“ፍላጎት ያሳዩትን ሁሉ መርዳት
1 እምነታችንና ለሌሎች ያለን ፍቅር ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት ያሳዩትን ሁሉ በመጋቢት ወር እንድንረዳና ወደ መታሰቢያው በዓል እንድንጋብዝ ይገፋፋናል። እንዲህ ዓይነት ሰዎች በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ወደተመሠረተው የይሖዋ የማዳን ዝግጅት እንድንመራቸው ያስፈልጋል። — ዕብ. 9:28
2 ለመታሰቢያው በዓል ልትጋብዟቸው የምትፈልጓቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር መጻፍ መልካም ሐሳብ ነው። በስብሰባዎች ላይ አንዳንድ ጊዜ የሚገኙትን እንዲሁም ከአሁን ቀደም ያጠኑ የነበሩ ወይም በሌሎች መንገዶች ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በዝርዝሩ ውስጥ አስገቡ። የማያምን የትዳር ጓደኛችሁንና ሌሎች የማያምኑ የቤተሰቡ አባላትንም አትዘንጉ። ዝርዝሩን ከጻፋችሁ በኋላ ሁሉንም ለመጠየቅ የተለየ ጥረት አድርጉ። አንዳንዶቹን ሰዎች ሄዶ በማነጋገር በኩል ሽማግሌዎች እንዲረዷችሁ ለመጠየቅ ትፈልጉ ይሆናል።
3 በጉብኝታችሁ ወቅት ምን ልትሉ ትችላላችሁ?
ሞቅ ያለ ሰላምታ ከሰጣችሁ በኋላ እንደሚከተለው ለማለት ትችላላችሁ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት አሳይተው ነበር። በአንድ ልዩ በዓል ላይ እንዲገኙ በማቀርብልዎ በዚህ ግብዣ ይደሰታሉ ብዬ አሰብሁ። [ወደ መታሰቢያው በዓል እንዲመጡ የሚጋብዘውን የግብዣ ወረቀት ለቤቱ ባለቤት ስጠው።] ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹ እንዲያከብሩት የሰጣቸው ብቸኛው በዓል የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ነው። በክርስቶስ ሞት አማካኝነት የተከናወኑትን ነገሮችና በእርሱም ምክንያት እንዴት የዘላለም ሕይወት ልናገኝ እንደምንችል የሚከልስ ንግግር ለመስማት በጉጉት እንጠባበቃለን። ባለፈው ዓመት በዚህ ልዩ ስብሰባ ላይ ከ11 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል። በዚህ ዓመት ደግሞ እርስዎም አብረውን ቢያከብሩ ደስ ይለኛል።” ጉባኤያችሁ የመታሰቢያውን በዓል የሚያከብርበትን ጊዜና ቦታ የግብዣ ወረቀቱ ላይ መጻፋችሁን አረጋግጡ። በተጨማሪም መጓጓዣ የሚያገኙበትን መንገድ ልታዘጋጁ ወይም አስፈላጊ ከሆነ ቦታው ድረስ ልትወስዱት እንደምትችሉ ሐሳብ አቅርቡ።
4 አዲስ የመጡ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ሲገኙ ጥሩ አቀባበል ሊደረግላቸው ይገባል። ከጉባኤው አስፋፊዎች ጋር እንዲተዋወቁ እርዷቸው። እንዲሁም በቤታቸው አቅራቢያ ከሚኖሩ ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ጋር አስተዋውቋቸው። በራሳቸው አካባቢ ያሉ በርከት ያሉ ሰዎች ለእውነት ፍላጎት እንዳላቸው ማወቃቸው ያበረታታቸዋል። የሚቻል ከሆነ የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ጊዜ ከቤተሰባችሁ ጋር እንዲቀመጡ ጋብዟቸው።
5 እርግጥ ነው፤ የመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘታቸው ብቻ መዳን አያስገኝላቸውም። ሆኖም ከጋበዛችኋቸው ሰዎች ብዙዎቹ እዚያ መገኘታቸው በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ለማመን የሚረዳ የመጀመሪያ እርምጃቸው ሊሆን ይችላል። ከስብሰባው ወደ ቤት በምትሄዱበት ጊዜ እንግዳው ሰው በሚቀጥለው እሁድ በሚደረገው የሕዝብ ስብሰባና የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ለመገኘት ይፈልግ እንደሆነ ጠይቁት። ሞቅ ያለ ስሜትና ሰዎችን የማስተናገድ መንፈስ ይኑራችሁ። በምትችሉት በማናቸውም መንገድ ልትረዱት ፈቃደኛ እንደሆናችሁ እንዲያውቅ አድርጉ። ከእኛ ጋር አዘውትሮ መገናኘቱን በቶሎ ከጀመረ መንፈሳዊ ዕድገቱም የተፋጠነ ይሆናል። እኛ ከረዳናቸው ብዙ ሰዎች ጋር ሆነን “ከታላቁ መከራ” ብንተርፍ እንዴት ያለ ደስታና እርካታ እናገኛለን! — ራእይ 7:9, 14