የጥያቄ ሣጥን
◼ በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናትና የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ጊዜ አንቀጾቹን ማን እንዲያነብ ማድረግ ይቻላል?
የሐምሌ 1977 እና የሰኔ 1980 የመንግሥት አገልግሎታችን ለአንባቢነት እነማን ብቁ እንደሚሆኑ ሐሳብ ሰጥቷል። የተጠመቁ ወንድሞች የሚገኙ ከሆነ እነሱ እንዲያነቡ ማድረግ ይቻላል። ችሎታ ካላቸው ሽማግሌዎች፣ ዲያቆናትና በጉባኤ ውስጥ ካሉ የተጠመቁ ወንድሞች መካከል መመረጥ ይኖርባቸዋል። በአንባቢነት የተመደቡ ሁሉ በትክክል በማጥበቅና ድምፅን በመለዋወጥ ሳይደነቃቀፉ ሊያነቡ ይገባል። ስሜት የሚቀሰቅሱና በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ ምዕራፍ 6 ላይ ያለውን ተገቢ የንግግር ጥራት ሊያሳዩ ይገባቸዋል። (ከነህምያ 8:8 ጋር አወዳድር።) በጠባያቸውም ለሌሎች ምሳሌ ሊሆኑ ይገባቸዋል።
የመጽሐፍ ጥናት ከሌሎች የጉባኤ ስብሰባዎች ጋር ሲነጻጸር የተሰብሳቢዎች ቁጥር አነስተኛ ስለሆነ አንባቢ ሊሆን የሚችል የተጠመቀ ወንድም ሁልጊዜ ላይገኝ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ የጥናቱ መሪ አንቀጾቹን ራሱ ለማንበብ ሊወስን ወይም ብቃት ያላት የተጠመቀችና በደንብ ማንበብ የምትችል እህት እንድትረዳው ሊጠይቅ ይችላል። የምታነበው እህት ከሆነች በማስተማር ቦታ ላይ ስላልሆነች የራስ መሸፈኛ ማድረግ አያስፈልጋትም። ማድረግ እንዳለባት የሚሰማት ከሆነ ግን ልታደርግ ትችላለች።
በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ግን ብዙ ጊዜ ብቃት ያላቸው አንባቢ ወንድሞች ይገኛሉ። የመጠበቂያ ግንብ ጥናት መሪው የአንባቢዎቹን ፕሮግራም አስቀድሞ ማውጣትና በማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ መለጠፍ ይገባዋል። በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ጊዜ አንባቢ ሆነው ሊመደቡ የሚገባቸውን መምረጥ የጠቅላላው የሽማግሌዎች አካል ኃላፊነት ነው። አንድ ወንድም በጥሩ ሁኔታ የማያነብ ከሆነ የመጠበቂያ ግንብ መሪው ቀዳሚ በመሆን አንዳንድ ምክሮችንና ድጋፍ ሊለግሰው ይገባል። አልፎ አልፎ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የአንባቢዎቹ የንባብ ጥራት ከፍተኛ ደረጃውን ጠብቆ እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ግምገማ ሊደረግ ይገባል። አንድ ወንድም ከአንባቢነት የሚወርድ ከሆነ ለምን እንደወረደና ወደፊት እንደገና ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ በየትኞቹ ብቃቶች ላይ ሊሠራባቸው እንደሚገባው ሊነገረው ይገባል።
አነስተኛ ቡድን በሆነው በጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ላይ የሚያነብም ሆነ ለጠቅላላው ጉባኤ በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ እንዲያነብ የተመደበ ወንድም የተሰጠውን ኃላፊነት በቁም ነገር ሊይዘው ይገባል። (1 ጢሞ. 4:13) “እውነተኛውን ቃል” በትክክል በሚያስተላልፍ በጥሩ ችሎታ በማንበብ በሚናገረው ነገር ላይ ያለውን ጽኑ እምነት ማሳየት ይገባዋል።— መክ. 12:10