የ1994 “አምላካዊ ፍርሃት” የወረዳ ስብሰባ
1 የእምነት ሰዎች ከአቤልና ከኖህ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ‘አምላካዊ ፍርሃት’ አሳይተዋል። (ዕብ. 11:4, 7) አምላካዊ ፍርሃት ማሳየት ማለት “ፈጣሪን መፍራትና ለእርሱ ጥልቅ አክብሮት ማሳየት እንዲሁም እሱን ላለማሳዘን ጤናማ ፍርሃት መያዝ” ማለት ነው። (ማስ — 1፣ ገጽ 818) በዚህ ዓመት “አምላካዊ ፍርሃት” በተባለው የወረዳ ስብሰባ ላይ በመገኘት ይህ ጥልቅ አክብሮት እንዳለን እናሳያለን። በመላው ፕሮግራም ለመደሰት ከመክፈቻው መዝሙር እስከ መደምደሚያው ጸሎት ድረስ በዚያ ትገኛለህን?
2 በየዓመቱ የወረዳ ስብሰባ መድረሱን የምንጠባበቀው በጉጉት ነው። ምንም እንኳ የማይናቅ የግል ጥረትና ወጪ ቢጠይቅብንም የምናገኛቸው በረከቶች ግን ብዙ ናቸው። ወደቤታችን የምንመለሰው ደስ ብሎን፣ ረክተንና በመንፈሳዊ ታንጸን ነው። (ከ1 ነገ. 8:66 ጋር አወዳድር።) አብረን መዋላችን የሚያነቃቃ ከመሆኑም በላይ ስብሰባው ከዘወትሩ ሩጫችን ለውጥ ይሆንልናል። ይሁን እንጂ የምንሰበሰበው ይሖዋን ለማምለክ እንደሆነ አስታውሱ። እንዲህ እንድናደርግ አዝዞናል። ራሳችንን እንዴት መጥቀም እንደምንችል እያስተማረን ነው። — ዘዳ. 31:12, 13፤ መዝ. 122:1
3 ፕሮግራሙ ዓርብ ጠዋት በ4:20 ተጀምሮ እሁድ ከሰዓት በኋላ በ10:15 ገደማ ይጠናቀቃል። ቅዳሜና እሁድ ፕሮግራሙ በ3:30 ይጀምራል። ጠዋት 1:30 በሩ ይከፈታል። ከዚህ ቀደም ብለው እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው ሥራ እንዲሠሩ የተመደቡ ብቻ ናቸው።
4 ለይሖዋ ያለን ጥልቅ አክብሮት በስብሰባው ላይ እንድንገኝ ግድ ይለናል፦ ጳውሎስ የዕብራውያን ክርስቲያኖችን “በአምላካዊ ፍርሃትና በታላቅ አክብሮት ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት አቅርቡ” በማለት መክሯቸዋል። (ዕብ. 12:28 አዓት) የዚህ ዓመት የወረዳ ስብሰባችን ይህን እንድናደርግ እኛን ለመርዳት የተዘጋጀ ነው። በስብሰባው ላይ ለመገኘት ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ የሚፈታተኑ አንዳንድ እንቅፋቶች ያጋጥሙን ይሆናል። እንደ ተራራ መስለው የሚታዩትንም እንቅፋቶች እንኳ በይሖዋ እርዳታ ልንወጣቸው እንችላለን። (ማቴ. 17:20) ከዓርብ ጠዋት አንሥቶ እስከ እሁድ ከሰአት በኋላ በሚደረገው መላው የስብሰባው ፕሮግራም ላይ ለመገኘት በቂ የእረፍት ቀናት ከሌሏችሁ ስለነገሩ በጸሎት አስባችሁበት አሠሪያችሁ ፈቃድ እንዲሰጣችሁ ጠይቃችሁታልን? (ያዕ. 1:6–8) ወላጆች በትምህርት ወቅት ስብሰባውን የሚካፈሉ ተማሪ ልጆቻቸውን የሃይማኖታዊ አምልኳቸው አስፈላጊ ክፍል በሆነው በዚህ ፕሮግራም ላይ ለመካፈል ሲሉ በትምህርት ገበታቸው ላይ እንደማይገኙ ለአስተማሪዎቻቸው በአክብሮት በማስረዳት ሊደግፏቸው ይገባል።
