ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉት
1 ከውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር አንድ ላይ መሆን ምንኛ መንፈስን የሚያድስ ነው! (1 ቆሮ. 16:17, 18) በጉባኤ ስብሰባዎች፣ በወረዳ ወይም በልዩ ስብሰባዎች፣ በአውራጃ ስብሰባዎችና በመስክ አገልግሎት ላይ አብረናቸው እንሆናለን። አልፎ አልፎ እቤታችን በእንግድነት ሲመጡም ከእነርሱ ጋር አብረን እንሆናለን። እንዲህ በማድረግ እንግዳ ተቀባይነታችንን ከማሳየታችንም በላይ እርስ በርስ እንበረታታለን። (ሮሜ 12:13፤ 1 ጴጥ. 4:9) ሠርግ ለመደገስ ዝግጅት ስታደርጉ በ4–105 መጠበቂያ ግንብ ላይ የተሰጠውን ጥሩ ምክር በአእምሯችሁ ያዙ።
2 ሥርዓታማ የሆኑ ማኅበራዊ ጉዳዮች፦ ‘የምንበላ ወይም የምንጠጣ ብንሆን ወይም ማናቸውም ነገር ብናደርግ ሁሉንም ለአምላክ ክብር ማድረግ አለብን።’ (1 ቆሮ. 10:31–33) አንዳንዶች ይህንን ምክር አላስተዋሉትም። ድግሶቹ በጣም ሰፊ በመሆናቸው የተነሳ በተገቢ ሁኔታ መቆጣጠር ስለማይቻል ችግሮች መከሰታቸውን ቀጥለዋል። አንዳንድ ጊዜ ዓለማዊ መዝናኛዎች በሚታዩባቸው ድግሶች ላይ ዝግጅቶቹን ለማዳመቅ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ይጋበዛሉ። አልፎ አልፎ ተጋባዦች የመግቢያ ወይም ሌሎች ክፍያዎች ይጠየቃሉ። እንዲህ ያሉት ድግሶች ሥርዓታማነት ከሚጎድላቸውና ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ውጪ ከሆኑት ዓለማዊ ሥርዓቶች ጋር ይመሳሰላሉ።— ሮሜ 13:13, 14፤ ኤፌ. 5:15–20
3 በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች የራሱ የሆነ ዝግጅት ያለው አንድ የመዝናኛ ቦታ በመከራየት ተገቢ ቁጥጥር ለማድረግ በማያመችና ዓለማዊ በሆነ የማያንጽ መዝናኛ ጊዜያቸውን እንዳሳለፉ ሪፖርት ተደርጓል። ይህንን የመሳሰሉ ዝግጅቶች በመደረጋቸው “የይሖዋ ምሥክሮች” በሆቴሎች ወይም በመዝናኛ ስፍራዎች ቅዳሜና እሑድን አሳለፉ ተብሎ በሰፊው ተወርቷል። ብዙ ሰዎች የሚገኙባቸውን እንዲህ ዓይነት ዝግጅቶች በተገቢው ሁኔታ መቆጣጠር ስለሚያስቸግር ችግሮች ተከስተዋል። አልፎ አልፎ ሁከት፣ የአልኮል መጠጦችን ከመጠን በላይ መጠጣትና ሌላው ቀርቶ የጾታ ብልግና ተፈጽሟል። (ኤፌ. 5:3, 4) እንደዚህ ዓይነት ምግባር የሚታይባቸው ድግሶች ይሖዋን አያስከብሩም። ከዚህ ይልቅ በጉባኤው መልካም ስም ላይ ነቀፋ ከማስከተሉም በላይ ሌሎችን ያሰናክላል።— 1 ቆሮ. 10:23, 24, 29
4 ክርስቲያኖች እንግዳ ተቀባዮች እንዲሆኑ ቢመከሩም ትኩረት የሚሰጠው እርስ በእርስ በምንለዋወጠው መንፈሳዊ ነገር ላይ መሆን አለበት። (ሮሜ 1:11, 12) ብዙውን ጊዜ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ተሰባስበው ቢጨዋወቱ ይመረጣል። አገልግሎታችን የተባለው መጽሐፍ በገጽ 136 ላይ እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ጊዜ ለክርስቲያናዊ ጨዋታ ሲባል በርከት ያሉ ቤተሰቦች ወደ አንዱ ቤት ይጠሩ ይሆናል። . . . ጋባዦቹ በዚህ ጊዜ ለሚደረጉት ነገሮች ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል ቢባል ምክንያታዊ ነው። አስተዋይ ክርስቲያኖች ይህንን በአእምሮአቸው በመያዝ የተጋባዦቹን ቁጥር ማሳነስና ግብዣው የሚቆይበትን ሰዓት ማሳጠር ጥበብ ሆኖ አግኝተውታል።” ዓላማችን ጓደኞቻችንን በመንፈሳዊ ለማበረታታት ከሆነ የተንዛዛ ነገር እንደማያስፈልግ ኢየሱስ ጠቁሟል።— ሉቃስ 10:40–42
5 ለመሰል ክርስቲያኖች የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየት ጥሩ ነው። ቢሆንም ቤታችን ውስጥ ልከኛ ዝግጅት በማድረግና አንድ የመዝናኛ ቦታ ተከራይቶ ዓለማዊ መንፈስ የሚያንጸባርቁ የተንዛዙ ድግሶችን በማዘጋጀት መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። ሌሎችን በእንግድነት ስትጋብዝ ለሚፈጸመው ነገር ሁሉ ሙሉ ኃላፊነት መውሰድ እንደምትችል እርግጠኛ መሆን አለብህ።— የነሐሴ 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 17–20 ተመልከት።
6 ይሖዋ መልካም ሥራዎችን ማከናወናችንን እንድንቀጥል የሚገፋፋ መንፈስን የሚያድስ ማበረታቻ የምናገኝበትን የወንድማማች ማኅበር በመስጠት ባርኮናል። (ማቴ. 5:16፤ 1 ጴጥ. 2:12) በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ልከኝነትና ምክንያታዊነት በማሳየት ዘወትር ለአምላካችን ክብር ከማምጣታችንም በላይ ሌሎችን የምናንጽ እንሆናለን።— ሮሜ 15:2