የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 11/93 ገጽ 3-6
  • ወጣቶች ሆይ፣ የይሖዋን ልብ አስደስቱ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ወጣቶች ሆይ፣ የይሖዋን ልብ አስደስቱ
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—1993
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሃይማኖቴን መምረጥ ያለብኝ እኔ ነኝ ወይስ ወላጆቼ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • እናንት ወጣቶች፣ ትኩረታችሁ ያረፈው በመንፈሳዊ ግቦች ላይ ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
  • በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆነ ቤተሰብ መገንባት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • እናንት ወጣቶች—ይሖዋን ለማገልገል ያላችሁ ፍላጎት እያደገ ይሂድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
ለተጨማሪ መረጃ
የመንግሥት አገልግሎታችን—1993
km 11/93 ገጽ 3-6

ወጣቶች ሆይ፣ የይሖዋን ልብ አስደስቱ

1 አንድ ሰው የወጣትነት ጥንካሬና ብርታቱን በትክክለኛው መንገድ ሲጠቀምበት ሕይወት አስደሳች ሊሆንለት ይችላል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “አንተ ጐበዝ፣ በጉብዝናህ ደስ ይበልህ፣ በጉብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው” ሲል ጽፏል። (መክ. 11:9) እናንተ ወጣቶች ለምታደርጓቸው ነገሮች በአምላክ ዘንድ ተጠያቂዎች ናችሁ።

2 አኗኗራችሁ ለናንተ ብቻ ሳይሆን ለወላጆቻችሁም ልዩነት ያመጣል። ምሳሌ 10:1 “ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል ሰነፍ ልጅ ግን ለእናቱ ኀዘን ነው” በማለት ይገልጻል። ከዚህ ይበልጥ ደግሞ አኗኗርህ ፈጣሪህን ይሖዋ አምላክንም የሚነካ ነው። ምሳሌ 27:11 “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” በማለት ወጣቶችን የሚያበረታታው ለዚህ ነው። እናንተ ወጣቶች ዛሬ የይሖዋን ልብ ልታስደስቱ የምትችሉት እንዴት ነው? በብዙ መንገዶች ልታስደስቱት ትችላላችሁ።

3 በጥሩ ምሳሌነታችሁ፦ እናንተ ወጣቶች የምትኖሩት ይመጣል ተብሎ በአምላክ ቃል ውስጥ አስቀድሞ በተነገረው “የሚያስጨንቅ ዘመን” ውስጥ ነው። (2 ጢሞ. 3:1) ከማያምኑ የትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱት አመለካከቶቻችሁ ላይ ከሚያፌዙባችሁ አስተማሪዎች ጭምር ተፅዕኖዎች ይመጡባችኋል። ለምሳሌ አንድ አስተማሪ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ እውነት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ግን መሠረተ ቢስ ተረት እንደሆነ ተናገረ። ይሁን እንጂ በዚያ ክፍል ውስጥ የነበረች አንዲት ወጣት አስፋፊ በታማኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ደግፋ ተከራከረች። በዚህም ምክንያት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለመጀመር ተችሏል። ፍላጎት ያሳዩ አንዳንዶችም በስብሰባዎች መገኘት ጀመሩ። የእናንተ የወጣት ወንድሞችና እህቶች እምነት አምላካዊ ያልሆነውን ዓለም ይኮንናል፤ ልበ ቅን የሆኑ ሰዎችንም ወደ እውነት ይስባል። — ከዕብራውያን 11:7 ጋር አወዳድር።

4 በጉባኤ ውስጥ ያሉ እኩዮቻችሁ መጥፎ የሆነ ነገር ለማድረግ እንዳይሸነፉ ልታበረታቷቸው ትችላላችሁን? በትምህርት ቤት፣ በቤት እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ጥሩ ምሳሌ በመሆን የሌሎች ወጣት አስፋፊዎችን እምነት ልታጠነክሩ ትችላላችሁ። (ሮሜ 1:12) ለሌሎች ምሳሌ በመሆን የይሖዋን ልብ አስደስቱ።

