አዲሱ መጽሐፍ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አስደስቷል
ባለፈው ሰኔ በተጀመረው የ“ነፃነት አፍቃሪዎች” ተከታታይ ስብሰባ ላይ ከቀረቡት ንግግሮች አንዱ “እስከዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው” በሚል ርዕስ የቀረበው ነበር። ለዚህ ንግግር ልዩ ድምቀት የሰጠው በንግግሩ መጨረሻ ላይ በዚሁ ርዕስ የተዘጋጀ አዲስ መጽሐፍ መውጣቱ ነበር። በዓለም ዙሪያ እነዚህን ተከታታይ ስብሰባዎች የተካፈሉ ከስድስት ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በዚህ መጽሔት ባለፉት ሁለት ርዕሰ ትምህርቶች ላይ ትንሽ ለውጥ ተደርጐ የቀረበውን ይህን ንግግር አዳምጠዋል።
እስከዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው የተሰኘው መጽሐፍ 60 በሚያህሉ ቋንቋዎች ከ12 ሚልዮን በሚበልጡ ቅጂዎች ታትሟል። የምሥራቅ አውሮፓ ቋንቋዎች በሆኑት በአልባኒያኛ፣ በክሮሺያኛ፣ በሀንጋሪያኛ፣ በመቄዶንያኛ፣ በፖላንድኛ፣ በሩሲያኛ፣ በሰርቢያኛና በእስሎቬንያኛ እንኳ ሳይቀር ተዘጋጅቷል። በተለይ በሶቪየት ኅብረት ውስጥ በተደረጉት ሰባት ስብሰባዎች ላይ የተገኙት ከ74,000 በላይ የሆኑ ተሰብሳቢዎች ይህን መጽሐፍ በሩሲያኛ ቋንቋ ሲያገኙ በጣም ተደስተዋል።
የመጽሐፉ ሐሳብ የተውጣጣው ከየት ነው?
በመጽሐፉ ውስጥ ያሉት ታሪኮች ከሚያዝያ 1, 1985 ጀምሮ በ149 የመጠበቂያ ግንብ ተከታታይ እትሞች ላይ በተከታታይ ሲወጡ የቆዩ ናቸው። ተከታታይ ታሪኮቹ በሰኔ 1, 1991 ዕትም ሲያበቁ ብዙ አንባቢዎች እንዳዘኑ ተናግረዋል። በኢጣልያ የምትኖረው መሊሳ የምትባል የ12 ዓመት ወጣት የመጨረሻውን ታሪክ በመጠበቂያ ግንብ ላይ ስታነብ ዓይኖችዋ እንባ አቅርረው ነበር። ይህች ልጅ “ከትልቁ ስብሰባችን በፊት በነበረው ምሽት ይሖዋ ስለ ኢየሱስ ሕይወት የሚገልጽ መጽሐፍ እንዲዘጋጅ እንዲያደርግ ጸልዬ ነበር። መጽሐፉ ሲወጣ እጄን እስኪያመኝ ድረስ አጨበጨብኩ” ብላለች።
በመጠበቂያ ግንብ ላይ በተከታታይ የወጣው ትረካ 133 ምዕራፎችና ሥዕሎች ባሉት በባለ 448 ገጽ መጽሐፍ ላይ ተጠቃሎ ወጥቷል። በመጽሐፉ ውስጥ ኢየሱስ ያደረጋቸው ንግግሮች በሙሉና በምድራዊ ሕይወቱ ጊዜ ያጋጠሙትን ሁኔታዎች በሙሉ፣ ምሳሌዎቹንና ተአምራቱን በሙሉ ለማቅረብ ጥረት ተደርጎአል። በተቻለ መጠን እያንዳንዱ ትረካ የቀረበው ነገሩ በተፈጸመበት ቅደም ተከተል መሠረት ነው። በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ ምዕራፉ የተመሠረተባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ተዘርዝረዋል።
አንድ ሰው ‘ተከታታይ ታሪኮቹን በመጠበቂያ ግንብ ላይ ስላነበብኩ መጽሐፉን አንብቤዋለሁ ማለት ነው’ ብሎ ያስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ የመጠበቂያ ግንብ አንባቢዎች የኢየሱስን ሕይወት ታሪክ ያነበቡት ከስድስት ዓመት በላይ በሆነ የጊዜ ርዝማኔ ውስጥ በየሁለት ሣምንቱ በሚወጣ ዕትም ላይ ተቆራርጦ ሲወጣ የቆየውን ነው። ርዕሰ ትምህርቶቹ በተከታታይ ሲወጡ በነበሩበት ጊዜም ቢሆን አስፈላጊውን ትምህርት ይሰጡ የነበሩ ቢሆንም ጠቅላላውን ታሪክ በአጭር ጊዜ ማንበብና እስከዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ስለሚበልጠው ታላቅ ሰው የተሟላ መግለጫ ለማግኘት መቻል በቀላሉ የሚገመት ነገር አይደለም።
