ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ደፋሮች ሁኑ
1 ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ያስደስትሃል? ብዙ አስፋፊዎች ተመላልሶ መጠየቅ ያደርጋሉ። በተለይ ቀደም ሲል ስታነጋግራቸው እምብዛም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በድጋሚ ስታነጋግር መጀመሪያ ላይ ፈራ ተባ ትል ይሆናል። ይሁን እንጂ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ‘ምሥራቹን ለመናገር እንድትችል አምላካችን ድፍረት በሰጠህ’ መጠን ይህ ሥራ ምን ያህል ቀላልና የሚክስ እንደሆነ ስለምትገነዘብ በጣም ትደሰታለህ። (1 ተሰ. 2:2) እንዴት?
2 ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግና ለመጀመሪያ ጊዜ በማነጋገር በኩል ትልቅ ልዩነት አለ። ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርገው እንግዳ ለሆነ ሰው ሳይሆን ቀደም ሲል ለተዋወቅነው ሰው ነው። ደግሞም በአጠቃላይ ሲታይ እንግዳ ከሆነ ሰው ጋር ውይይት ከማድረግ ይልቅ ከምናውቀው ሰው ጋር መወያየት ቀላል ነው። ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ከሚያስገኛቸው አስደሳች ውጤቶች አንዱ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነው።
3 ከቤት ወደ ቤት በምናገለግልበት ጊዜ ቀደም ሲል ጎብኝተናቸው ፍላጎት ወዳላሳዩ ሰዎች ቤት ደጋግመን እንሄዳለን። ታዲያ ሳናቋርጥ ወደ ቤታቸው የምንሄደው ለምንድን ነው? የሰዎች ሁኔታ ሊለወጥ እንደሚችልና ቀደም ሲል ስናነጋግረው ምንም ፍላጎት ያላሳየ ወይም የተቃወመ ግለሰብ እንኳን ሳይቀር በሚቀጥለው ጊዜ ተመልሰን ስንሄድ ፍላጎት ሊያሳይ እንደሚችል ስለምናውቅ ነው። ይህን በአእምሯችን በመያዝ በዚህ ጊዜ ጥሩ ፍላጎት እንዲኖረው የሚያደርግ አንድ ነገር ለመናገር እንድንችል ጥሩ አድርገን እንዘጋጃለን፤ በተጨማሪም የይሖዋን በረከት ለማግኘት እንጸልያለን።
4 ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ሥራ በምንካፈልበት ጊዜ ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት ፍላጎት ላላሳዩ ሰዎች የምንሰብክ ከሆነ ለመንግሥቱ መልእክት መጠነኛ ፍላጎት ላሳየ ለማንኛውም ሰው ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ የበለጠ ፈቃደኛ መሆን አይገባንም?— ሥራ 10:34, 35
5 አብዛኞቻችን እውነትን ልንማር የቻልነው አንድ አስፋፊ በትዕግሥት ተመላልሶ መጠየቅ ስላደረገልን ነው። ይህን እርዳታ ካገኙት አንዱ ከሆንክ ራስህን እንዲህ ብለህ ልትጠይቅ ትችላለህ:- ‘ለዚህ አስፋፊ መጀመሪያ ላይ ያሳየሁት ስሜት ምን ዓይነት ነበር? የመንግሥቱን መልእክት ገና እንደሰማሁ ወዲያው በደስታ ተቀበልኩ? ምንም ፍላጎት የሌለኝ እመስል ነበር?’ አስፋፊው ተመላልሶ መጠየቅ ሊደረግልን የሚገባ ሰዎች እንደሆንን አድርጎ በመቁጠር ‘ምሥራቹን ለመናገር በአምላክ በኩል ድፍረት አግኝቶ’ ተመልሶ በመምጣቱና እውነትን ማስተማሩን በመቀጠሉ መደሰት ይኖርብናል። መጀመሪያ ላይ ጥቂት ፍላጎት አሳይተው በኋላ ግን አልፈልግም ስለሚሉ ሰዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? የሚከተለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው ይሆናል የሚል ዝንባሌ መያዝ በጣም አስፈላጊ ነው።