5 በአለባበስና በአበጣጠር፦ አንዲት ወጣት እህት ልከኛ የሆነ ልብስ በመልበሷ ይቀልዱባትና ያሾፉባት ነበር፤ እንዲሁም “የማትነካ” የሚል ስም አወጡላት። ይህ አስፈራርቷት አምላካዊ ካልሆነው የዓለም አቋም ጋር እንድትስማማ አላደረጋትም። ከዚህ ይልቅ እሷ የይሖዋ ምስክር እንደሆነችና የምስክሮቹን ከፍተኛ የአቋም ደረጃ እንደምትጠብቅ ገለጸችላቸው። እንዲህ ዓይነት ጥንካሬ አላችሁ? ወይስ የሰይጣን ዓለም በራሱ የአስተሳሰብ መንገድና ጠባይ እንዲቀርጻችሁ ትፈቅዱለታላችሁ? ከእናንተ ከወጣቶች ብዙዎች የይሖዋን ትምህርት በመከታተል የዚህን ዓለምና የገዥዎቹን የአጋንንትን የተዝረከረኩ የልብስ ስታይሎች፣ ወረቶችና ጣዖታት እንዳስወገዳችሁ ማየቱ እንዴት የሚያስደስት ነው! — 1 ጢሞ. 4:1

6 በመዝናኛና በጨዋታ አመራረጣችሁ፦ ወላጆች ልጆቻቸው ትክክለኛውን መዝናኛና ጨዋታ በጥበብ እንዲመርጡ የመርዳትን አስፈላጊነት ማስታወስ ያስፈልጋቸዋል። አንድ ወንድም በጣም ይወደው ስለነበረ አንድ ጥሩ ቤተሰብ በአድናቆት ተናግሯል። እነዚያ ወላጆች መንፈሳዊ አስተሳሰብ ስለነበራቸው በቤተሰቡ መዝናኛም ረገድ መመሪያ ይሰጡ ነበር። ወንድም የተመለከተውን ሲናገር:- ‘ነገሮችን አብረው የሚሠሩ በመሆናቸው አደንቃቸዋለሁ። ወላጆቻቸው ልጆቻቸውን ለአገልግሎት በሚያደርጉት ዝግጅት ብቻ ሳይሆን በመዝናኛም ረገድ ይረዷቸው ነበር። የእግር ጉዞ ማድረግ፣ ሙዚየሞችን መጎብኘት ወይም እቤታቸው ሆነው መጫወት ወይም አንድ ሥራ መሥራት ደስ ይላቸው ነበር። እርስ በርሳቸው እንዲሁም ለሌሎች ያላቸው ፍቅር የመጣው ቢመጣ ወደፊት በእውነት ውስጥ መጓዛቸውን እንደሚቀጥሉ እንድትተማመኑ ያደርጋችኋል።’

7 ቤተሰቡ በሙሉ በአንድ ዓይነት ጨዋታ ወይም መዝናኛ እንዲካፈል ማድረግ የማይቻልባቸው ጊዜያት እንዳሉ የተረጋገጠ ነው። እናንተ ወጣቶች ይህንንና ትርፍ ጊዜያችሁን የምታሳልፉበትን መንገድ የመምረጡ ጉዳይ ክብደት ያለው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋችኋል። ሰይጣን የተቻለውን ያህል ብዙ ሰዎችን ለማሳሳት ቆርጦ ተነስቷል። ወጣቶችና ተሞክሮ የሌላቸው ሰዎች ደግሞ መሠሪ ለሆኑት ድርጊቶቹና አታላይ ማባበያዎቹ የተጋለጡ ናቸው። (2 ቆሮ. 11:3፤ ኤፌ. 6:11) ስለዚህ በዛሬው ጊዜ ሰይጣን እናንተን አታልሎ ከመንገዳችሁ ለማስወጣት እንዲሁም ራስ ወዳድ የሆነ፣ ተድላ አሳዳጅና ጽድቅ የጎደለው አኗኗር እንድትከተሉ ለማድረግ በተለያዩ መንገዶች ይጠቀማል።

8 ቴሌቪዥን ቁሳዊ ሀብትን ማሳደድንና ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር መከተልን የሚያበረታታ ዋነኛው ማታለያ ነው። ፊልሞችና ቪድዮዎች ዓመፅና በግልጽ የሚታዩ የጾታ ግንኙነቶችን ያሳያሉ። ታዋቂ ዘፈኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ ወራዳና ቀፋፊ እየሆኑ መጥተዋል። የሰይጣን ማባበያዎች ከላይ ሲታዩ ጉዳት የማያስከትሉ ሊመስሉ ይችላሉ፤ ሆኖም በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያን ወጣቶችን አጥምደው የተሳሳተ አስተሳሰብና መጥፎ ጠባይ እንዲኖራቸው አድርገዋል። እንዲህ ያሉ ተፅዕኖዎችን ለመከላከል በርትታችሁ ጽድቅን መከታተል አለባችሁ። (2 ጢሞ. 2:22) በመዝናኛ ወይም በጨዋታ ረገድ አስተሳሰባችሁን ወይም ድርጊታችሁን ማስተካከል ካስፈለገ ይህንን ማስተካከያ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? መዝሙራዊው እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል:- “በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፣ ከትእዛዝህ አታርቀኝ።” — መዝ. 119:10