እምነትን ያጠነክራል
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በዋሽንግተን ዲ ሲ የምትኖር አንዲት ሴት “ጽሑፉን በሁለት ሳምንት ውስጥ አንብቤ ጨረስኩ። በማነብበት ጊዜ ዓይኖቼ እንባ ያቀርሩ ነበር። ማንበቡን አቁሜ እጸልይና አለቅስ ነበር። መጽሐፉ ከኢየሱስ ጋር ሆኜ አብሬው ሥቃዩን እንደምቀበል ሆኖ እንዲሰማኝ አድርጎኛል። መጽሐፉን አንብቤ ከጨረስኩ ከአንድ ሳምንት በኋላ እንኳ ሳይቀር ስላነበብኩት ነገር ሳስብ እንባዬ ይመጣ ነበር። ይሖዋ ልጁን ስለሰጠን ወደእሱ ይበልጥ እንደቀረብኩ ሆኖ ይሰማኛል” በማለት ገልጻለች።
አንዲት በዩናይትድ ስቴትስ ፒትስበርግ ፔንሲልቫንያ የምትኖር ሴት ደግሞ “ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን መጽሐፍ ዛሬ አንብቤ ጨረስኩ። በጣም ግሩም ነበር። የመጨረሻዎቹን ምዕራፎች በማነብበት ጊዜ ዓይኖቼ እንባ ያቀርሩ ነበር። መጽሐፉን በአንድ ጊዜ አንብቦ መጨረስ በጣም ጥሩ ነው። ስለ መጽሐፉ የሚሰማኝን በቃላት ልገልጽ አልችልም። በጣም ወድጄዋለሁ ከማለት በስተቀር ምንም ለማለት አልችልም” ስትል ጽፋለች።
በመጽሐፉ ውስጥ ያሉት ያማሩ ሥዕላዊ መግለጫዎች ለታሪኩ ተጨማሪ ኃይል ይሰጣሉ። አንድ አድናቂ አንባቢ እንደገለጸው ነው፦ “ለሞተችው ልጃቸው ሲያለቅሱ እንደምሰማቸው ሆኖ እንዲሰማኝ አድርጐኛል (ምዕራፍ 47) ወይም ደም ይፈሳት የነበረችው ሴት ኢየሱስን ዳስሳ ስትድን ኢየሱስ ምን እንደተሰማው እንዳወቅን ሆኖ እንዲሰማን ያደርጋል። (ምዕራፍ 46) በሥዕላዊ መግለጫው ላይ ያሉት ሰዎች ፊት በጣም እውን ከመምሰሉ የተነሣ ስሜት ይነካል። . . . ይህን መጽሐፍ ማንበብ አሰልቺ ሥራ ሳይሆን ይበልጥ የመዝናኛ ዓይነት እንዲሆንልኝ ወይም በቀኑ አጻጻፍ ኢየሱስ ምን እንዳደረገ ብቻ ሳይሆን ምን እንዳሰበና እንደተሰማው ፍንጭ ይሰጠናል።
የተለያዩ ጥቅሞች አሉት
ብዙዎቹ መጽሐፉን በቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ሊጠቀሙበት ጀምረዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ሲልቨርቶን ኦሬገን የሚኖሩ ወላጆች ሲጽፉ “ሦስት ወጣት ልጆች አሉን። ይህ መጽሐፍ ‘በየቀኑ ማታ ማታ ለምናደርገው የቤተሰብ ጥናት’ እጅግ በጣም ጥሩ ሆኖልናል። በእርግጥም አፍቃሪ ንጉሣችን የሆነውን የክርስቶስ ኢየሱስን የጥንት ታሪክ በጥንቃቄ ማጥናታችን ተገቢ ነው” ብለዋል።
አንድ በጃፓን አገር የሚኖር ወጣት ደግሞ እንዲህ በማለት ገልጿል፦ “ሁልጊዜ ከራት በኋላ በምንዝናናበት ጊዜ አባቴ መጽሐፉን ሲያነብልን ቆይቷል። አንድ ላይ ሆነን በቤተሰብ ደረጃ ከመጀመሪያው ጀምሮ እያነበብነው ቢሆንም ማታ ማታ ከመተኛቴ በፊት ከመጽሐፉ መጨረሻ ጀምሬ አንዳንድ ምዕራፍ ለማንበብ ወሰንኩ። ይሁን እንጂ መጽሐፉ በጣም የሚመስጥ ከመሆኑ የተነሣ ጊዜው ማለፉ ሳይታወቀኝ እስከ ሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሳነብ እቆያለሁ።”
