ሌሎች ሰዎች ስለ አምላክ ልጅ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲማሩ እርዷቸው
1 በዓመቱ ውስጥ ከማንኛውም ወር ይልቅ ታኅሣሥ ክርስቲያን ነን የሚሉ አብዛኞቹ ሰዎች ስለ ኢየሱስ የሚያስቡበት ወር ነው። ስለዚህ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለውን መጽሐፍ ለማበርከት ታኅሣሥ በጣም ጥሩ ወር ነው። በአገልግሎት ክልላችን ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች ስለ አምላክ ልጅ ማወቅ የሚያስደስታቸው ሆነው ሲገኙ ላገኘናቸው ሁሉ መጽሐፉን ለማበርከት እንፈልጋለን። ይህን መጽሐፍ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው?
2 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተና በኢየሱስ ላይ ያተኮረ ቀጥተኛ ውይይት ለመጀመር ሞክር።
ለቤቱ ባለቤት ሰላምታ ካቀረብክ በኋላ ቀጥሎ ያለውን የሚመስል አንድ ሐሳብ ልትናገር ትችላለህ፦
◼ “ዛሬ ጎረቤቶቻችን ከመጽሐፍ ቅዱሳቸው ውስጥ ስለ ዘላለም መኖር ቢያነቡ ምን እንደሚሰማቸው እየጠየቅናቸው ነው። [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ይህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነው፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ለዘላለም ስለመኖር ወደ 40 ያህል ጊዜ ይናገራል። እንዲህ ያለው ሕይወት ለእኛ ምን ትርጉም ይኖረዋል? ራእይ 21:4 የሚለውን ልብ ይበሉ። [አንብብ] ምን ተስፋ እንደተሰጠን አስተዋሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?” ዮሐንስ 17:3ን አንብብና ስለ አምላክና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የማወቅን አስፈላጊነት አጉላ። ከዚያም ፍላጎቱን በይበልጥ ለማነሣሣት በመግቢያው ላይ የወጡትን ንዑስ ርዕሶች በመጠቀም ታላቁ ሰው የተባለውን መጽሐፍ ለቤቱ ባለቤት አሳየው።
3 የቤቱ ባለቤት መጽሐፉን ለመውሰድ ካልፈለገ በቅርቡ የወጡ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች እትሞችን አቅርብለት ወይም ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም የሚለውን ትራክት ስጠው። በምታቀርብለት ጽሑፍ ላይ ባሉ በአንድ ወይም በሁለት የተወሰኑ ነጥቦቸ ላይ እንዲያተኩር አድርግ። ስለ ርዕሰ ጉዳዩ ያደረጋችሁትን ውይይት ለመቀጠል በሚመቸው ጊዜ ልትመለስ እንደምትፈልግ ጥቀስለት።
4 የቤቱ ባለቤት ሥራ የበዛበት መስሎ ከታየህ ከላይ ያለውን ንግግር ማሳጠሩ ጥበብ ይሆናል። በተጨማሪም አዲስ አስፋፊዎች ቀጥሎ ያለውን አቀራረብ መጠቀም ቀላል ሆኖ ያገኙት ይሆናል።
ራሳችንን ካስተዋወቅን በኋላ እንዲህ ልንል እንችላለን፦
◼ “ዛሬ ጎረቤቶቻችንን ከመጽሐፍ ቅዱሳቸው ላይ ስለ ዘላለም መኖር ቢያነቡ ምን እንደሚሰማቸው እየጠየቅናቸው ነው። ለምሳሌ ኢየሱስ በዮሐንስ 17:3 ላይ የተናገረውን ይመልከቱ። [አንብብ] ይህ መጽሐፍ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና እርሱ ስላስተማራቸው ነገሮች የበለጠ እንዲያውቁ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ታላቁ ሰው የተባለውን መጽሐፍ ግለጥና ውብ ከሆኑት ሥዕላዊ ማስረጃዎች አንዳንዶቹን አሳየው። ወደ መግቢያው ተመለስና “ስለ እርሱ በመማር የሚገኝ ጥቅም” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ያለውን ሁለተኛውን አንቀጽ አንብብ።” ከዚያም መጽሐፉን አበርክትለት።
5 መጽሐፉን ካበረከትክ በዚያው ቀን ወይም ከጥቂት ቀናት በኋላ ተመልሰህ ስትመጣ “ከሰማይ የመጣ መልእክት” በሚለው የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ውይይት ለማድረግ ሐሳብ በማቅረብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር መሠረት ጣል። በሚቀጥለው ጊዜ የቤቱን ባለቤት ተመልሰህ ስትጠይቀው መደበኛ በሆነ መንገድ ለተወሰነ ጊዜ እንደምትነጋገሩ ከመንገር ይልቅ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ያምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ተጨማሪ አስደሳች ትምህርት ሊማር እንደሚችል ብቻ ንገረው።
6 ሁላችንም ዓለማዊ በዓል የሚከበርበትን ይህን ወቅት ሌሎች ስለ አምላክ ልጅ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚነገረው እውነት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉና ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ እንዲመላለሱ ለመርዳት እንጠቀምበት።—ማቴ. 7:14