏል:- “በጣም የምወደው መጽሐፍ እስከ ዛሬ ድረስ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለውን ነው፤ ምክንያቱም ከመጽሐፉ ብዙ ትምህርት አግኝቻለሁ።” በመስክ አገልግሎት ላይ ወጣቶችን ስናገኝ ወላጆቻቸው ከፈቀዱ ጊዜ ወስደን ለእነዚህ ልጆች መጽሐፉን ማሳየትና ጎላ ጎላ ያሉትን ነጥቦችና ሥዕሎቹን እንዲመለከቱ ማድረግ ይገባናል። ለእነዚህ ወጣቶች መጽሐፉን ለማበርከት እንችል ይሆናል። በአሁኑ ጊዜ ያሉ ወጣቶች ስለ ኢየሱስ የማወቅ አጋጣሚ ካገኙ ወደ እርሱ ሊቀርቡ ይችላሉ። ኢየሱስ በቀላሉ የሚቀረብ ሰው ነበር። — ማቴ. 19:14, 15
6 ታላቁ ሰው የተባለውን መጽሐፍ ማንበብ የሰዎችን አኗኗር ሊለውጥ ይችላል። የመጽሐፉን ይዘት የተቻላችሁን ያህል ለብዙ ሰዎች ለማስተዋወቅ ጥረት አድርጉ። በመጽሐፉ መግቢያ የመጨረሻ ገጽ ላይ “ስለ እርሱ በመማር ጥቅም አግኝ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ያለውን ትምህርት ተጠቀሙበት። ይህ ትምህርት ሰዎች መጽሐፉን በማንበብ ማግኘት በሚችሉት ነገር ላይ እንዲያተኩሩ ይረዳቸዋል። አንድ ሰው መጽሐፉን ካነበ በኋላ “እስከ ዛሬ ድረስ ካነበብኳቸው መጽሐፎች ሁሉ የሚበልጥ መጽሐፍ ነው! ሕይወቴን ለውጦታል” ብሎ በአድናቆት እንደተናገረው ሁሉ በክልላችሁ ውስጥ የሚገኙ ብዙ ሰዎችም እንዲሁ ይናገሩ ይሆናል።