እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለውን መጽሐፍ ማጥናት
1 በሌሎች አገሮች ነሐሴ 2 በሚጀምረው ሳምንት እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለው መጽሐፍ በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት መጠናት ይጀምራል። የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወትና አገልግሎት መመርመሩ እንዴት የሚያስደስት ይሆናል! መጽሐፉ ከዚህ በፊት ካጠናናቸው ሌሎች መጽሐፎች ትንሽ ለየት ብሎ የተዘጋጀ ስለሆነ መመሪያ የሚሆኑ ጥቂት ሐሳቦችን ማግኘት ጠቃሚ ይሆናል።
2 መጽሐፉ የገጽ ቁጥር የለውም፤ ስለዚህ በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ ታትሞ የሚወጣው ፕሮግራም የሚጠኑትን ምዕራፎች ይዘረዝራል። ብዙውን ጊዜ በእያንዳንዱ ሳምንት ሦስት ወይም አራት ምዕራፍ ይጠናል። ምዕራፍ 35፣ 111 እና 116 ረዘም ያሉ ስለሆኑ እያንዳንዳቸው በሁለት ጊዜ ይጠናሉ። ብቃት ያለው አንድ ወንድም ጠቅላላ ምዕራፉን (ወይም ምዕራፍ 35፣ 111 እና 116 ከሆነ ደግሞ ጠቅላላ ንዑስ ርእሱን) ካነበበ በኋላ የጥናቱ መሪ ከምዕራፉ ወይም ከተነበበው ክፍል ጋር የሚዛመደውን በምዕራፉ መጨረሻ ላይ ያለውን ጥያቄ ይጠይቃል። መልሶቹ ሁልጊዜ በምዕራፉ ውስጥ ያለውን ቅደም ተከተል አይጠብቁም። በትምህርቱ ላይ የተመሠረተ አጭርና ቀጥተኛ መልስ መሰጠት ይኖርበታል።
3 ከዚያም በኋላ ጊዜ በፈቀደ መጠን በምዕራፉ መጨረሻ ላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች መነበብ ይኖርባቸዋል። የተለያዩ አስፋፊዎች በንባቡ እንዲካፈሉ ለማድረግ ሲባል ረዘም ያሉ ጥቅሶችን መከፋፈልና በተነበበው ጥቅስ ላይ ሐሳብ መስጠት ይቻላል። በጥናቱ መሪ የሚዘጋጁት ቀጥተኛ ጥያቄዎች የተነበቡት ጥቅሶች በመጽሐፉ ውስጥ ከጎላው ሐሳብ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ የሚያሳዩ ትርጉም ያላቸው ሐሳቦች እንዲመለሱ ለማድረግ ይረዳሉ። የሚጠየቁት ጥያቄዎችና መልሶች ሁሉ በስብሰባው ላይ የሚገኙት ሰዎች ትኩረታቸውን በኢየሱስ ክርስቶስ፣ በአኗኗሩና በትምህርቶቹ ላይ እንዲያደርጉ የሚረዳቸው መሆን ይኖርበታል።
4 ታላቁ ሰው የተባለው መጽሐፍ የጊዜ ቅደም ተከተልን ጠብቆ የኢየሱስን ሕይወት ይመረምራል። የተፈጸሙትን ነገሮች በዓይነ ኅሊና ማየትና የተፈጸሙበትን ቦታ በአእምሮ መቅረጽ ሁኔታዎቹን ለማስታወስ በጣም ሊረዳን ይችላል። ስለዚህ ባለቀለም ሥዕላዊ መግለጫዎቹንና በመጽሐፉ መጀመሪያ ላይ ከመግቢያው ቀጥሎ ያለውን ካርታ ደጋግመህ ተመልከት።
5 በመጀመሪያው ሳምንት የመጽሐፉ መግቢያ ይጠናል። በየንዑስ ርዕሱ ሥር ያሉት አንቀጾች በሙሉ ከተነበቡ በኋላ የጥናቱ መሪ ያዘጋጃቸውን ተገቢ የሆኑ ጥያቄዎች ይጠይቃል። ይህ የመጀመሪያ ጥናት ለአንድ ዓመት ያህል በተከታታይ ለሚደረጉት ጥናቶች መንገድ ያመቻቻል። ትምህርቱ በተሳካ ሁኔታ መሸፈኑ የተመካው ጥናቱን የሚካፈሉት ሁሉ በሚያደርጉት ዝግጅት ላይ ነው። የመጽሐፍ ጥናቱ ቡድን እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠውን ታላቅ ሰው ጌታችንና አዳኛችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በሚገባ እንዲያውቀው ለመርዳት በተለይ የጥናቱ መሪ በየሳምንቱ በሚገባ እየተዘጋጀ መምጣት ይኖርበታል።
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል1]
(ወደ ገጽ 4 አምድ 3 ይዞራል )
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል1]
ታላቁ ሰው (ከገጽ 1 የዞረ )