መንግሥቲቱ ያስገኘችልንን አንድነት መጠበቅ
1 የአምላክ መንግሥት ኃይልና ሥልጣን ያላት እውን መስተዳድር ናት። ይህች መንግሥት የኢየሱስ ስብከት ዋነኛ ርዕስ ነበረች። (ማቴ. 4:17) ሌሎችን ማስተማርና ስለ መንግሥቲቱ እውነት መመሥከር የኢየሱስ አገልግሎት ዋነኛ ክፍል ነበር። መንግሥቲቱ እንድትመጣ እንድንጸልይና እርሷን አስቀድመን መፈለጋችንን እንድንቀጥል አስተምሮናል። (ማቴ. 6:9, 10, 33) ከይሖዋና ከድርጅቱ ጋር ተጣብቆ መቀጠል፣ የስብከት ተልእኳችንን መፈጸምና ምን ጊዜም ከዓለም ገለልተኛ መሆን መንግሥቲቱ ያስገኘችልንን አንድነት ጠብቀን ለመኖር ያስችለናል። ከመንግሥቲቱ ጎን የቆምን መሆናችንን በድርጊታችንም ሆነ በንግግራችን እናሳያለን።— ዮሐ. 18:37
2 ከ1914 ጀምሮ መንግሥቲቱ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ዜጎቿ እውን እየሆነች መጥታለች። በእነዚህ የመንግሥቲቱ ዜጎች መካከል ያለው አንድነት በዚህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ እጅግ ደምቆ ይታያል። መንግሥቲቱ አንድነት የምታመጣ ኃይል እንድትሆን ከተፈለገ በሕይወታችን ውስጥ እውን ሆና እንድትታይ ማድረግ አለብን። እውን እንድትሆንልን የሚያደርጋት ምን ድን ነው?
3 እንደ ሌሎቹ መስተዳድሮች ሁሉ መንግሥቲቱም ብዙ ሕጎች አሏት። ሆኖም ሕጎቿ የሚገኙት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመሆኑ ከሌሎቹ ትለያለች። የመንግሥቲቱ ዜጎች እንደመሆናችን መጠን የአምላክን ቃል ዘወትር ማንበባችን ምን ማድረግ እንዳለብን ተገቢውን ማሳሰቢያ ይሰጠናል። በጽሑፎቻችን ላይ የሚደረግ የግል ጥናትና “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚሰጣቸው መመሪያዎች የአምላክን ሕጎች በዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ እንድናደርግ ይረዱናል። (ማቴ. 24:45) በግለሰብ ደረጃ እንዲህ ዓይነቱን ትጋት እያሳየን በሄድን መጠን መንግሥቲቱ የበለጠ ሕያው እየሆነችልን ትመጣለች፣ በዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ የበለጠ በመቀራረብ በኢየሱስ አገዛዝ ሥር በአምልኮ አንድነት ያለው አንድ ቤተሰብ እንሆናለን።
4 በመንግሥቲቱ ስብከት የሚገኝ አንድነት፦ ተልእኳችን የመንግሥቲቱን ምሥራች “እስከ ምድር ዳር ድረስ” መስበክ ነው። (ሥራ 1:8) “በአንድ ልብ” ሆነን የምናደርገው ስብከት ይሖዋን ‘ለማክበር’ በምናደርገው ጥረት ያስተባብረናል። (ሮሜ 15:5, 6) ከዓለም አቀፍ የሥራ ባልደረቦቻችን ጋር በቅንዓት መተባበር እምነታችንን ያጠነክርልናል እንዲሁም የይሖዋ መንፈስ ፈቃዱን ለመፈጸም በእኛ በኩል እንዲሠራ ያደርጋል። ‘ሁልጊዜ የጌታ ሥራ የበዛልን መሆናችን’ ‘የምንደላደል የማንነቃነቅ’ ያደርገናል።— 1 ቆሮ. 15:58
5 በብዙ አገሮች ሰይጣን በስብከቱ ሥራ ላይ እንቅፋቶችን በመፍጠር አንድነታችንን ለመበጥበጥ ይሞክራል። ሰይጣን ጠብ በመዝራት አለመግባባት ለመፍጠርና ብጥብጥ ለማነሳሳት ማንኛውንም ዘዴ ይጠቀማል። (ምሳሌ 6:19፤ ገላ. 5:19–21, 26) በዓለም ግጭቶች መካከል ጣልቃ እንድንገባና አልፎ ተርፎም በፖለቲካና በማኅበራዊ ንትርክ የአንዱ ወገን ደጋፊ እንድንሆን ይፈልጋል። (ያዕ. 3:14–16) ቅዱሳን ጽሑፎች የሱን ተጽዕኖ እንድንቃወም አጥብቀው ይመክሩናል፤ አለበለዚያ አድኖ ይውጠናል። (1 ጴጥ. 5:8, 9) የመንግሥቲቱ ተስፋ እውንነት ከልባችንና ከአእምሯችን እንዲደበዝዝ መፍቀድ የለብንም።
6 አንድነታችንን ጠብቆ ለመቆየት ጤናማ አስተሳሰብ መያዝንና ላይኛይቱን ጥበብ ማግኘትን ያጠቃልላል። አንዳንድ ችግሮች ሲነሱ በተለይ ደግሞ ወንድሞቻችንን የሚጨምሩ ከሆኑ ሰላም እንዳይደፈርስ የመንፈስ ፍሬን ማሳየት አለብን። እንደ ኩራት፣ ቅንዓትና ራስ ወዳድነት ያሉትን የሚከፋፍሉ ዓለማዊ ባሕርያት ማሸነፍ አለብን። (ኤፌ. 4:1–3፤ ቆላ. 3:5–10, 12–14) አእምሯችንን ጠቃሚና ገንቢ በሆኑ ሐሳቦች ልንሞላው ይገባል። መንግሥቲቱ በሕይወታችን ውስጥ እውን ናት! ይህን አመለካከታችን እንደያዝን ለመቀጥል ንቁዎች መሆን ይገባናል!— ኤፌ. 6:11, 13
7 አስደናቂ የሆነው የመንግሥቱ ተስፋችን እውን ሲሆንልን ለዘላለም በአንድነት ያስተሳስረናል።— መዝ. 133:1