9 የስፖርትና የመዝናኛ ኮከብ ተጫዋቾችን እንደ ጣዖት ማምለክ የተለመደ ነው። ይሖዋን መፍራት ፍጽምና የሌላቸውን ሰዎች እንደ ጣዖት ከማምለክ እንድትርቁ ይረዳችኋል። ዛሬ የጾታ ብልግና ራሱ በብዙዎች ዘንድ እንደ ጣዖት እየተመለከ ነው። ወሲብ ነክ ከሆኑ ጽሑፎችና ሥነ ምግባርን ከሚያበላሹ ሙዚቃዎች በመራቅ እንዲህ ካሉ ዝንባሌዎች ራሳችሁን ለመጠበቅ ትችላላችሁ። ሙዚቃን በተመለከተ የሚያዝያ 15, 1993 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ሙዚቃ መለኮታዊ ስጦታ ነው። ይሁን እንጂ ለብዙዎች ጊዜያቸውን የሚይዝ ሆኖባቸዋል። . . . ለሙዚቃ ተገቢ ቦታ ሰጥታችሁ ትኩረታችሁንና አሳባችሁን በሙሉ በይሖዋ ሥራ ላይ ማድረግ ዓላማችሁ ይሁን። ስለምትመርጡት ሙዚቃ ጠንቃቆችና መራጮች ሁኑ። ይህን ካደረጋችሁ በዚህ መለኮታዊ ስጦታ አላግባብ ሳይሆን በአግባቡ ለመጠቀም ትችላላችሁ።”

10 መጥፎ ለሆነው ነገር ፍጹም ጥላቻ ኮትኩቱ። (መዝ. 97:10) መጥፎ ነገር ለማድረግ ስትፈተኑ ይሖዋ ነገሩን እንዴት እንደሚመለከተው አስቡበት፤ የሚያስከትለውንም ውጤት ማለትም ያልተፈለገ እርግዝና፣ በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች፣ አስጨናቂ የስሜት መቃወስ፣ ራሳችን ለራሳችን የነበረን አክብሮት ማጣትና በጉባኤ ውስጥ አንዳንድ መብቶች ማጣትን አስቡት። ክፋትን ከሚያበረታቱ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ፊልሞች፣ ቪድዮዎች፣ ዘፈኖች ወይም ጭውውቶች ራቁ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰነፎች” ብሎ ከሚመድባቸው ጋር አትወዳጁ። (ምሳሌ 13:19) መራጮች ሁኑ፤ ይሖዋንና የጽድቅ አቋም ደረጃዎቹን የሚወድዱ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሰዎችን የቅርብ ጓደኞቻችሁ አድርጋችሁ ምረጡ።

11 አዎን፤ የይሖዋን ልብ በእውነት ለማስደሰት የሚፈልጉ ወጣቶች በኤፌሶን 5:15, 16 ላይ ያለውን ጥሩ ምክር ይሰማሉ:- “እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ።” በነዚህ የመጨረሻ ቀኖች እድገታችሁን ‘በጥንቃቄ መጠበቅ’ እንድትችሉ የሚረዳችሁ ምንድን ነው?

12 ለሚያስፈልጓችሁ መንፈሳዊ ነገሮች ማሰብ፦ በማቴዎስ 5:3 ላይ ኢየሱስ “ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” ብሎ ነበር። እናንተም ለሚያስፈልጋችሁ መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ በመሆን ደስተኞች መሆን ትችላላችሁ። የሚያስፈልጋችሁን ነገር ማሟላት ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ መካፈልንም ይጨምራል፤ ምክንያቱም መስበክ በተማርናቸው ነገሮች ላይ ያለንን እምነት ያጠነክርልናል። — ሮሜ 10:17

13 ዘወትር በአገልግሎቱ መካፈል ሁልጊዜ ቀላል አለመሆኑን በግል ካገኛችሁት ተሞክሮ አውቃችኋል። ቀላል እንዳይሆን ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ በችሎታዎቻችሁ ለመተማመን አለመቻል ነው። ስለዚህ ቆራጦች መሆን ያስፈልጋችኋል። በአገልግሎት አዘውትራችሁ በመካፈል የምስክርነት አሰጣጥ ችሎታችሁን አዳብሩ፤ ለመስበክ ባላችሁ ችሎታም ተማመኑ።