5 ያወጣኸው ወጪ መና አይቅር፦ ይህ ወጪ ምንድን ነው? ስብሰባውን ለመካፈል የምታጠፋው ጊዜና ጉልበት ነው። በዚህ ዓመት ለሚደረገው የወረዳ ስብሰባ ጥንቃቄ የተሞላበት እቅድ ስናወጣ የሰነበትነው ከአመዛኙ የፕሮግራሙ ክፍል ምንም ሳንጠቀም እሁድ ዕለት ወደቤታችን ለመመለስ ከሆነ ይህ ጥበብ የጎደለው ድርጊት ነው። ሌሎች የምሠራቸው ጉዳዮች አሉኝ በሚል ሰበብ ከተጠራህበት የእራት ግብዣ አቋርጠህ ትወጣ ነበርን? እንግዲያው ያገኘነው መንፈሳዊ ጉልምስናና አምላካዊ ፍርሃት ይሖዋ ካዘጋጀልን መንፈሳዊ ግብዣ የትኛውም ክፍል ቢሆን እንዲያመልጠን ሊፈቅድልን አይገባም። — ከ1 ቆሮ. 2:9, 10 ጋር አወዳድር።
6 አብዛኞቻችን ስብሰባው ሳያልቅ ተነሥተን ለመሄድ አናስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ የፕሮግራሙ ብዙ ክፍል ሊያመልጠን ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ከሚቀርቡት ክፍሎች የምንችለውን ያህል ጥቅም ለማግኘት የሚያስችለንን እቅድ አስቀድመን ባለማውጣታችን ነው። ጠዋት ጥሩ ቁርስ አድርገን ለመውጣትና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማከናወን የሚያስችለንን ጊዜ እንድናገኝ ማልደን ለመነሣት እንፈልጋለን። እንዲህ ከሆነ ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት በመቀመጫዎቻችን ላይ መገኘት እንችላለን። በሚቀጥለው ቀን ንቁ ሆነን ቀኑን ሙሉ የሚካሄደውን ፕሮግራም በትኩረት መከታተል እንችል ዘንድ ሌሊት ጥሩ እንቅልፍ ማግኘታችንም አስፈላጊ ነው።
7 ከፕሮግራሙ ይበልጥ ለመጠቀም የተሻለ ሆኖ የተገኘው ዘዴ አጫጭር ማስታወሻዎችን መያዝ ነው። ማስታወሻ መያዙ ለጎልማሶቹ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ለትንንሽ ልጆችም አስፈላጊ ነው። የ16 ዓመት ዕድሜ ያለው አንድ አስፋፊ እንዲህ ብሏል:- “በንግግሩ መሀል የሚጠቀሱትን ጥቅሶች እጽፋለሁ። ከዚያም ወደ ቤት ከተመለስኩ በኋላ ንግግሩን ለመከለስ እችላለሁ።” ሌላም የ16 ዓመት ወጣት እንዲህ በማለት አክሏል:- “ዋና ዋና ነጥቦቹን በአጭሩ እጽፋቸዋለሁ። ይህ አእምሮዬ ከመስመር እንዳይወጣ ይረዳኛል።” ለፕሮግራሙ የሚያስፈልጉን የተለመዱ ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ፣ የመዝሙር መጽሐፍ፣ መጠነኛ ይዘት ያለው የማስታወሻ ደብተርና እርሳስ ወይም ብዕር ናቸው። እርግጥ ትንንሽ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያስፈልጉትን ነገሮች ማድረግ ቢችሉም ከመጠን በላይ ብዙ ዕቃዎችን በመቆለል በራሳችንና በሌሎች ላይ ችግር አለመፍጠራችን ይመረጣል።
8 አንዳንድ ወንድሞች ቤታቸው ሲመለሱ ደግመው ለመከታተል እንዲያስችላቸው በድምጽ መቅጃ መሣሪያዎች ወይም የቪዲዮ ምስል መቅረጫዎችን በመጠቀም ፕሮግራሙን ይቀረጻሉ። አንድ ሰው ይህን ማድረጉና አለማድረጉ የግል ውሳኔው ነው። ነገር ግን የአንዳንዶች ተሞክሮ እንዳሳየው ከሆነ ወደ ዘወትሩ የኑሮ እንቅስቃሴያቸው ከተመለሱ በኋላ የቀረጹትን መልሰው ለማየት ጊዜ አይኖራቸውም። ከዚህም በተጨማሪ የመቅጃ መሣሪያዎችን ሲያስተካክሉ በመሀል አንዳንድ ቁልፍ ነጥቦች ሊያመልጧቸው ይችላሉ።
9 ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት በመቀመጫችን ላይ ለመገኘት ልባዊ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ፕሮግራሙ ሊጀምር እንደሆነ የስብሰባው ሊቀመንበር ሲያስታውቅ ቀድሞ ከምናውቃቸው ወዳጆቻችን ጋር አስደሳች ተሞክሮዎችን እየተለዋወጥንም ቢሆን ጭውውታችንን ወዲያውኑ አቁመን ወደ መቀመጫችን መመለሳችን ፕሮግራሙን ለሚመሩትና ለቀሩት ወንድሞቻችን ያለንን አክብሮት ያሳያል።
