የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለመፈለግ ቆርጠህ ተነሳ
1 ይህ አሮጌ ዓለም ጊዜው እያለቀበት እንደሆነ የሚያሳዩት ማስረጃዎች እየጨመሩ ሄደዋል። (2 ጢሞ. 3:1–5) ይህ ምን ማለት ነው? የሰው ሕይወት በቋፍ ላይ ነው ማለት ነው። ይሁን እንጂ አንዳንዶች እንዲድኑ መርዳት እንችላለን። (ምሳሌ 3:27) ለዚህ ስንል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለማስጀመርና ለመምራት አጥብቀን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
2 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱት ጽሑፎቻችን በመሠራጨታቸው ምክንያት ብዙ ለመሥራት ተችሏል። ሆኖም ሰዎች ይበልጥ የሚያስፈልጋቸው ነገር ቋሚ በሆነ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት የግል እርዳታ ማግኘት ነው። ይህ እንዲታያቸው ለመርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
3 ብዙ ሰዎችን የሚያሳስቡ ጥያቄዎችን ልናነሳ እንችላለን። የምናነሳቸው ጥያቄዎች ሥነ ምግባር ከፍተኛ ውድቀት የደረሰበት ለምን እንደሆነ፣ የቤተሰብ ኑሮ ያልተረጋጋ የሆነበትን ምክንያት፣ ዓመፅና ወንጀል ይህን ያህል አስጊ ደረጃ ላይ የደረሱበትን ምክንያት፣ አፍቃሪ የሆነው አምላክ በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት ሁኔታዎች እንዲኖሩ የፈቀደበትን ምክንያትና የመሳሰሉትን ነገሮች የሚመለከቱ ሊሆኑ ይችላሉ። በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሊስቡ የሚችሉ ጉዳዮችንና የተፈጸሙ ሁኔታዎችን በንቃት ተከታተል። መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን ግለጽ መልስ አሳያቸው። የምናሠራጨው ጽሑፍ ስለነዚህና ሁላችንንም ስለሚነኩ ስለ ሌሎች ታላላቅ ጉዳዮች መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለመማር እንዴት እንደሚረዳቸው አሳያቸው።
4 የቤቱ ባለቤት በውይይቱ ውስጥ እንዲገባ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። የቤቱን ባለቤት የሚያሳስበው ነገር ምን እንደሆነ ለማስተዋል ንቁ ሁን። ውይይታችሁ እርሱ ለማወቅ በሚፈልጋቸው ወይም በሚያስጨንቁት ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር አድርግ። ሰውየው መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ዘር ችግሮች የሚሰጠውን መፍትሔ በሚያብራራ በአንድ መጽሐፍ፣ ብሮሹር፣ መጽሔት ወይም ትራክት ውስጥ በሚገኝ ሐሳብ ላይ እንዲያተኩር ልታደርገው ትችላለህ። ከመሄድህ በፊት ቀጥለህ የምትመጣበትን ጊዜ በጉጉት እንዲጠባበቅ ያደርገዋል ብለህ የምታምንበትን አንድ ወይም ሁለት ጥያቄዎች ልታነሳለት ትችላለህ። ተመልሰህ ስትሄድ እነዚህን ጥያቄዎች አስታውሰው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ እንዲያውቅ ለማድረግ ስትረዳው ቀደም ሲል በተውክለት ጽሑፍ ተጠቀም።
5 ጥናት ማስጀመራችንና ቋሚ በሆነ ሁኔታ ጥናቱን መምራታችን የሰዎችን ሕይወት ሊለውጥ ይችላል። በመስክም ሆነ መደበኛ ባልሆኑ አጋጣሚዎች የምናገኛቸው ሰዎች ስለሚያሳስቧቸው ጉዳዮች በእውነት እንደምናስብ ልናሳያቸው ያስፈልጋል። ፍላጎታቸው ቀስ በቀስ እያደገ እንዲሄድ ለማድረግ ጥሩ ዝግጅት ይጠይቃል። መንፈሳዊውን ምግብ ቋሚ በሆነ መልኩ ልንመግባቸው እስክንችል ድረስ እየተመላለሱ መጠየቁ ትዕግሥት ይጠይቃል። ሰዎቹን ራሳቸውን መውደድም ይጠይቃል። በማንዣበብ ላይ ካለው ጥፋት እንዲድኑ ለመርዳት ልባዊ ፍላጎት ሊኖረን ይገባል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማስጠናቱ ሥራችን ዘወትር አጥብቀን ልንጸልይለት የሚያስፈልገው ጉዳይ መሆን ይኖርበታል። — 1 ተሰ. 5:17
6 ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች ተጠምቀው ደቀ መዛሙርት ሆነው ማየቱ በጣም የሚያበረታታ ነው። (ማቴ. 28:19, 20) በአሁኑ ጊዜ በየወሩ አራት ሚልዮን ተኩል የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራት ላይ እንገኛለን። ይህም ስለ ሌሎች ሕይወት ያለንን አሳቢነት ያሳያል። አንተስ? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጠናቱ ሥራ ለመካፈል ልባዊ ጥረት እያደረግህ ነህን? የራሳችንም ሆነ የሌሎች ሕይወት ማግኘት የተመካው እኛ በዚህ ረገድ በምናሳየው ትጋት ነው። — ሕዝ. 3:17–19