14 የበለጠ ልምድ ካላቸው የጉባኤያችሁ አስፋፊዎች ለምሳሌ ከዘወትር አቅኚዎችና ከሽማግሌዎች ጋር ለመሥራት ዝግጅት አድርጉ። የመልእክት አቀራረባቸውንና በየበሩ የሚያጋጥሟቸውን ተቃውሞዎች እንዴት እንደሚያበርዱ ልብ ብላችሁ አዳምጡ። ምክንያቱን ማስረዳት በተባለው መጽሐፍና የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሚወጡትን ሐሳቦች በደንብ ተጠቀሙባቸው። ሁለመናችሁን ለይሖዋ ስለምትሰጡ ባጭር ጊዜ ውስጥ ከአገልግሎታችሁ የበለጠ ደስታ ታገኛላችሁ። — ሥራ 20:35

15 አንዳንዶች በትምህርት ቤት ለመመስከር በሚያስችሏቸው አጋጣሚዎች ለመጠቀም በመቻላቸው ደቀ መዛሙርት በማድረጉ በኩል ብዙ ተሳክቶላቸዋል። (ማቴ. 28:19, 20) አንድ ክርስቲያን ወጣት እንዲህ አለ:- “ነጻ በምንሆንባቸው ክፍለ ጊዜዎች በተለይ በበዓላት ሰሞን ለመመስከር የምችልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች ይኖሩኛል። ሌሎች ማየት በሚችሉበት ቦታ ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ዴስኬ ላይ ሳስቀምጥ ፍላጎት ያላቸው ብዙ ተማሪዎች መጥተው ያነጋግሩኛል።” እያደር በርካታ ተማሪዎችና አስተማሪውም ጭምር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መገኘት ጀመሩ። እንዲያውም አንዷ አስተማሪ ጥሩ ዕድገት በማሳየት ራሷን የወሰነች ምስክር እስከመሆን ደርሳለች። ይሖዋ እንደናንተ ያሉ ወጣት አምላኪዎች ለስሙ ውዳሴ ሲያመጡ በጣም ደስ ይለዋል።

16 የሚያስፈልጋችሁን መንፈሳዊ ነገር ለማርካት የምትችሉበት ሌላው መንገድ የግል ጥናት በማድረግ ነው። የይሖዋን ልብ ለማስደሰት ስለ እርሱ፣ ስለ ዓላማዎቹና እርሱ ስለሚፈልግብን ነገሮች ማወቅ አለብን። ለግል ጥናት ጊዜ ትመድባላችሁን? ዘወትር ጊዜ ወስዳችሁ እንደምትበሉ ሁሉ አዘውትራችሁ ታጠናላችሁን? (ዮሐ. 17:3) በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ በሚወጣው ፕሮግራም መሠረት ከምታነቡት በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ የግል ፕሮግራም አውጥታችኋልን? ለሁሉም ስብሰባዎች በደንብ ትዘጋጃላችሁን? መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን አዘውትራችሁ ታነባላችሁን? በተለይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” በሚል ርዕስ የሚወጡትን ትምህርቶች ሁሉ እያንዳንዱን ጥቅስ እያወጣችሁ በጥንቃቄ በመመልከት ታነቧቸዋላችሁን? እንዲሁም ማኅበሩ ለሚያስፈልጓችሁ መንፈሳዊ ነገሮች በማሰብ ያወጣውን የወጣቶች ጥያቄዎችና ሊሠሩ የሚችሉ መልሶቻቸው የተባለውን መጽሐፍ አትዘንጉት። በመላው ዓለም የሚገኙ ክርስቲያን ወጣቶችና ወላጆቻቸው ይህ መጽሐፍ ወደ ይሖዋ የበለጠ እንዲቀርቡ እንዴት እንደረዳቸው በመግለጽ ደብዳቤ ጽፈዋል።

17 መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተዘጋጁ ቲኦክራሲያዊ የሆኑ አጋዥ መጻሕፍት ስታነቡ ስለ ይሖዋ፣ ለነገሮች ስላለው አመለካከትና ስለ ዓላማዎቹ ይነግሯችኋል። የምታነቡት ሐሳብ እንዴት ሊጠቅማችሁ እንደሚችል አጢኑት። እንዲሁም ከዚህ በፊት ካነበባችሁት ጋር አዛምዱት። ይህም ማሰላሰል አለባችሁ ማለት ነው። በነገሩ ላይ ማሰላሰላችሁ ትምህርቱ ወደ ልባችሁ ጠልቆ እንዲገባና ለተግባር እንዲገፋፋችሁ ያደርጋል። — መዝ. 77:12