10 የይሖዋ የተትረፈረፈ በረከት ስለሚዘንብባቸው የወረዳ ስብሰባዎች ሁልጊዜ በደስታ የሚያስፈነድቁ አጋጣሚዎች ናቸው። መንፈሳዊና ሥጋዊ ጥቅሞችን እናገኝባቸዋለን። ለመሰብሰቢያው ቦታ ኪራይ ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ እንደሚደረግ መታወስ ይኖርበታል። የምግብ ዋጋ እየናረ ሄዷል። እንዲሁም ማኅበሩ በየወረዳ ስብሰባዎች ላይ ጥሩ ምግቦችን ገዝቶ ያቀርባል። እነዚህና ሌሎቹም ወጪዎች የሚሸፈኑት እንዴት ነው? በፈቃደኝነት በምናደርገው እርዳታ ነው። ይህም ‘ለይሖዋ ክብር እንድናመጣና ወደ አደባባዮቹም ስጦታን እንድናስገባ’ ከሚያበረታታን የመዝሙር 96:8 መንፈስ ጋር የሚስማማ ነው።
11 ጠባይህ ስሙን ያስመሰግናልን? በየዓመቱ የጥቅምት ወር የመንግሥት አገልግሎታችን በወረዳ ስብሰባ ላይ ስንገኝ ጥሩ ጠባይ ማሳየታችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በደግነት ያሳስበናል። እርግጥ ነው፤ በጠባያችን ምን ጊዜም ለሌሎች ምሳሌ መሆን ይኖርብናል፤ ሆኖም በብዙ ቁጥር አንድ ላይ ስንሰበሰብ ከእውነት ውጭ ባሉ ሰዎች ዓይን ውስጥ በቀላሉ እንገባለን። ጠባያችን ጥሩም ይሁን መጥፎ ከስብከታችን የጎላ ድምጽ አለው። በምንናገረውና በምናደርገው ነገር ይሖዋ እንዲመሰገን እንፈልጋለን። — ምሳሌ 27:2፤ 1 ጴጥ. 2:12
12 ያለፈው ዓመት “መለኮታዊ ትምህርት” የተባለው የወረዳ ስብሳባ ሲጠናቀቅ አንድ የጸጥታ አስከባሪ በአንድ ቦታ ስለታዘበው ነገር ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “እነዚህ እስከ ዛሬ ካየኋቸው ልጆች ሁሉ የተሻሉ ልጆች ናቸው።” ስለ ሌሎች ወጣቶች መጥፎ ጠባይና አጥፊነት ከተናገረ በኋላ ስለ ምሥክሮቹ ልጆች እንዲህ በማለት ቀጠለ:- “የታረሙ ናቸው ከእነርሱ ጋር መሆን ያስደስታል። እዚህ የሚደረጉት ሌሎች ስብሰባዎችም እንዲህ ቢሆኑ እንዴት ደስ ባለኝ።”
13 አንድ የጋዜጣ አምድ አዘጋጅ ስለ ስብሰባው ያስተዋሉትን ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “ሴቶችና ልጃገረዶች የሚያማምሩ ልብሶች ለብሰዋል፣ አዋቂዎችና ወንዶች ልጆች ኮትና ክራቫት አድርገዋል። የአራቱንም ቀን ተናጋሪዎች በትኩረት በመከታተል ማስታዎሻ ይጽፋሉ። ንጽሕና ከአምላካዊ አክብሮት ቀጥሎ የሚታይ ነገር ከሆነ ከማንኛውም ሰው ይበልጥ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ጉዳይ ወደ አዲስ ምዕራፍ አድርሰውታል።”
14 ወላጆች ልጆቻቸው በስብሰባው ወቅት ወዲያና ወዲህ እየተሯሯጡ እንዳይረብሹ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጧቸው ይገባል። ያለማቋረጥ በኮሪደሮች ላይ መሯሯጣቸው ሁካታ ስለሚፈጥር ለማዳመጥ የሚጥሩትን ሰዎች ሀሳብ ሊከፋፍልባቸው ይችላል። ጥቂቶች በፕሮግራሙ መሀል የሚያከናውኗቸው ነገሮች ይኖሯቸው ይሆናል፤ ሌሎቻችን ግን ቦታችንን ይዘን በትኩረት ማዳመጥ አይገባንምን?