በትረካዎቹ ውስጥ ብዙ ዝርዝር ጉዳዮች በመገለጻቸው ብዙዎቹ ተገርመዋል። አንድ ምሥክር “የማላውቃቸውን ብዙ ነገሮች ተማርኩ” በማለት ጽፏል። ከካሊፎርኒያ ዩናይትድ ስቴትስ የመጣ ደብዳቤ ደግሞ “ሚስቴና እኔ ከ35 ዓመት በላይ በእውነት ውስጥ ቆይተናል። ይህን ያህል በጣም ስሜት የሚነካ መጽሐፍ በእጃችን ገብቶ አያውቅም ብለን በሐቀኝነት ልንናገር እንችላለን” በማለት ገልጿል።
መጽሐፉ የይሖዋ ምስክሮች በኢየሱስ አያምኑም የሚለውን ውሸት ውድቅ ለማድረግ ይረዳል። አንድ አመስጋኝ አንባቢ “መጽሐፉ የይሖዋ ሕዝቦች በኢየሱስ ክርስቶስ አያምኑም ወይም ደግሞ አያከብሩትም የሚሉትን ሰዎች አለማወቅ የሚያጋልጥ በመሆኑ ማንበቤን ለማቋረጥ ወይም መጽሐፉን ለማስቀመጥ አልቻልኩም። አሁን ማድረግ የሚያስፈልገን ይህ ላለማወቃቸው ጥሩ ምላሽ የሚሰጠው መጽሐፍ እጃቸው እንዲገባ ማድረግ ብቻ ነው” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።
በእርግጥ ይህ መጽሐፍ ለይሖዋ ምስክሮች አገልግሎት ጠቃሚ ድርሻ ያበረክታል። አንዲት ምስክር “መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት አንዲት ሴት ይህን መጽሐፍ ሰጠኋት። በእሷ ላይ ያመጣው ውጤት ተአምር ይመስላል። ለአንድ ዓመት ያህል ስታጠና ከቆየች በኋላ እንኳ ወደ ስብሰባ አልመጣም ብላ አስቸግራኝ ነበር” በማለት ጻፈች። ተማሪዋ ከአዲሱ መጽሐፍ 45 ምዕራፎች ካነበበች በኋላ “አቋም መውሰድ እንዳለባት ስለተሰማት እሁድ በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንደምትገኝ ነገረችኝ” በማለት ምስክሯ ገልጻለች።
ጠቃሚ ገጽታዎች
እስከዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው የተባለው መጽሐፍ ወንጌሎችን የሚያብራራ መጽሐፍ ነው ሊባል ይችላል። ኢየሱስ ስለተናገራቸውና ስላስተማራቸው ስለ ብዙዎቹ ነገሮች ማብራሪያዎች ስለቀረቡና መጽሐፉም የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ አጥብቆ ስለሚከተል እንደ ጠቃሚ የምርምር መሣሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።
በተለይ በጣም ጥሩ የሆነ ገጽታው እያንዳንዱ ክንውን የተተረከው የአፈጻጸሙን የጊዜ ቅደም ተከተል ጠብቆ መሆኑ ነው። ስለዚህ መጽሐፉን በማገላበጥ ብቻ እንኳ አንዳንድ ሁኔታዎች የተፈጸሙት በኢየሱስ አገልግሎት ሂደት ውስጥ በየትኛው ጊዜ እንደሆነ ለመገንዘብ እንደሚያስችል መረዳት ይቻላል። ወንጌሎችን የሚያነቡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የሚጋጩ የሚመስሉ ነገሮች ያጋጥሟቸዋል። አዲሱ መጽሐፍ በእነዚህ የሚጋጩ በሚመስሉ ነገሮች ላይ ልዩ ትኩረት ሳያደርግ በአቀራረቡ ብቻ የሚጋጩ የሚመስሉትን ነገሮች አስማምቷቸዋል።
ክርስቲያኖች በመሆናችን የታማኙን ምሳሌያችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት በጥንቃቄ ከማጥናት ችላ ለማለት መፈለግ የለብንም። ስለዚህ እስከዛሬ ድረስ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው በተሰኘው መጽሐፍ ረዳትነት የወንጌሎችን ትረካ ቀረብ ብለን እንመርምር።