18 ለሚያስፈልጋቸው መንፈሳዊ ነገር ንቁ የሆኑ ወጣቶች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሲገኙ በማየታችን ደስ ብሎናል። እናንተ ክርስቲያን ወጣቶች በስብሰባዎች ላይ ስሜት የሚሰጡ ሐሳቦችን አዘውትራችሁ ስትሰጡ ሌሎችን ልታበረታቱ ትችላላችሁ። በየስብሰባው ቢያንስ አንድ ጊዜ ሐሳብ ለመስጠት ግብ አውጡ። ከስብሰባ በፊትና በኋላ አብራችሁ በመቆየት በማንኛውም ዕድሜ ከሚገኙ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሰዎች ጋር ሞቅ ያለ ወዳጅነት አዳብሩ። (ዕብ. 10:24, 25) አንድ ወጣት ወንድም ወላጆቹ በየስብሰባው ቢያንስ ቢያንስ ከአንድ በዕድሜ የገፋ ወንድም ወይም በዕድሜ ከገፋች እህት ጋር እንዲነጋገር ያበረታቱት እንደነበር ተናግሯል። በዕድሜ ከገፉ የጉባኤው አባላት ጋር አብሮ ጊዜ በማሳለፉ ያገኘውን ልምድ ዛሬ በጣም ከፍ ያለ ዋጋ ይሰጠዋል።

19 መንፈሳዊ ግቦችን ተከታተሉ፦ የብዙ ወጣቶች ሕይወት ዓላማ ወይም አቅጣጫ የሌለው መሆኑ ያሳዝናል። ይሁን እንጂ ቲኦክራሲያዊ ግቦችን አውጥቶ በተሳካ ሁኔታ ግቦቹ ላይ መድረስ አያስደስትም? በመለኮታዊ ትምህርት ብርሃን አማካይነት እነዚህን ግቦች መከታተሉ በአሁኑ ጊዜ የግል እርካታን የሚሰጥ በመጨረሻው ደግሞ ወደ ዘላለም መዳን የሚመራ ነው። — መክ. 12:1, 13

20 ግብ ስታወጡ በጸሎት አስቡበት። ከወላጆቻችሁና ከሽማግሌዎች ጋር ተነጋገሩበት። ራሳችሁንና ችሎታዎቻችሁን መርምሩና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉና ራሳችሁን ከሌሎች ጋር በማወዳደር ሳይሆን እናንተ ራሳችሁ ልታከናውኑ የምትችሏቸውን ግቦች አውጡ። እያንዳንዱ ሰው በአካል፣ በአእምሮ፣ በስሜትና በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ የተለያየ አቋም አለው። ስለዚህ አንድ ሌላ ሰው ሊፈጽም የቻላቸውን ነገሮች ሁሉ እፈጽማለሁ ብላችሁ አትጠብቁ።

21 ልትደርስባቸው የምትችላቸው አንዳንድ ግቦች ምንድን ናቸው? ገና አስፋፊ ካልሆንክ ወይም ካልተጠመቅህ እነዚህን ግቦችህ ልታደርጋቸው ትችላለህ። አስፋፊ ከሆንክ በየሳምንቱ በአገልግሎት የተወሰነ ሰዓት ለማምጣት ግብ ልታወጣ ትችላለህ። ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ጊዜ ጐበዝ አስተማሪ ለመሆን ጥረት አድርግ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራትንም ግብ አድርገው። የተጠመቅህ ወጣት ተማሪ ከሆንክ በእረፍት ወራት ረዳት አቅኚ ለመሆን ለምን ግብ አታወጣም? ‘የምትሠራው ብዙ የጌታ ሥራ’ አለ። — 1 ቆሮ. 15:58

22 የወላጆች እርዳታ የግድ አስፈላጊ ነው፦ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ሕይወትን ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ብቻቸውን እንደሆኑ በጭራሽ ሊሰማቸው አይገባም። ይሖዋ ወጣቶች በየዕለቱ ለሚያደርጓቸው ውሳኔዎችና በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን እንቅፋቶች ለመወጣት የሚረዷቸውን ምክሮች በድርጅቱ በኩል ሰጥቷቸዋል። ራሳቸውን የወሰኑ ወላጆች ልጆቻቸው ትክክለኛ ውሳኔዎችን እንዲያደርጉ የመርዳት ተቀዳሚ ኃላፊነት አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ቆሮንቶስ 11:3 ላይ ባልን የቤተሰቡ ራስ አድርጎ ሾሞታል። እንግዲያው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ አባት የአምላክን ትዕዛዛት ለልጆቹ በማስተማር ግንባር ቀዳም ይሆናል፤ በዚህ በኩል ሚስቱም አብራው ትሠራለች። (ኤፌ. 6:4) ይህም ከሕፃንነቱ ጀምሮ በትጋት በሚሰጥ ሥልጠና አማካኝነት ይከናወናል። የሕፃን አእምሮ በመጀመሪያዎቹ የሕይወቱ ሦስት ዓመታት ውስጥ በሦስት እጥፍ ስለሚያድግ ወላጆች የሕፃኑን ልጃቸውን የመማር ችሎታ በፍጹም ዝቅ አድረገው መመልከት አይገባቸውም። (2 ጢሞ. 3:15) ልጆቹ እያደጉ ሲሄዱ ይሖዋን እንዲወድዱና ከእርሱ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኮተኩቱ ወላጆች ደረጃ በደረጃ ማስተማር ያስፈልጋቸዋል።