15 አብዛኞቹ ወላጆች ልጆቻቸው በየሳምንቱ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘታቸውን በመከታተል ረገድ ጥብቅ ናቸው። ታዲያ ልጆቻቸው በፕሮግራሙ ወቅት በኮሪደሮች ላይ ወዲያና ወዲህ እያሉ እንዳይረብሹና አጠገባቸው ቁጭ ብለው እንዲያዳምጡ በማድረግ በኩልስ የዚያኑ ያህል ጥብቅ መሆን የለባቸውምን? የወረዳ ስብሰባ የሚደረግበት ቦታ እንደ ትልቅ የመንግሥት አዳራሽ ተደርጎ የሚታይ ነው። ይሁንና ያለነው በሰይጣን ሥርዓት ውስጥ በመሆኑ መጥፎ አላማ ይዘው ወደዚያ የሚገቡ ይሉኝታ የለሽ ሰዎች ይኖራሉ። በማንኛውም ጊዜ ልጆቻችሁ የት እንዳሉና ምን እያደረጉ እንዳሉ ማወቅ ይኖርባችኋል።
16 አለባበስ፣ አበጣጠርና አጋጌጥ፦ የምንኖረው የግዴለሽነትና የተዝረከረከ አለባበስ ተቀባይነት ባገኘበት ጊዜ ላይ ነው። ብዙ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያንና የሙዚቃ ትርዒት ወደሚታይባቸው ቦታዎች ሲሄዱ ወይም ሆቴል ቤት ሲገቡ የሚለብሱት ልብስ ቅጥ ያጣና የተዝረከረከ ነው። በአንቀጽ 14 ላይ የተሰጠው አስተያየት እንደሚያሳየው ከአምልኮ ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ መንገድ አሁንም ቢሆን ሥርዓታማ አለባበስን ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች አሉ። የተዝረከረከና የግዴለሽነት አለባበስ እንዲሁም ተገቢ ያልሆነ የጸጉር አበጣጠር ስለ እኛ ብዙ ይናገራል። የመሰብሰቢያ ሕንፃው በዚያን ወቅት የስፖርት ሜዳ ያለመሆኑን አስታውሱ። ሰፊ የመንግሥት አዳራሽ ነው። አንዳንዶች ስብሰባው ላይ ሲገኙ ለስብሰባው አክብሮት እንዳላቸው የሚያሳይ ልብስ ለብሰው ይመጡና የቀኑ ፕሮግራም ካለቀ በኋላ ወደሌሎች ቦታዎች ሲሄዱ ተገቢ ያልሆነና ልከኝነት የጎደለው ልብስ ይለብሳሉ።
17 የጥምቀት እጩዎች አንዳንድ የልብስ ዓይነቶች ለሁኔታው የማይስማሙ ስለመሆናቸው ማሳሰቢያ ሊሰጣቸው ይገባል። ልብሱ ልከኛና ተመልካችን ቅር የማያሰኝ መሆን አለበት። ይህን መወሰን የሚገባው ማን ነው? ሽማግሌዎች ከጉባኤያቸው ተጠማቂዎች መካከል ማናቸውም ለሌሎች የመሰናከያ ምክንያት እንዳይሆኑ የመከታተል ኃላፊነት አለባቸው። (2 ቆሮ. 6:3, 4) ይህም ሰውነትን የሚያሳይ የዋና ልብስ ወይም እርጥበት ሲነካው ልከኝነቱን የሚቀይር እንዲሁም አለማዊ መፈክሮች ወይም የንግድ ማስታወቂያዎች ያሉባቸው ካናቴራዎችን (ቲ–ሸርቶች) ማስቀረት ማለት ይሆናል። ሽማግሌዎች አገልግሎታችን በተባለው መጽሐፍ ላይ የሚገኙትን ጥያቄዎች ሲከልሱለት በዚህ ጉዳይ ላይም ከጥምቀት እጩው ጋር መወያየታቸው ተገቢ ይሆናል።