6 አንድ ቀን ማለዳ ሁለት አስፋፊዎች በመንገድ ላይ ምሥክርነት እየተካፈሉ ሳለ ሕፃን ጋሪ ላይ አስቀምጣ እየገፋች ከምትሄድ አንዲት ወጣት ጋር ተገናኙ። ሴትዮዋ መጽሔት ተቀበለችና በሚቀጥለው እሑድ እቤቷ እንዲመጡ እህቶችን ጋበዘቻቸው። በተባሉት ሰዓት እቤቷ ሄዱ። ይሁን እንጂ ሴትዮዋ ለመነጋገር ጊዜ እንደሌላት ነገረቻቸው። ሆኖም በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚመቻት ገለጸችላቸው። እህቶች በቀጠሮዋ ስለመገኘቷ ጥርጣሬ አድሮባቸው ነበር። ሆኖም ተመልሰው በሄዱ ጊዜ ሴትዮዋ እየጠበቀቻቸው ነበር። ጥናት ተጀመረላት፤ ሴትዮዋም አስገራሚ በሆነ መንገድ እድገት ማድረጓን ቀጠለች። በአጭር ጊዜ ውስጥ በስብሰባዎች ላይ አዘውትራ መገኘትና በመስክ አገልግሎት መካፈል ጀመረች። አሁን ተጠምቃለች።
7 በመጀመሪያ ጉብኝትህ ወቅት መሠረት ጣል፦ የተሳካ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ መሠረት የሚጣለው ብዙውን ጊዜ በመጀመሪያ ጉብኝት ወቅት ነው። የቤቱ ባለቤት የሚሰጠውን ሐሳብ በጥንቃቄ አዳምጥ። ስለምን ጉዳይ አንስቶ አነጋገረህ? ሃይማይኖታዊ ዝንባሌ ያለው ነው? ማኅበራዊ ጉዳዮች ያሳስቡታል? ለሳይንስ፣ ለታሪክ ወይም ለአካባቢ ሁኔታ ትኩረት የሚሰጥ ሰው ነው? በውይይትህ መደምደሚያ ላይ ፍላጎት የሚቀሰቅስ አንድ ጥያቄ ልታነሳና ሌላ ጊዜ ስትመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ለጥያቄው በሚሰጠው መልስ ላይ ውይይት እንደምታደርጉ ልትነግረው ትችላለህ።
8 ለምሳሌ ያህል የቤቱ ባለቤት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገነቲቷ ምድር ስለሚናገረው ተስፋ ጥሩ ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ በዚህ ርዕስ ላይ ተጨማሪ ውይይት ማድረግ ተገቢ ይሆናል። ከመሄድህ በፊት “አምላክ ይህን ተስፋ እንደሚፈጽም እርግጠኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?” ብለህ ልትጠይቅ ትችላለህ። ከዚያም ቀጠል አድርገህ “የቀሩት የቤተሰቡ አባላት እቤት በሚሆኑበት ጊዜ ጎራ ብዬ መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ ላሳይዎት እችላለሁ።”
9 የቤቱ ባለቤት በየትኛውም ነጥብ ላይ ፍላጎት ካላሳየ የመንግሥት አገልግሎታችን የመጨረሻ ገጽ ላይ ከሚወጡት የመግቢያ ሐሳቦች መካከል አንድ ጥያቄ በማቅረብ በሚቀጥለው ጊዜ ለምታደርገው ውይይት እንደ መሠረት አድርገህ ልትጠቀምበት ትችላለህ።
10 ትክክለኛ ማስታወሻ ያዝ፦ ከቤት ወደ ቤት መመዝገቢያ ቅጽህ በትክክልና በተሟላ ሁኔታ መሞላት ይኖርበታል። አንድ ሰው አነጋግረህ ስትጨርስ የቤቱን ባለቤት ስምና አድራሻ ጻፍ። የጻፍከውም ዝርዝር ትክክል መሆኑን አረጋግጥ። የግለሰቡን ሁኔታ ጻፍ። ውይይት ያደረጋችሁበትን ርዕስ፣ ያነበብካቸውን ጥቅሶች፣ ያበረከትከውን ጽሑፍና ተመልሰህ በምትሄድበት ወቅት የምትመልሰውን ጥያቄ በማስታወሻ ደብተርህ ላይ አስፍር። ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተህ ውይይት ያደረግህበትንና ተመልሰህ እንደምትሄድ የተናገርከውን ቀንና ሰዓት ጨምረህ ጻፍ። አሁን መመዝገቢያ ቅጽህ የተሟላ ስለሆነ እንዳይጠፋብህ በጥንቃቄ ያዘው! ማስታወሻውን ሌላ ጊዜ ለመመልከት በሚያስችልህ ጥሩ ቦታ አስቀምጠው። ስለ ግለሰቡና ቀጣዩን ጉብኝት እንዴት እንደምታከናውን አስብ።