23 የወላጆች መልካም አርዓያነት ሥልጠናውን ለመጀመር የሚያስችል የተሻለ መንገድ ነው። ማድረግ ስላለባቸውና ስለሌለባቸው ብዙ ከመናገር ይልቅ ልጆቻችሁን በመንፈሳዊ ለመርዳት ይህ በጣም ይረዳችኋል። ወላጆች ትክክለኛ አርዓያ ለመሆን በቤት ውስጥ ለትዳር ጓደኛም ሆነ ለልጆች የመንፈስ ፍሬዎችን ማሳየት ያስፈልጋቸዋል። (ገላ. 5:22, 23) ብዙዎች የአምላክ መንፈስ ጥሩ ነገርን ለማድረግ የሚገፋፋ ኃይል መሆኑን ከተሞክሮ ተመልክተዋል። የልጆቻችሁን አእምሮና ልብ ለመቅረጽ እናንተንም ይረዳችኋል።

24 በተጨማሪም ወላጆች በግል ጥናት ልማድ፣ በጉባኤ በመገኘትና በአገልግሎቱ አዘውትረው በመካፈል ጥሩ ምሳሌ መሆን ያስፈልጋቸዋል። በቤት ውስጥ ስለ እውነት ሞቅ ባለ መንፈስ የምትናገሩ ከሆናችሁ በአገልግሎቱ በቅንዓት ግንባር ቀደም ሆናችሁ ከተካፈላችሁና የግል ጥናትን በተመለከተ ገንቢ አመለካከት ካላችሁ ልጆቻችሁ ለመንፈሳዊ ነገሮች ከልብ ፍላጎት እንዲኖራቸው ሊበረታቱ ይችላሉ።

25 ቋሚና ስሜት የሚሰጥ የቤተሰብ ጥናት ካለና ታስቦበት ዝግጅት ከተደረገበት የሚያጓጓና አስደሳች ሊሆን ይችላል፤ ቤተሰቡ በሚያጽናና ሁኔታ አንድ ላይ እንዲሆንም ያስችላል። ጊዜ ወስዳችሁ የልጆቻችሁ ልብ እንዲነካ አድርጉ። (ምሳሌ 23:15) ብዙ ቤተሰቦች ይህንን አጋጣሚ ለሳምንታዊው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ለመዘጋጀት ይጠቀሙበታል፤ አልፎ አልፎ ግን ቤተሰቡ በሚያስፈልገው አንድ የተለየ ትምህርት ላይ ቢነጋገሩ የሚያበረታታ ሊሆን ይችላል። የአመለካከት ጥያቄዎችን በመጠየቅ እያንዳንዱ የቤተሰቡ አባል የሚሰጠውን ሐሳብ ማዳመጡ እውቀት የሚጨምርና የሚያነቃቃ ነው። እያንዳንዱን የቤተሰብ አባል የሚጠቅም ጥናት መምራት ለቤተሰቡ ራስ በእርግጥ ቀላል አይደለም። ነገር ግን ሁሉም በመንፈሳዊ ሲያድጉ እንዴት የሚያረካ ይሆንለታል! ሁሉም በጥናቱ ውስጥ እንዲካፈሉ ከተደረገ ደስ የሚል መንፈስ ይኖራል።

26 የልጆችህን ሕይወት ለማዳን አሁን የምትሰጣቸው ፍቅራዊና ልዩ የሆነ ሥልጠና በጣም ወሳኝ ነው። (ምሳሌ 22:6) ይህንን በአእምሮህ ከያዝክ ይህ ከማስተማር ሥራዎችህ ሁሉ የሚበልጥ መሆኑን በቀላሉ ልትረዳ ትችላለህ። ልዩና በጣም አስፈላጊ የሆነውን ይህንን ሥራ የምትሠራው አንተ ብቻ እንደሆንክ በፍጹም አይሰማህ። ለቤተሰብህ ያለብህን ኃላፊነት የምትወጣበትን መመሪያ ለማግኘት በይሖዋ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መመካትን ተማር። ይህም ብቻ አይደለም። ሌሎችም ከፍተኛ እርዳታ ሊሰጡህ ይችላሉ።