18 የድምፅና የምስል መቅረጫ መሣሪያዎች፦ ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው የመቅረጫ መሣሪያዎች በተለይም የቪድዮ ካሴት መቅረጫዎችን መጠቀሙና አለመጠቀሙ የእያንዳንዱ ሰው የግል ውሳኔ ነው። ለመቅረፅ ከወሰናችሁ እባካችሁን በዙሪያችሁ ለሚገኙት ሰዎች አሳቢነት አሳዩ። የሚቀርጸው ሰው ቦታው ላይ እያለም ቢሆን እንኳ የሌሎችን ሐሳብ ሊከፋፍል ይችላል። ማንም ሰው ፕሮግራሙን ለመቅዳት ሲል የተሰበሰቡትን ሰዎች እይታ መጋረድ የለበትም። የትኛውም ዓይነት የመቅረጫ መሣሪያ በስብሰባው ቦታ ካለው የኤሌክትሪክ መስመር ወይም የድምጽ ማስተላለፊያ መሣሪያ ጋር እንዲያያዝ የማይፈቀድ ከመሆኑም በላይ ክፍት የተተዉ መተላለፊያዎችን ወይም መንገዶችን መዝጋት አይኖርባቸውም።
19 መቀመጫዎች፦ ከመቀመጫ ጋር የተያያዙ ችግሮች አሁንም ትኩረት ይሻሉ። መቀመጫ መያዝ የሚፈቀደው ለቤተሰባችሁና ከእናንተ ጋር በመኪናችሁ አብሮ ለሚጓዝ ሰው ብቻ መሆኑን ለሁላችሁም ደግመን ልናሳስባችሁ እንወዳለን። በአንዳንድ የወረዳ ስብሰባዎች ላይ በ1:30 በሩ ሲከፈት ወንድሞችና እህቶች ወደ ሕንፃው ግር ብለው ሲገቡ ተስተውሏል። ብዙዎች በመደዳ ያሉ መቀመጫዎቹን ያዙ፤ ነገር ግን ሁሉም ላይ ሰው አልተቀመጠበትም ነበር። ያላሰለሰ ማሳሰቢያ ቢሰጥም እንኳ ይህ ዓይነቱ አሳቢነት የጎደለው ድርጊት የቀጠለ ይመስላል። በዚህ ረገድ ልባችንን መመርመርና በፊልጵስዩስ 2:3, 4 ላይ ባሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ማሰላሰል አይገባንምን?
20 በእያንዳንዱ የወረዳ ስብሰባ ላይ ለየት ያለ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው አረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች ልዩ ቦታ እንዲዘጋጅላቸው ማበረታቻ ይሰጣል። እባካችሁ በዚህ ቦታ ለመቀመጥ የማይገባችሁ ከሆነ ለእነዚህ ወንድሞችና እህቶች የተመደበውን ቦታ እንዳትይዙባቸው ተጠንቀቁ። እንዲሁም እነርሱን ለመርዳት ኃላፊነት የወሰደ ሰው አብሯቸው ከሌለ እነዚህን ልዩ እንክብካቤ የሚፈልጉ ሰዎች መቀመጫ እንዲያገኙ ለመርዳት ንቁዎች ሁኑ።
21 የጽሑፍና የምግብ አገልግሎት፦ በወረዳ ስብሰባዎች አንድ ላይ ስንሰበሰብ የተትረፈረፈ ሥጋዊና መንፈሳዊ ምግብ አግኝተን እንደሰታለን። ሁለቱንም ቢሆን በአመስጋኝነት መቀበል አለብን፤ ምንም ነገር መባከንም አይኖርበትም። (2 ዜና. 31:10፤ ምሳሌ 3:10፤ ዮሐ. 6:12) እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ አሁንም የምግብ ትኬቶችን ቀደም ብላችሁ እንድትገዙ ሐሳብ እናቀርብላችኋለን። ከአሁን ጀምራችሁ ለጽሑፍ የሚሆን ገንዘብ ለማጠራቀም ዕቅድ ልታወጡ ትችላላችሁ። ምግብና ጽሑፍ ለመውሰድ በምትሰለፉበት ጊዜ እባካችሁ ለሌሎች ፍቅራዊ አሳቢነት አሳዩ።
22 ከጥቂት ሳምንታት በኋላ “አምላካዊ ፍርሃት” የተባለው የወረዳ ስብሰባ መካሄድ ይጀምራል። የምታደርጉትን ዝግጅት አጠናቃችሁ በሦስቱ ቀናት የወንድማማች ኅብረትና መልካም መንፈሳዊ ነገሮች ለመደሰት ተዘጋጅታችኋልን? ‘በአምላካዊ ፍርሃት’ የወረዳ ስብሰባ ላይ ከተዘጋጀው የይሖዋ የመልካም ነገሮች ማዕድ ለመመገብ የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ እንዲባርክለችሁ ልባዊ ጸሎታችን ነው።