ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የመታሰቢያው በዓል!
1 እሑድ መጋቢት 23 ቀን ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ በዓል እናከብራለን። (ሉቃስ 22:19) ይህ በእርግጥም ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ወቅት ነው! ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ለይሖዋ ፍጹም አቋሙን መጠበቁ ሰው የይሖዋን የአጽናፈ ዓለም የመግዛት መብት በመደገፍ ከባድ ፈተናዎች ቢደርሱበትም እንኳ ፍጹም በሆነ መንገድ ለአምላክ የማደር ባሕርይ ሊያሳይ እንደሚችል አረጋግጧል። (ዕብ. 5:8) ከዚህም በተጨማሪ የክርስቶስ ሞት የሰው ዘሮችን ለመቤዠት ፍጹም ሰብዓዊ መሥዋዕት ስላስገኘ እምነት ያላቸው ሁሉ ለዘላለም እንዲኖሩ መንገድ ጠርጓል። (ዮሐ. 3:16) በመታሰቢያው በዓል ላይ በመገኘት ይሖዋ ያሳየንን ፍቅርና ኢየሱስ ለእኛ ላቀረበው መሥዋዕት ያለንን ከልብ የመነጨ አድናቆት በተግባር ልናሳይ እንችላለን።
2 በ1997 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ እንደሰፈረው ከመጋቢት 18-23 እንዲነበብ የወጣውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ሁላችንም እንድንከተል ማበረታቻ ተሰጥቶናል። በተጨማሪም በምድር ላይ እስካሁን ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ከተሰኘው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ከምዕራፍ 112-16 ባሉት ሐሳቦች ላይ ከቤተሰቦቻችን ጋር ውይይት ማድረጋችን በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከሁሉ በላቀው ሳምንት ላይ እንድናተኩር ይረዳናል።
3 የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ሰሞን በመስክ አገልግሎት ላይ የምታሳልፈውን ሰዓት ከፍ ለማድረግ ትችላለህን? ብዙ አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ ሆነው በማገልገል በመጋቢት ወር ያሉትን አምስት ሳምንቶች ሙሉ በሙሉ ይጠቀሙበታል። ከእነርሱ አንዱ ለመሆን ለምን አትሞክርም? በመታሰቢያው በዓል ላይ የመገኘትን አስፈላጊነት አጉልቶ በመናገር ሁላችንም ሙሉ ተሳትፎ ልናደርግ እንችላለን። በዓሉ የሚከበረው እሑድ ዕለት ስለሚሆን ብዙ ሰዎች በበዓሉ ላይ ለመገኘት አይቸግራቸውም። ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችና ሌሎች ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አብረውን በዓሉን እንዲያከብሩ መጋበዛችሁን አትርሱ። እውቀት በተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 127 አንቀጽ 18 ላይ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ልዩ በሆነ መንገድ ስለሚከበረው በዓል የሚገልጸውን ትምህርት ከልሱላቸው።
4 የኢየሱስ ሞት ለሁሉም ሰዎች የሚያመጣቸውን በረከቶች በከፍተኛ አድናቆት በማሰብ በ1997 ከሁሉ የበለጠ ግምት የሚሰጠውን ይህን ታላቅ በዓል አክብር። በየትም ቦታ የሚኖሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች የመታሰቢያውን በዓል በሚያከብሩበት በመጋቢት 23 ምሽት በበዓሉ ላይ ተገኝ።