በይሖዋ መመርመሩ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
1 ሁሉም ሰው ጥሩ ጤንነት እንዲኖረው ይፈልጋል። ጥሩ ጤንነት ሕይወትን የበለጠ አስደሳች ያደርገዋል። ይሁንና ጥሩ ጤንነት ያላቸው ብዙ ሰዎችም አልፎ አልፎ የጤና ምርመራ ያደርጋሉ። ይህን የሚያደርጉት ለምንድን ነው? በውስጣቸው ያቆጠቆጡ የጤና ችግሮች ሳይባባሱ ተደርሶባቸው መፍትሔ እንዲያገኙ ስለሚፈልጉ ነው። መንፈሳዊ ጤንነታችንን መንከባከብ ደግሞ ከዚህ ይበልጥ አንገብጋቢ ነው። በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ማግኘታችን የተመካው “በእምነት ጤናሞች” ሆነን በመቀጠላችን ላይ ነው።— ቲቶ 1:13 አዓት
2 በይሖዋ የምንመረመርበት ጊዜው አሁን ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ በተቀደሰው መቅደሱ ሆኖ የሁሉንም ሰዎች ልብ እየመረመረ ነው። (መዝ. 11:4, 5፤ ምሳሌ 17:3) ልክ እንደ ዳዊት “አቤቱ፣ ፍተነኝ መርምረኝም፤ ኩላሊቴንና ልቤን ፍተን” በማለት ይሖዋ አንድ በአንድ እንዲመረምረን እንጠይቀዋለን።— መዝ. 26:2
3 ሥጋችን ፍጹም ስላልሆነ ከውስጣችን ሊመነጩና መንፈሳዊ ጤንነታችንን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ነገሮች መጠንቀቅ አለብን። ምሳሌ 4:23 “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና” በማለት ምክር ይሰጣል።
4 በተጨማሪም መንፈሳዊ ጤንነታችን ዙሪያችንን ከከበበን ሥነ ምግባር ከጎደለው የነቀዘ ዓለም ጉዳት ሊደርስበት ይችላል። ከዚህ ክፉ ሥርዓት ጋር በጣም ከተቀራረብን አስተሳሰቦቹን ማንጸባረቅና ዓለማዊ ዝንባሌዎችን ማሳየት ልንጀምር እንችላለን። ወይም ደግሞ ዓለማዊ አኗኗር ልንመርጥና በዓለም መንፈስ ልንሸነፍ እንችላለን።— ኤፌ. 2:2, 3
5 ሰይጣን መንፈሳዊነታችንን ለማጥፋት ስደት ወይም ቀጥተኛ ተቃውሞ በማምጣት ሊጠቀም ይችላል። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ እኛን ለማባበል የሚጠቀመው በዓለማዊ ማታለያዎች ነው። ሰይጣን “የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ” ስለሚዞር ‘የማስተዋል ስሜታችንን እንድንጠብቅና ንቁዎች እንድንሆን’ ጴጥሮስ አጥብቆ አሳስቦናል። ‘በእምነት ጸንተን እንድንቃወመው’ ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል።— 1 ጴጥ. 5:8, 9 አዓት
6 እምነታችንን በየዕለቱ እየገነባን በእምነት ጠንካሮች ሆነን በመኖር መንፈሳዊ ጤንነታችንን መጠበቅ ያስፈልጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ሳናቋርጥ እምነታችንን እንድንፈትን መክሮናል። አንድ ጥሩ ችሎታ ያለው ዶክተር የሚሰጠንን ሊሠሩ የሚችሉ ምክሮች እንደምንከተል ሁሉ ይሖዋ የሚያደርግልን መንፈሳዊ ምርመራ መስተካከል የሚያስፈልገው ችግር እንዳለ ሲጠቁም ይሖዋን እናዳምጠዋለን። ይህም ‘እየተስተካከልን ለመቀጠል’ ያስችለናል።— 2 ቆሮ. 13:5, 11 አዓት
7 በእርግጥም ከይሖዋ የበለጠ መርማሪ የለም። የምርመራው ውጤት ሁልጊዜ ትክክል ነው። የሚያስፈልገን ምን እንደሆነ በትክክል ያውቃል። በቃሉ እንዲሁም ‘በታማኝና ልባም ባሪያው’ በኩል ለጤንነት የሚጠቅም መንፈሳዊ ምግብ ያዝልናል። (ማቴ. 24:45፤ 1 ጢሞ. 4:6) በቤትና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተን ከዚህ የተመጣጠነ መንፈሳዊ ምግብ ሳናሰልስ መመገባችን በመንፈሳዊ ጤናሞች ሆነን ለመቀጠል ያስችለናል። በአገልግሎትና በሌሎች ክርስቲያናዊ ሥራዎች ዘወትር መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ማድረጉም ጠቃሚ ነው። ስለዚህ ይሖዋ የተሻለ መንፈሳዊ ጤንነት ይዘን ለመቀጠል እንደሚረዳን በመተማመን ዘወትር የሚያደርግልንን ምርመራ በደስታ እንቀበላለን።