ዮሐንስ 17:3 ላይ የተመዘገቡት
የኢየሱስ ቃላት በቁም ነገር ሊያዙ የሚገባቸው ናቸው። አምላክንና ክርስቶስን ማወቅ የዘላለም ሕይወት ማለት መሆኑን ያለ ማጋነን ተናግሯል! ይሁን እንጂ ይሖዋንና ኢየሱስን ማወቃችን ብቻ የዘላለም ሕይወት ሽልማት ያስገኝልናል ማለት ነውን? በጭራሽ። እሥራኤላውያን ይሖዋ አምላካቸው እንደሆነ በሚገባ ያውቁ ነበር። ይሁን እንጂ አኗኗራቸው እንዲህ ያለ እምነት እንዳላቸው አላሳየም። በውጤቱም የእርሱን ሞገስ አጡ። (ሆሴዕ 4:1, 2, 6) በአሁኑ ጊዜም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ‘ለአምላክ የሚቀኑ’ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በትክክለኛ እውቀት መሠረት አይደለም። (ሮሜ 10:2) “እውነተኛ አምላክ ብቻ” የሆነውን ይሖዋን ማወቅና እርሱን በትክክል እንዴት ማገልገል እንደሚችሉ መማር ይኖርባቸዋል። ለዚህም ሲባል በኅዳር ወር ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት ወይም በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተሰኙትን መጽሐፎች እናበረክታለን። ምን ዓይነት አቀራረብ ትጠቀማለህ? ሊረዱህ የሚችሉ ጥቂት ሐሳቦች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል።
2 በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ሐሳብ ለብዙ ሰዎች አዲስ ስለሚሆን የሚከተለው መግቢያ ፍላጎታቸውን ሊያነሳሳ ይችል ይሆናል:-
◼ “ጎረቤቶቻችንን አንድ ጥያቄ እየጠየቅናቸው ነው። እንዲህ በመሰለ ዓለም ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ ግብዣ ቢቀርብልዎ ግብዣውን ይቀበላሉ? [እውቀት ከተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 4ና 5 ላይ ያለውን ሥዕል ወይም ለዘላለም መኖር ከተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 12ና 13 ላይ ያለውን ሥዕል አሳይ። መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ይህ በሕይወትዎ ሊያገኙት የሚችሉት አስደሳች ዕድል ሊሆን ይችላል። ይህ ሁኔታ ለእርስዎ እውን እንዲሆን ምን ማድረግ ያለብዎ ይመስልዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ዮሐንስ 17:3 ላይ ምን ማድረግ እንደሚገባዎ የሚናገረውን ልብ ይበሉ። [ጥቅሱን አንብብ።] ብዙ ሰዎች እንደዚህ የመሰለውን ልዩ እውቀት እንዲያገኙ ይህ መጽሐፍ ረድቷቸዋል። የሚያነቡት የግል ቅጂ እንዲኖርዎት ይፈልጋሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] በዚች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንደምናገኝ ማመን የምንችለው ለምን እንደሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ተመልሼ ስመጣ ልንወያይ እንችላለን።”
3 ዮሐንስ 17:3ን ካወያየሃቸው ሰዎች ጋር ለመነጋገር ተመልሰህ በምትሄድበት ጊዜ በዚህ መንገድ ውይይትህን ልትከፍት ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው በመጣሁ ጊዜ አምላክንና እርሱን ማወቅ የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝ ኢየሱስ ማረጋገጫ የሰጠበትን ዮሐንስ 17:3 ላይ የሚገኙትን የኢየሱስ አስደናቂ ቃላት አንብቤልዎ ነበር። ብዙ ሰዎች ግን የተሻለ ሕይወት የሚገኘው በሰማይ ብቻ እንደሆነ ያምናሉ። እርስዎ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ምድር ተመልሳ ገነት እንደምትሆን የሚያረጋግጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ባለፈው ጊዜ ትቼልዎት ከሄድኩት መጽሐፍ ውስጥ ባሳይዎት ደስ ይለኛል። [እውቀት ከተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 9ና 10 ላይ የሚገኙትን ከ11-16 ያሉትን አንቀጾች ወይም ደግሞ ዘላለም መኖር ከተሰኘው መጽሐፍ ከገጽ 156-8 ያሉትን ተወያዩ።] በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት በእነዚህ ተስፋዎች ላይ ማመን የሚችሉት ለምን እንደሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ስመጣ አሳይዎታለሁ። እስከዚያው ጊዜ ግን ከወሰዱት መጽሐፍ ምዕራፍ 2ን ሊያነቡ ይችላሉ።”
4 ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ካላቸው ሰዎች ጋር በምትወያይበት ጊዜ የሚከተሉትን አቀራረቦች ልትጠቀም ትችላለህ:-
