አንተም ጥሩ ጥሩ ተሞክሮዎችን ልታገኝ ትችላለህ!
አንዳንድ አስፋፊዎች ሰዎችን ሲያነጋግሩ ወይም ተመላልሶ መጠየቅ ሲያደርጉ ያገኟቸውን አስደሳችና የሚያበረታቱ ተሞክሮዎች ይናገራሉ። ጥሩ ተሞክሮዎች እንዲሁ የሚገኙ ነገሮች አይደሉም። በአብዛኛው ጥሩ ተሞክሮዎች የሚገኙት በትጋትና ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ነው። ጥሩ ችሎታና የአነጋገር ቅልጥፍና ላላቸው አስፋፊዎች ብቻ የተወሰኑ አይደሉም።
አንዳንዶች በጣም የተሳካላቸው የሚከተሉትን ነገሮች በማድረጋቸው መሆኑን ለማስተዋል ተችሏል:- (1) በእያንዳንዱ ሳምንት በተደጋጋሚ ወደ መስክ አገልግሎት በመውጣት ያለማቋረጥ በዚህ የመካፈል ልማድ አላቸው። ይህም ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ጋር እንዲገናኙ ብዙ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል፤ (2) አስቀድመው የቤቱ ባለቤት ጥሩ ምላሽ አይሰጥም ብለው ከመደምደም ይልቅ ይሆናል የሚል አመለካከት በመያዝ የቤቱን ባለቤት ያነጋግራሉ፤ (3) በቀላሉ ከሰዎች ጋር የመግባባት ችሎታ ያላቸውና ለሚያዳምጧቸው ሰዎች ሞቅ ያለ መንፈስና እውነተኛ የመርዳት ፍላጎት ያላቸው ናቸው፤ (4) ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግና እቤት ያላገኟቸውን ሰዎች በድጋሚ ሄደው ለማነጋገር የማይታክቱና ጽኑ ናቸው፤ (5) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማስጀመር ግብ አላቸው።
የአገልግሎት እንቅስቃሴህን ከመረመርክ በኋላ እነዚህን የመሰሉ አስደሳች ተሞክሮዎችን ማግኘት የምትችልበትን መንገድ ልትገነዘብ ትችል ይሆናል። ይህም አገልግሎቱን ይበልጥ ፍሬያማና አርኪ ያደርግልሃል።