27 እርዳታ ለመስጠት ሌሎች ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር፦ ሽማግሌዎች ወጣቶችና ወላጆቻቸው አብረው በመሆን የመንግሥት አዳራሹን እንዲያጸዱ ሊያደርጉ ይችላሉ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ልጆቹን አበረታቷቸው። በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ክፍል ያላቸው ሽማግሌዎችና ዲያቆናት የአድማጮች ተሳትፎ በሚያስፈልግባቸው ክፍሎች ላይ እጃቸውን ያወጡ ልጆች እንዳሉ መፈለግ ይኖርባቸዋል። አጋጣሚው ሲኖር አርዓያ የሆኑ ወጣቶችን ፈልጋችሁ ከወላጆቻቸው ጋር ትዕይንት እንዲያቀርቡ አድርጉ። አንዳንዶችም ቃለ ምልልስ ሊደረግላቸውና አጫጭር ሐሳቦችን ሊሰጡ ይችሉ ይሆናል።

28 የሚያደርጉትን ጥረት እንደ ተራ ነገር አትመልከቱት። ወጣቶች ለጉባኤው ልዩ ሀብት ሆነው ተገኝተዋል። ብዙዎች በመልካም ምግባራቸው ‘የአዳኛችን የአምላክ ትምህርት በሁሉ ነገር እንዲከበር’ አድርገዋል። (ቲቶ 2:6–10 የ1980 ትርጉም) አነስተኛ ተሳትፎ የሚያደርጉትን ወጣቶችም ቢሆን ማመስገኑ አስፈላጊ ስለሆነ በዚህ ረገድ ንቁ ሁኑ። እንዲህ ማድረግ ተዘጋጅተው እንዲመጡና ወደፊትም እንዲሁ ተሳትፎ የማድረግ ፍላጎት እንዲኖራቸው ያበረታታቸዋል። ትልልቆች ለወጣቶች ተሳትፎ የሚያሳዩት አድናቆት በቀላሉ የሚገመት ሳይሆን እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነው። ሽማግሌ ወይም ዲያቆን ከሆንክ አንድ ወጣት የጉባኤ አባል በስብሰባ ላይ ላቀረበው ንግግር ወይም ትዕይንት ምን ያህል ጊዜ አመስግነህ ታውቃለህ?

29 አቅኚዎችስ እነርሱን ለመርዳት ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? ፕሮግራማችሁን መርምራችሁ ተማሪዎችን በከሰዓት በኋላ ወይም በቅዳሜና እሁድ ፕሮግራማችሁ ውስጥ ለማስገባት ለምን አታስተካክሉትም? ስለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ምርጫችሁ ገንቢ በሆነ መንገድ ትናገራላችሁን? ከአገልግሎታችሁ ደስታ እንዳገኛችሁ ከፊታችሁ ይነበባልን? ሌሎችም በተለይ ወጣቶች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ቢሆኑ ጥሩ እንደሆነ ሐሳብ ታቀርቡላቸዋላችሁን? ከበር ወደ በር እየሄዳችሁ ስታገለግሉ አነጋገራችሁ የሚያንጽና ገንቢ ነውን? እንደዚያ ከሆነ በጣም አስፈላጊ በሆነው በዚህ የሥልጠና ሥራ እናንተም በአቅኚነታችሁ ተካፋዮች ትሆናላችሁ።

30 በጉባኤ ውስጥ ያሉት ሁሉ ወጣቶችን ማሠልጠኑ በጣም አስፈላጊ ሥራ መሆኑን በሚገባ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። በመስክ አገልግሎት አብራችሁ ለመሥራት ቀጠሮ መያዝ ትችሉ ይሆን? ከበር ወደ በር እየሄዳችሁ ለማገልገል አቀራረቦችን አብራችሁ ልትለማመዱ ትችላላችሁ? በመስክ አገልግሎት አብራችሁ ስታገለግሉ ወደፊት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ሊያደርጉ ስለሚችሉባቸው አጋጣሚዎች አንስታችሁ ማበረታቻ ለመስጠት ንቁዎች ናችሁን? እያንዳንዱ አስፋፊ የሚሰጠው ትንሽ ሐሳብ እንኳን ለአንድ ወጣት ዘላለማዊ ጥቅም ሊያመጡለት ስለሚችሉ የዕድሜ ልክ መንፈሳዊ ግቦች ገንቢ በሆነ መንገድ እንዲያስብ የሚያበረታታው ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይኖርበታል።

