ብዙ ሰዎች እየጎረፉ ነው
1 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው ሁሉ በአሁኑ ጊዜም በክርስቲያን ጉባኤ እየታየ ያለው ጭማሪ እጅግ ከፍተኛ ነው። (ሥራ 2:41፤ 4:4) ባለፈው ዓመት 366, 579 አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ተጠምቀዋል። ይህም በአማካይ በቀን ከ1, 000 የሚበልጡ ሰዎች ተጠምቀዋል ማለት ነው! ባለፉት ሦስት ዓመታት ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች ተጠምቀዋል። በእርግጥም ይሖዋ እጅግ ብዙ አማኞች መጨመሩን ቀጥሏል።— ሥራ 5:14
2 በክርስቲያናዊ አኗኗር እምብዛም ተሞክሮ የሌላቸው ብዙ አዳዲስ ሰዎች በእምነት ጠንካራ ከሆኑት እርዳታና ሥልጠና ማግኘት ይኖርባቸዋል። (ሮሜ 15:1) በጥንት ጊዜ ከነበሩት ክርስቲያኖች መካከል ከተጠመቁ ረዥም ጊዜ የሆናቸው እንኳን ሳይቀሩ ‘ወደ ጉልምስና ማደጋቸውን’ አቁመው ነበር። (ዕብ. 5:12፤ 6:1) ጳውሎስ ወደ ዕብራውያን በጻፈው ደብዳቤው ላይ ክርስቲያኖች በምን መስኮች በመንፈሳዊ ማደግ እንዳለባቸው ጎላ አድርጎ የገለጸው ከዚህ የተነሳ ነው። እነዚህ መስኮች ምንድን ናቸው? አስፈላጊ የሆኑ እርዳታዎችን መስጠት የሚቻለውስ እንዴት ነው?
3 ጥሩ የጥናት ልማድ ማዳበር:- ጳውሎስ ከሰጠው መመሪያ ጋር በመስማማት ጥሩ ተማሪ ለመሆን በንቃት መማር፣ ትምህርቱን መከለስና የይሖዋ ድርጅት የሚያቀርበውን “ጠንካራ ምግብ” መመገብ አስፈላጊ ነው። (ዕብ. 5:13, 14፤ የነሐሴ 15, 1993 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 12-17 ተመልከት።) ከአዳዲስ አማኞች ጋር መንፈሳዊ ውይይቶችን በማድረግና በግል ምርምር አድርገህ ያገኘሃቸውን ውድ የእውነት እንቁዎች ለእነርሱ በማካፈል ጥሩ የጥናት ልማድ እንዲያዳብሩ ልታነሳሳቸው ትችላለህ። ምናልባትም አንድ አዲስ አማኝ የግል ጥናት ወይም የቤተሰብ ጥናት በምታደርግበት ጊዜ አብሮህ እንዲገኝ ልትጋብዘው ትችላለህ።
4 አዘውትሮ በስብሰባዎች መገኘት:- የምታሳየው የታማኝነት ምሳሌና የምትናገራቸው ፍቅራዊ የማበረታቻ ቃላት አዳዲስ የጉባኤ አባላት ጳውሎስ አንዳንዶች ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የመቅረት “ልማድ” አላቸው ብሎ ከገለጸው ከሌላኛው ሁኔታ እንዲቆጠቡ ይረዳቸዋል። (ዕብ. 10:24, 25) ስብሰባዎች በመንፈሳዊ ሕያው ሆነው በጉባኤ ውስጥ እንዲኖሩ የሚያግዛቸው መሆኑን እንዲገነዘቡ እርዳቸው። በወንድማማች ማኅበራችን ውስጥ የባይተዋርነት ስሜት እንዳያድርባቸው በራስህ ተነሳስተህ እርዳቸው።
5 በልበ ሙሉነት ወደ ይሖዋ መቅረብ:- ሥጋዊ ድካምንና የግል ድክመቶችን ለማሸነፍ ውስጣዊ ስሜታችንንና በጣም የሚያሳስቡንን ነገሮች በመግለጽ ይሖዋን በጸሎት ለመሻት ጥረት ማድረግ አለብን። ጳውሎስ አጥብቆ እንዳሳሰበው አዲሶች ይሖዋ እንዲረዳቸው አጥብቀው ከመለመን መቆጠብ እንደሌለባቸው መማር ይኖርባቸዋል። (ዕብ. 4:15, 16፤ 10:22) በዚህ በኩል ያለህን የግል ተሞክሮ መናገርህ አንድ አዲስ ሰው ይሖዋ ከልብ የሚቀርቡ ጸሎቶችን እንደሚሰማ ይበልጥ እንዲያምን ያደርገዋል።
6 ለአገልግሎት ጊዜ መመደብ:- በተጨማሪም ጳውሎስ “ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት” በምናቀርብበት ጊዜ መንፈሳዊነታችን እንደሚጠናከር ተናግሯል። (ዕብ. 13:15) ለመስክ አገልግሎት ባወጣኸው ሳምንታዊ ፕሮግራምህ ላይ አንድ አዲስ አስፋፊ አብሮህ በአገልግሎት እንዲካፈል ልትጋብዝ ትችላለህ? ምናልባት አንድ ላይ ሆናችሁ መግቢያ መዘጋጀት ወይም አዲሱ አስፋፊ ገና ያልሞከረው የአገልግሎት መስክ ምን እንደሚመስል ልትወያዩ ትችላላችሁ።
7 ብዙ ሰዎች ወደ እውነት እየጎረፉ መሆናቸው ትልቅ የደስታ ምንጭ ሆኖልናል። አዳዲስ የጉባኤ አባላትን ለማሰልጠንና ለማደፋፈር ራሳችንን ማቅረባችን ‘ነፍሳቸውን ለመጠበቅ’ የሚያስችላቸውን ጠንካራ እምነት እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል።— ዕብ. 3:12, 13፤ 10:39