በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ማበርከት
1 ለዘላለም መኖር የተባለው መጽሐፍ ሲወጣ በጣም ተደስተን ነበር! መጽሐፉ ሰዎች የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በታኅሣሥ ወር ይህንን መጽሐፍ በክልላችን ውስጥ ለማበርከት የሚያስችል አጋጣሚ ይኖረናል። የሰዎችን ፍላጎት ለማነሳሳት ምን ብለን መናገር እንችላለን?
2 የሚከተለው አቀራረብ በአምላክ ላይ ያለው እምነት የተዳከመበትን ሰው ትኩረት ሊስብ ይችላል:-
◼ “ብዙ ሰዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ በአምላክ ያምኑ የነበረ ቢሆንም አሁን ያላቸው እምነት ግን የድሮውን ያክል አይደለም። ምክንያቱ ምን ይመስልዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ያሉትን አስደናቂ ነገሮች ስንመለከት በአምላክ ላይ ያለን እምነት ይጠነክራል። [መዝሙር 19:1ን አንብብ።] እነዚህን ሰማያዊ አካላት የሚቆጣጠሩ ሕጎች ያወጣው አምላክ ለእኛም ጠቃሚ መመሪያዎችን ሰጥቶናል። [መዝሙር 19:7-9ን አንብብ።] እነዚህ ጥቅሶች ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ የቻልነውን ያህል መማር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጠበቅ አድርገው ይገልጻሉ። [ገጽ 12 እና 13 ላይ ያለውን ሥዕል አሳየው።] ከዚህ ልዩ እውቀት መጠቀም የሚፈልጉ ከሆነ ይህንን መጽሐፍ ትቼልዎ ልሄድ እችላለሁ።”
3 በቅርቡ የተከሰተ አሳዛኝ ነገር በአእምሮህ ይዘህ እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “ስለ [የተከሰተውን ነገር ጥቀስ] ሰምተው ሊሆን ይችላል። አምላክ በሌሎች ላይ የምናየውና አልፎ ተርፎም በእኛ ላይ የሚደርሰው የፍትሕ መጓደልና መከራ ያሳስበው እንደሆነና እንዳልሆነ ራስዎን ጠይቀው ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ እንደሚወደንና ችግር በሚያጋጥመን ጊዜ እንደሚረዳን ያረጋግጥልናል።” መዝሙር 72:12-17ን አለፍ አለፍ እያልክ አንብብ። መጽሐፉን ከፍተህ ገጽ 99 አውጣና ይህ መጽሐፍ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሚጠይቁት አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ እንደሚሰጥ ግለጽለት። “መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ በጣም የሚያጽናና ሆኖ ያገኙታል። መልሱን ራስዎ አንብበው እንዲደርሱበት ይህን መጽሐፍ ትቼልዎት ብሄድ ደስ ይለኛል።”
4 ወላጅ ካጋጠመህ በቤተሰብ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ትችላለህ:-
◼ “አብዛኞቹ ወላጆች የቤተሰብን ደስታ የሚያሳጡ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ይስማማሉ። ቤተሰብ ደስታ እንዳያገኝ የሚያደርጉ ከባድ ችግሮች ምንድን ናቸው ብለው ያስባሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አብዛኞቻችን ቤተሰባችንን ደስተኛ ለማድረግ የቻልነውን ያህል ጥረት እያደረግን ቢሆንም ብዙውን ጊዜ የተሻለ ውጤት እንድናገኝ የሚረዳ ነገር ብናገኝ ደስ ይለናል። መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ጥሩ ምክር ይሰጣል። [ቆላስይስ 3:12, 18-21ን አለፍ አለፍ እያልክ አንብብ።] በዚህ መጽሐፍ 29ኛው ምዕራፍ ላይ ‘የቤተሰብን ኑሮ የተሳካ ማድረግ’ በሚለው ርዕስ ሥር እንደተገለጸው መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ይናገራል። ይህ ምዕራፍ በትዳር ውስጥ ያሉ ውጥረቶችን እንዴት ማርገብ እንደሚቻልና ልጆቻችን የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዴት መፍታት እንደሚቻል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሰጠውን ምክር ያቀርባል። ይህን መጽሐፍ በማንበብ እንደሚጠቀሙ እርግጠኛ ነኝ።”
5 አጠር ለማድረግ ከፈለግህ በሚከተለው አቀራረብ ልትጠቀም ትችላለህ:-
◼ “የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው ብለው አስበው ያውቃሉ? በዚህ መጽሐፍ ገጽ 74 ላይ ለምን እንደምንሞትና አምላክ ሞትን እንዴት እንደሚያስወግደው ተገልጿል። አምላክ ለሚወዱት ሰዎች የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንደሰጣቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። [ዮሐንስ 17:3ን አንብብ።] ስለዚህ ጉዳይ ለማወቅ ከፈለጉ መጽሐፉ ይበልጥ ትምህርት ሰጪ ሆኖ ያገኙታል።”
6 ጥሩ ዝግጅት ካደረግን ሰዎች ከፍተኛ ደስታ በሚያገኙበት መንገድ ይህንን መጽሐፍ ‘ቅዱሳን ጽሑፎችን እየጠቀስን ለማስረዳት’ ልንጠቀምበት እንችላለን!— ሉቃስ 24:32 የ1980 ትርጉም