እየወረዳ ስብሰባ ማሳሰቢያዎች
ጥምቀት፦ በሁለተኛው ቀን ጠዋት ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት የጥምቀት እጩዎች በተመደበላቸው ቦታ መቀመጥ አለባቸው። አንዳንዶች የሚለብሷቸው ልብሶች ለሁኔታው ክብር የማይሰጡና የተመልካችን ስሜት ቅር የሚያሰኙ መሆናቸው ተስተውሏል። እያንዳንዱ ተጠማቂ ልከኛ ልብስ ወይም ውሃ ውስጥ በሚገባበትም ጊዜ ልከኝነቱን የማይቀይር ልብስና (ስስ ፖሊስተር ያልሆነ) ፎጣ ይዞ መምጣት ይኖርበታል። የጥምቀት ንግግሩና ጸሎቱ በተናጋሪው ከቀረበ በኋላ የመድረኩ ሊቀመንበር ለእጩዎቹ አጠር ያለ መመሪያ ይሰጥና መዝሙር እንዲዘመር ይጋብዛል። የመጨረሻው ስንኝ ከተዘመረ በኋላ አስተናጋጆች እጩዎቹን ጥምቀቱ ወደሚከናወንበት ቦታ እየመሩ ይወስዷቸዋል። ጥምቀት አንድ ሰው ራሱን መወሰኑን የሚያሳይበት ምልክትና በግለሰቡና በይሖዋ መካከል ብቻ ያለ የግል ጉዳይ ስለሆነ የጓደኛሞች ጥምቀት ተብሎ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ የጥምቀት እጩዎች ተቃቅፈው ወይም እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲጠመቁ አይፈቀድም።
ደረት ላይ የሚለጠፉ ካርዶች፦ በስብሰባው ላይ እንዲሁም ወደ ስብሰባው ቦታ ስትሄዱና ስትመጡ ለ1994 የተዘጋጀውን ደረት ላይ የሚለጠፍ ካርድ እባካችሁ አድርጉ። ይህን ደረት ላይ የሚለጠፍ ካርድ ማድረግ በምንጓዝበት ጊዜ ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት ያስችለናል። ይህ እውነት መሆኑ ባለፈው ዓመት በናይሮቢና በአዲስ አበባ በተደረጉት ስብሰባዎች ላይ ጎልቶ ታይቷል። በደረት ላይ የሚለጠፉትን ካርዶችና መያዣቸውን በጉባኤያችሁ በኩል ልታገኙ ትችላላችሁ። በስብሰባው ላይ ግን አይገኙም። የወቅቱን የሕክምና መመሪያ ካርዳችሁን መያዝ አትርሱ።
የአቅኚዎች መታወቂያ፦ ሁሉም የዘወትርና ልዩ አቅኚዎች እንዲሁም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የመታወቂያና የምድብ ቦታ ካርዳቸውን ወደ ስብሰባው ይዘው መምጣት ያስፈልጋቸዋል። እነሱ የሚካፈሉበት የወረዳ ስብሰባ በሚደረግበት ጊዜ ቢያንስ ቢያንስ ስድስት ወር የሞላቸው አቅኚዎች ካርዳቸውን ካሳዩ ለአንድ ስብሰባ ብቻ የምግብ ቲኬቶች ያገኛሉ። ስለዚህ ካርዶቹን እንደ ገንዘብ አድርጋችሁ በጥንቃቄ ያዟቸው። በስብሰባው ላይ ቢጠፋባችሁ ሌላ አይሰጣችሁም። በስጦታ የሚሰጡ አዲስ የወጡ ወይም በአቅኚ ዋጋ የሚወሰዱ ጽሑፎችን ከመጽሐፍ ክፍል ማግኘት የሚችሉትም የመታወቂያ ካርዳቸውን በማሳየት ነው። በቤቴል አገልግሎት ያሉትም የቤቴል መታወቂያቸውን በማሳየት ከእነዚሁ ዝግጅቶች ሊጠቀሙ ይችላሉ።
የፈቃደኝነት አገልግሎት፦ በስብሰባው ላይ ከእነዚህ ክፍሎች በአንዳቸው ውስጥ ለማገልገል ጊዜ ልትመድቡ ትችላላችሁን? ምንም ለጥቂት ሰዓታት ቢሆን ወንድሞችን ማገልገሉ ትልቅ እገዛ ሲሆን ከፍተኛ እርካታም ያመጣላችኋል። ልትረዱ የምትችሉ ከሆነ በስብሰባው ቦታ ለሚገኘው ለፈቃደኛ አገልግሎት ክፍል አስታውቁ። ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆችም ለስብሰባው መሳካት አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ይሁን እንጂ የሚሠሩት ከወላጆቻቸው ጋር ወይም ኃላፊነት ሊወስድ ከሚችል ሌላ ትልቅ ሰው ጋር መሆን አለበት።
የማስጠንቀቂያ ምክር፦ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉትን ነገሮች ንቁ ሆነን በመጠበቅ አላስፈላጊ ችግር እንዳይደርስብን ልንከላከል እንችላለን። ብዙውን ጊዜ ሌቦችና አንዳንድ ይሉኝታ የሌላቸው ሰዎች ከአካባቢያቸው ርቀው የመጡ ሰዎችን ያድናሉ። የተሽከርካሪዎቻችሁ በሮች ሁልጊዜ መቆለፋቸውን አረጋግጡ። እንዲሁም ሌሎች መስተዋቱን እንዲሰብሩ የሚጋብዛቸው ከውጭ ሊታይ የሚችል ነገር ትታችሁ አትሂዱ። ሌቦችና ኪስ አውላቂዎች ብዙ ሕዝብ የተሰበሰበበት ቦታ ይመቻቸዋል። ውድ ዋጋ ያላቸውን ማንኛቸውንም ነገሮች ቦታችሁ ላይ ትታችሁ መሄዳችሁ ጥበብ አይሆንም። አጠገባችሁ ያለው ሁሉ ክርስቲያን ለመሆኑ እርግጠኞች መሆን አትችሉም። ለምን እንዲፈተን ትጋብዙታላችሁ? ከውጭ የገቡ አንዳንድ ሰዎች ልጆችን አባብለው ለመውሰድ ሙከራ እንዳደረጉ የሚገልጹ ሪፖርቶች ደርሰውናል። ልጆቻችሁን ሁልጊዜ ከአይናችሁ አታርቋቸው።
ጉባኤዎች ለስብሰባው ጉዞ ብለው የተኰናተሯቸውን ወይም የተከራዩአቸውን ተሽከርካሪዎች ከልክ በላይ ላለመጫን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል። የቄሳርን ሕግ ከመጣስ ከዚያም አልፎ የወንድሞችንና የእህቶችን ሕይወት ለአደጋ ከማጋለጥ ወይም ተሽከርካሪውን ከመጠን በላይ በመጫን ወይም ወደ ስብሰባው ቦታ ቀደም ብላችሁ ለመድረስ ስትሉ ሹፌሩ በፍጥነት እንዲነዳ በማበረታታት ጥፋት ከመጋበዝ ይልቅ ለመጓጓዣ ተጨማሪ ገንዘብ ለማውጣት ተዘጋጅቶ መምጣት የተሻለ ነው። (ሮሜ 13:1–7፤ ዘዳ. 21:1–9) እንዲህ ባሉ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጓዙ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች አስፈላጊ ሲሆን ፍቅራዊ ምክር ከመስጠት ወደኋላ ማለት አይኖርባቸውም።