◼ “በዓለም ዙሪያ ብዙ ሃይማኖቶች የኖሩት ለምን እንደሆነ ከጎረቤቶቻችን ጋር እየተነጋገርን ነው። በዓለም ዙሪያ ወደ 10,000 የሚጠጉ ሃይማኖቶች አሉ። ይሁን እንጂ ያለው አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ይህን ያህል የሃይማኖት ዝብርቅ ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው ብለው ያስባሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። እውቀት የተሰኘውን መጽሐፍ ምዕራፍ 5ን እውጣና አንቀጽ 1ን አንብብ ወይም ለዘላለም መኖር ከተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 30ን አውጣና አንቀጽ 13ን አንብብ።] ይህን ምዕራፍ በማንበብ ለጥያቄዎቹ አጥጋቢ የሆኑ መልሶች ሊያገኙ ይችላሉ። መጽሐፉን ለመመርመር የሚፈልጉ ከሆነ ትቼልዎት ብሄድ ደስ ይለኛል።” መጽሐፉን ከወሰደ ተመልሰህ የምትሄድበትን ቀን ንገረውና “ድጋሚ ስመጣ ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አንድ ቦታ የሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶች መሆን አለመሆናቸውን እንወያያለን።”
5 ብዙ ሃይማኖቶች የኖሩት ለምን እንደሆነ ካነጋገርከው ሰው ጋር ውይይትህን ለመቀጠል እንደገና ተመልሰህ በምትሄድበት ጊዜ እንዲህ ለማለት ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ ስንነጋገር ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አንድ ቦታ የሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶች ናቸው ወይስ አይደሉም የሚል ጥያቄ አንስቼ ነበር። ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ስለዚህ ጉዳይ ኢየሱስ ምን እንዳለ ትቼልዎት በሄድኩት መጽሐፍ ውስጥ ባሳይዎት ደስ ይለኛል። [እውቀት የተሰኘውን መጽሐፍ ምዕራፍ 5ን አውጣና አንቀጽ 6ንና 7ን ወይም ዘላለም መኖር ከተሰኘው መጽሐፍ ምዕራፍ 3ን አውጣና አንቀጽ 1-3 አንብብ፤ በተጨማሪም ማቴዎስ 7:21-23ን አክለህ ከአንቀጽ 14 ጋር አንብብ።] የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ በትክክል ማወቅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ማወቅዎ ያስገርምዎ ይሆናል። የሚቀጥሉት አንቀጾች ትምህርት ሰጪ ሆነው ያገኟቸዋል። የዚህን ምዕራፍ የቀሩትን አንቀጾች እባክዎ ያንብቡት። በሚቀጥለው ጊዜ ተመልሼ ስመጣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ያለውን ዋጋማነት አብራራልዎታለሁ።”
6 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ቀጥተኛ የሆነ አቀራረብ መጠቀም ብዙውን ጊዜ ውጤታማ ነው። “ማመራመር” መጽሐፍ ገጽ 12 ላይ የሚከተለው መግቢያ ይገኛል:-
◼ “የመጣሁት ቋሚ የሆነ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለመስጠት እንደምችል ለመግለጽ ነው። ፈቃድዎ ከሆነ ለጥቂት ደቂቃዎች ከ200 በላይ በሆኑ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በየቤታቸው ከቤተሰባቸው ጋር እንዴት እንደሚያጠኑ ባሳይዎት ደስ ይለኛል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከቀረቡት ርዕሶች መካከል የፈለግነውን መርጠን ልንወያይበት እንችላለን። [በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኘውን የአርዕስት ማውጫ አሳየው።] ከእነዚህ ርዕሶች መካከል በተለይ ለማወቅ የሚፈልጉት ስለየትኛው ነው?” ሰውየው እስኪመርጥ ድረስ ጠብቅ። የመረጠውን ምዕራፍ ግለጥና በመጀመሪያው አንቀጽ ተጠቅመህ ጥናት ጀምር።
7 ጥናት ለመጀመር የሚያስችል ሌላው ስኬታማ አቀራረብ የሚከተለው ነው:-
◼ “መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ለሰዎች አስተምራለሁ፤ ተጨማሪ ተማሪዎችን ለማስጠናት በቂ ጊዜ አለኝ። መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት የምንጠቀመው ይህን መጽሐፍ ነው። [መጽሐፉን አሳያቸው።] ጥናቱ ለጥቂት ወራት የሚቀጥል ሲሆን እንደሚከተሉት ላሉት ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጣል:- አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ? የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው? በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ምን ይሆናሉ? ከአምላክ ጋር መቀራረብ የምትችለው እንዴት ነው? ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ ላሳይዎት እችላለሁ?” ጥናቱን ለመጀመር ፈቃደኛ ካልሆነ መጽሐፉን በግሉ ማንበብ ይፈልግ እንደሆነ ጠይቀው።
8 አምላክንና ክርስቶስን በትክክል የሚያውቅ ማንኛውም ሰው እንዴት ያለ ደስታ ያገኝ ይሆን! እነርሱን ማወቅ ማለት ፍጹም ሁኔታዎች በሰፈኑበት የዘላለም ሕይወት ማግኘት ማለት ነው። በኅዳር ወር፣ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኘውን እውቀት ለሌሎች ለማካፈል ማንኛውንም አጋጣሚ እንጠቀም።