አዲስም ሆነ ልምድ ካለው አገልጋይ የሚፈለጉ ብቃቶች
1 መዝሙራዊው ዳዊት “አቤቱ፣ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል?” በማለት ጠይቆ ነበር። ዳዊት ጥቂትና ምርጥ የሆኑ ቃላት ተጠቅሞ “በቅንነት የሚሄድ፣ ጽድቅንም የሚያደርግ፣ . . . እውነትን የሚናገር” ሲል መልሱን ሰጥቷል። (መዝ. 15:1, 2) እነዚህ ብቃቶች አሁንም አልተለወጡም። ዛሬም ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ለአምልኮ የሚመጡ ሁሉ ሥነ ምግባር የጎደላቸውን ልማዶችና ስካርን መተው አለባቸው። በይሖዋ ሕዝቦች ዘንድ ጠብ የሚወዱ፣ ራሳቸውን መቆጣጠር እስኪሳናቸው ድረስ የሚናደዱ ሰዎች ወይም አታላዮች ሊኖሩ አይገባም። አዲሶችም ሆንን የቆየን በአምላክ ቃል ውስጥ በግልጽ የተቀመጡትን ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃዎች በታማኝነት መጠበቅ አለብን። — ገላ. 5:19–21
2 ብዙ አዳዲስ ሰዎች ከይሖዋ ድርጅት ጋር መቀራረብ ጀምረዋል። ወጣቶችም ሆኑ አዛውንቶች አምላክ የሚፈልገው ዓይነት አኗኗር ለመኖር ሲሉ አስተሳሰባቸውን ለውጠዋል። በደቡብ አሜሪካ የሚገኝ አንድ ልጅ የወላጆች አመራር ሳያገኝ በማደጉ ምክንያት ጠባዩ በጣም ተበላሸ። 18 ዓመት ሲሆነው የዕፅ ሱሰኛ ሆነ። ይህንን ሱሱን ለማርካት ሲልም በመስረቁ ምክንያት ታስሮ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናቱ ከበፊት ጓደኞቹ ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋረጠ። በይሖዋ ምስክሮች ጉባኤ ውስጥ አዳዲስ ጓደኞች አገኘ። በመጨረሻም ሕይወቱን ለአምላክ ወሰነ።
3 እኛም በተመሳሳይ በጠባያችን ሁሉ ‘በእውነተኛ ጽድቅና በታማኝነት አቋም’ አምላክን ለማስደሰት መቁረጥ አለብን። (ኤፌ. 4:24) ተራራ መሰል በሆነው የአምላክ ድርጅት ውስጥ ለመቆየት ከፈለግን ‘አሮጌውን ሰውነት ከሥራው ጋር’ አውልቀን “[በትክክለኛ ዕውቀት] የሚታደሰውን አዲሱን ሰውነት” የመልበስ ግዴታ አለብን። — ቆላ. 3:9, 10
4 ብርቱ ግፊት የሚያሳድረው የአምላክ ቃል፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸልን የይሖዋ ጠባይ በአስተሳሰባችንና በድርጊቶቻችን ላይ ገንቢ ለውጥ ሊያስከትል ይችላል። (ሮሜ 12:2) ቃሉ አእምሮን የመለወጥና ልብን የመመርመር ኃይል አለው። (ዕብ. 4:12) በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች የይሖዋ ፈቃድ ንጹሕ ሥነ ምግባር ጠብቀን እንድንኖር፣ ለሕዝብ በሚደረገው አገልግሎት ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖረንና ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን እንዳንተው እንደሚፈልግብን ያስተምሩናል።
5 አስጨናቂ በሆነው በዚህ ዘመን ውስጥ እየጨመሩ የሚሄዱ ተጽዕኖዎች አንድ ክርስቲያን የአምላክን ሕግጋት እንዲጥስ ግፊት ሊያሳድሩበት ይችላሉ። የግል ጥናት፣ የቤተሰብ ጥናት፣ የጉባኤ ስብሰባዎች ወይም አገልግሎት ችላ ከተባሉ በፊት ጠንካራ የነበረ ክርስቲያን እንኳን ከእምነት እያፈገፈገ ሊሄድና ምናልባትም ወደ መጥፎ አኗኗር ሊወድቅ ይችላል። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “ለራስህና ለአስተማሪነትህ ዘወትር ጥንቃቄ አድርግ” እንዲሁም “የምልህን ዘወትር አስብበት” ብሎ የጻፈለት ለዚህ ነው። — 1 ጢሞ. 4:16 አዓት፤ 2 ጢሞ. 2:7 አዓት
6 አዲሶችም ሆንን ለዓመታት ካዳበርነው ተሞክሮ የተነሳ የጎለመስን ክርስቲያኖች ሕይወታችንን ለማዳን ከፈለግን አምላክ በሚፈልግብን ብቃቶች ላይ ማተኮር፣ በአገልግሎታችን ሚዛናዊ መሆንና ተስፋችንን አጥብቀን መያዝ አለብን። (1 ጴጥ. 1:13–16) አምላክ የሚፈልግብንን የጽድቅ ብቃቶች ዕለት ተዕለት መጠበቃችን የግድ አስፈላጊ ነው።
7 የ1993 የአገልግሎት ዓመት የመጨረሻ ወር በሆነው በዚህ ወር በመስክ አገልግሎት ለመሳተፍ ግብ አድርግ። በእምነት እንዲያድጉ ሌሎችን ለመርዳትና ራስህም በመስክ አገልግሎት ይበልጥ ፍሬያማ ለመሆን ቆርጠህ ተነሳ። (ሮሜ 1:12) የግል ጥናትህንና የቤተሰብ ጥናትህን ቋሚ በማድረግ እንዲሁም አዘውትረህ በስብሰባ በመገኘት አእምሮህ ተገቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር አድርግ። (ፊል. 4:8) አምላክ የሚፈልግብህን ብቃት እያሟላህ በመኖር አምላክን ለማስደሰት የምታደርገው ጥረት ተረስቶ አይቀርም። — ቆላ. 3:23, 24