የጥያቄ ሣጥን
◼ በአደገኛ የአገልግሎት ክልል ውስጥ ስንሠራ ምን ጥንቃቄ እንድናደርግ ይፈለግብናል?
1 በተለይ በከተማዎች ረብሻዎች፣ ዝርፊያዎችና ማኅበረሰባዊ ብጥብጦች እንደ ደረሱ የምንሰማቸው ወሬዎች እየጨመሩ ነው። ይህ ሁኔታ ቢያሳስበንም ረብሻ በበዛባቸው ቦታዎችም እንኳን የመንግሥቱን መልእክት የሚቀበሉ ቅን ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን። ስለዚህ በተገቢው ጊዜ በይሖዋ ጥበቃ በመተማመን አገልግሎታችንን በቁርጠኝነት ለመቀጠል መድፈር አለብን። — ምሳሌ 29:25፤ 1 ተሰ. 2:2
2 አደጋ ሊያስከትሉ ወደሚችሉ ቦታዎች ስንሄድ ይሖዋ ጥንቁቅ እንድንሆንና በጥሩ የማመዛዘን ችሎታ እንድንጠቀም ይጠብቅብናል። ንቁ ሁን። “ብልህ ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጎዳሉ።” (ምሳሌ 22:3) ተሞክሮ ያላቸው አስፋፊዎች አስፈላጊ ሲሆን አንድ ላይ የመሥራትን ጥበብ ይገነዘባሉ። መክብብ 4:9, 12 “አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል። አንዱም አንዱን ቢያሸንፍ ሁለቱ በፊቱ ይቆማሉ” ሲል ይገልጻል።
3 በሕንፃዎች ውስጥ ጨለም ባሉ መተላለፊያዎችና ጭር ባሉ ደረጃዎች አካባቢ ስትሄድ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርግ። አንድ ቤት ወይም አፓርታማ ውስጥ እንድትገባ ስትጋበዝ ተጠንቀቅ። ከሚዝቱ ወይም ጥል የሚፈልጉ ከሚመስሉ ሰዎች ጋር አትከራከር። ያጋጠሙህ ሰዎች ኃይማኖታዊ አክራሪ ካልሆኑ ቶሎ ብለህ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ እንደሆንክ ግለጽ። አንዳንድ አስፋፊዎች ማንነታቸውን ለማሳወቅ ሲሉ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም መጠበቂያ ግንብ ወይም ንቁ! በእጃቸው ይይዛሉ።
4 ሥራ ፈትተው በአካባቢው የሚዘዋወሩትን ሰዎች በትኩረት ተከታተል። ውድ የሆኑ ጌጣ ጌጦችን አታድርጉ። በምሽት የምትወጣ ከሆነ ጥቂት መንገደኞች ብቻ ባሉበት ጨለማ መንገዶች ከመሄድ ተቆጠብ። ዘራፊዎች ከመጡብህ የሚፈልጉት የአንተን ገንዘብና ንብረት ብቻ ከሆነ አትከላከል፤ ሕይወትህ ካሉህ ንብረቶች ሁሉ ይበልጥ ውድ ነው። — ማር. 8:36
5 አንዳንዴ አደጋው የሚመጣው ከቤት ወደ ቤት እየሄድን የምናደርገውን አገልግሎት ከማይወዱ ኃይማኖታዊ አክራሪዎች ነው። መከራከር አንፈልግም። (1 ጢሞ. 2:24) በቀላሉ አድማ የሚፈጠሩባቸውን ሁኔታዎች በጥበብ እንርቃለን። (ምሳሌ 17:14) ለምሳሌ በአንዳንድ የአገልግሎት ክልሎች የቡድን ምሥክርነት መስጠት ጥሩ ላይሆን ይችላል። (ማቴ. 10:16) ወጣት አስፋፊዎች ከትልልቆች ጋር ማገልገል አለባቸው። የኃላፊነት ቦታ ያላቸው ወንድሞች የአገልግሎት ክልል የወሰዱ አስፋፊዎችን ለመከታተል ንቁ መሆን አለባቸው። አብዛኛውን ጊዜ ሌሎች አጠገባችን ቢሆኑ ይመረጣል። በአካባቢው አንድ ዓይነት ዓመፅ ወይም ረብሻ ከተፈጠረ ቡድኑ በፍጥነት የአገልግሎት ክልሉን ለቆ መውጣት አለበት።
6 ንቁና ጥንቁቅ ከሆንን በአደገኛ ቦታዎች ያሉትን ‘አሁን እየተሠራ ስላለው ርኩሰት ሁሉ የሚያለቅሱና የሚተክዙ ሰዎችን’ መርዳታችንን ልንቀጥል እንችላለን።— ሕዝ. 9:4