31 ወጣቶች ራሳቸውን ሊረዱ ይችላሉ፦ ወጣቶች ሆይ፣ የይሖዋን ትምህርቶች መከታተላችሁንና ዓለም የሚያቀርብላችሁን ነገር መሸሻችሁን እንድትቀጥሉ እያንዳንዳችሁን እናበረታታችኋለን። ጠባያችሁንና ውስጣዊ ስሜቶቻችሁን አዘውትራችሁ መርምሩ። ለይሖዋና እርሱ በዕለት ተዕለት አኗኗራችሁ ለሚፈልግባችሁ ነገሮች ምን ዓይነት አመለካከት አላችሁ? የሰይጣንን ሐሳቦች ለመቋቋም የምትችሉትን ያህል ጠንክራችሁ ትታገላላችሁን? (1 ጢሞ. 6:12) ሰዎች በተለይም ወጣቶች በተፈጥሮአቸው በእኩዮቻቸው ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ይፈልጋሉ። ታዲያ መጥፎ ነገር በማድረግ አብዛኛው ሕዝብ የሚያደርገውን ለመከተል ትሳባላችሁን? (ዘጸ. 23:2) ሐዋርያው ጳውሎስ የዓለምን መንገድ እንድንከተል የሚያደርገን ከባድ ተፅዕኖ እንደሚኖር ተገንዝቧል። — ሮሜ 7:21–23

32 የዓለምን ተፅዕኖ ለመቋቋም፣ ከዓለማዊ እኩዮቻችሁ የተለየ መንገድ ለመከተል እንዲሁም የአምላክን ትምህርቶች ለመከታተል ድፍረት ይጠይቃል። በጥንት ጊዜ የነበሩ ሰዎች በዚህ ረገድ ተሳክቶላቸዋል። ኖህ የነበረውን ድፍረት ተመልከቱ። በእምነቱና በጊዜው ከነበሩት ክፉ አድራጊዎች የተለየ በመሆኑ ዓለምን በሙሉ ኮንኗል። (ዕብ. 11:7) ሊጣርለት የሚገባው ስለሆነ ጠንክራችሁ ታገሉ። የሰይጣንን ጭፍራ የሚከተሉ ደካማ፣ ልፍስፍስና ፈሪ የሆኑ ሰዎችን አትምሰሉ። በተቃራኒው ግን በይሖዋ ዓይን ሞገስ እያገኙ ያሉትን ሰዎች ወዳጅነት ለማግኘት ጣሩ። (ፊል. 3:17) ከእናንተ ጋር አብረው ወደ አምላክ አዲስ ዓለም ከሚጓዙት ሰዎች ጋር አብራችሁ ሁኑ። (ፊል. 1:27) ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው አንድ መንገድ ብቻ መሆኑን አስታውሱ። — ማቴ. 7:13, 14

33 ለአምላካችን ውዳሴና ክብር የሚያመጡ ወጣቶችን ማየቱ እኛን ካስደሰተን እሱንማ ምን ያህል ያስደስተው ይሆን! ይሖዋ ታላላቅ ዓላማዎቹን በማወጁ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ የሚያደርጉ ወጣቶችን ሲያይ ደስ እንደሚለው ምንም አያጠራጥርም። እነርሱ የእርሱ ‘ስጦታዎች’ ስለሆኑ ጥሩ ጥሩውን ይመኝላቸዋል። (መዝ. 127:3–5፤ 128:3–6) ክርስቶስም የአባቱን ፍላጎት በማንጸባረቅ ከወጣት ልጆች ጋር አብሮ መሆን ደስ ይለው ነበር። ጊዜ ወስዶም ይሖዋን እንዲያመልኩ ያበረታታቸው ነበር። ያቀርባቸውና ይወድዳቸው ነበር። (ማር. 9:36, 37፤ 10:13–16) ወጣቶቻችንን የምንመለከታቸው ይሖዋና ኢየሱስ በሚያዩአቸው መንገድ ነውን? በጉባኤዎቻችን ያሉ ወጣቶች ይሖዋና መላእክቱ ታማኝነታቸውንና መልካም ምሳሌነታቸውን እንዴት እንደሚመለከቱት ይገነዘባሉን? መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ በመጣር ይሖዋን እንዲያስደስቱ ምስጋናና ማበረታቻ ሊሰጣቸው ይገባል። ወጣቶች ሆይ፣ አሁንም ሆነ ለወደፊቱ በረከት የሚያመጡላችሁን ግቦች ተከታተሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