የጥያቄ ሣጥን
◼ በስብሰባዎች ላይ ማንበብን በተመለከተ በአእምሮአችን ልንይዛቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድን ናቸው?
በመጠበቂያ ግንብ እና በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ፕሮግራም ወቅት አብዛኛውን ጊዜ የሚወስደው አንቀጾቹን ማንበቡ ነው። በመሆኑም እንዲያነብ የተመደበው ወንድም ከባድ የማስተማር ኃላፊነት አለበት ማለት ነው። አንባቢው አድማጮች እንዲገባቸው ብቻ ሳይሆን ለሥራ እንዲያንቀሳቅሳቸውም ጭምር የትምህርቱን ‘መልእክት ሊረዱ’ በሚችሉበት መልኩ ሊያነብ ይገባል። (ነህ. 8:8 አዓት) በመሆኑም አንባቢው ክፍሉን በሚገባ መዘጋጀት ይኖርበታል። (1 ጢሞ. 4:13 የ1980 ትርጉም፤ መመሪያ መጽሐፍ ጥናት 6ን ተመልከት።) በሕዝብ ፊት ትርጉም ያለው ንባብ ለማንበብ በጣም አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ነጥቦች እነሆ:-
በተገቢው ቦታ ላይ ማጥበቅ፦ ትክክለኛውን መልእክት ለማስተላለፍ እንዲቻል የትኞቹ ቃላት ወይም ሐረጎች ረገጥ ተደርገው መነበብ እንዳለባቸው አስቀድመህ ወስን።
ቃላቱን በትክክል አንብብ፦ አድማጮች በጽሑፉ ላይ የሰፈሩትን አገላለጾች በግልጽ እንዲረዷቸው ከተፈለገ ቃላቱን በትክክልና ትርጉም በሚያስተላልፍ መልኩ ማንበብ ያስፈልጋል። እንግዳ የሆኑና እምብዛም የማይሠራባቸውን ቃላት በመዝገበ ቃላት ተመልከት።
ድምፅህን ከፍ አድርገህ በግለት አንብብ፦ ድምፅን ከፍ አድርጎ በግለት ማንበብ የመስማት ፍላጎት ያሳድራል፣ ስሜትን ይቀሰቅሳል እንዲሁም አድማጮችን ለሥራ ያነሣሣል።
ሞቅ ባለ መንፈስ ከሰው ጋር እንደምትወያይ አድርገህ አንብበው፦ ንባቡን ሕያው ማድረግ የምትችለው ሳትደነቃቀፍ ስታነብ ነው። አንባቢው አስቀድሞ ከተዘጋጀና ከተለማመደ ዘና ለማለት ይችላል፤ ንባቡም አሰልቺና አንድ ወጥ ከመሆን ይልቅ ማራኪ ይሆናል።— ዕን. 2:2 አዓት
እንደተጻፈው አንብብ፦ የግርጌ ማስታወሻዎች እንዲሁም በቅንፍ ውስጥ የሚገኙ ሐሳቦች ነጥቡን ይበልጥ ግልጽ የሚያደርጉ ከሆነ በተለመደው መንገድ ይነበባሉ። የማይነበቡት ሐሳቡ የተወሰደበትን ምንጭ የሚጠቅሱ ከሆነ ብቻ ነው። የግርጌ ማስታወሻው በአንቀጹ ውስጥ በተጠቀሰበት ቦታ ላይ ሊነበብ የሚገባው ሲሆን “የግርጌ ማስታወሻው እንዲህ ይነበባል . . .” ብሎ ወደዚያ መሸጋገር ይቻላል። ከግርጌ ማስታወሻው በኋላ የቀሩትን የአንቀጹን ክፍሎች አንብብ።
በሕዝብ ፊት ጥሩ አድርጎ ማንበብ ሌሎች ሰዎች ታላቁ አስተማሪያችን ‘ያዘዛቸውን ነገሮች ሁሉ እንዲጠብቁ ከምናስተምርባቸው’ በጣም ጠቃሚ መንገዶች አንዱ ነው።— ማቴ. 28:20