11 ዓላማህን እወቅ፦ በመጀመሪያ ሞቅ ያለ የወዳጅነት ስሜት በማሳየት የቤቱ ባለቤት ዘና እንዲል የተቻለህን ሁሉ አድርግ። ጥያቄ ሳታበዛ ለእርሱ ያለህን አሳቢነት ግለጽ። ቀጥሎ ባለፈው ጉብኝትህ ወቅት ያቀረብከውን ጥያቄ አስታውሰው። የሚሰነዝረውን አስተያየት በጥንቃቄ አዳምጥ፤ ለሚሰጠውም ሐሳብ ልባዊ አድናቆት አሳይ። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ለምን ተግባራዊ እንደሆነ ግለጽ። ከተቻለ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት ከተሰኘው መጽሐፍ ለዚህ ጉዳይ ማብራሪያ በሚሰጠው ክፍል ላይ እንዲያተኩር አድርግ። ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርግበት ዋና ዓላማ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር እንደሆነ ምን ጊዜም አትዘንጋ።
12 እውቀት የተሰኘው መጽሐፍ የሚያስተላልፈው ቀጥተኛ ሐሳብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በምንመራበት ጊዜ ተማሪዎች በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙና ከይሖዋ ድርጅት ጋር እንዲተባበሩ ‘በድፍረት’ እንድናበረታታ ያነሳሳናል። ባለፉት ጊዜያት ግለሰቦች ከእኛ ጋር በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ከመጋበዛችን በፊት ረዘም ላለ ጊዜ እንዲያጠኑ እናደርግ ነበር። አሁን ግን ብዙ ተማሪዎች ጥናት እንደጀመሩ ወዲያውኑ በስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። ይህም ፈጣን እድገት እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል።
13 አንድ ባልና ሚስት ለሥራ ባልደረባቸው መሠከሩለት። ሰውየው ለእውነት ፍላጎት ሲያሳይ እውቀት በተሰኘው መጽሐፍ ጥናት እንዲጀምር ጋበዙት። በዚያኑ ጊዜ ለበርካታ ጥያቄዎቹ መልስ እንዲያገኝ በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንደሚኖርበት ነገሩት። ሰውየው እንዲያጠና ያቀረቡለትን ግብዣ ተቀበለና በሳምንት ሁለት ጊዜ ከማጥናቱም በላይ በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይም አዘውትሮ መገኘት ጀመረ።
14 አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? በተሰኘው ብሮሹር ተጠቀም፦ “የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች” በተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ላይ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተሰኘውን ብሮሹር አግኝተናል። ይህ ብሮሹር ምንም ዓይነት የትምህርት ደረጃ ይኑራቸው ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር በጣም ጠቃሚ ነው። ብሮሹሩ መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በመዳሰስ ሰፊ ትምህርቶችን አቅፎ ይዟል። የአምላክን እውቀት በማስተላለፍ በኩል ውጤታማ መሣሪያ ነው። እውነትን ግልጽ በሆነና ቀለል ባለ መንገድ የሚያብራራ በመሆኑ ሌሎች ሰዎችን አምላክ የሚፈልግባቸውን ብቃቶች ለማስተማር ሁላችንም ልንጠቀምበት እንችላለን። ብዙ አስፋፊዎች በዚህ ብሮሹር አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የመምራት መብት ሊያገኙ ይችላሉ።
15 እውቀት የተሰኘውን መጽሐፍ ለማጥናት ጊዜ እንደሌላቸው የሚሰማቸው አንዳንድ ግለሰቦች አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? በተሰኘው ብሮሹር አማካኝነት አጠር ያለ ጥናት ለማድረግ ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ። በተማሯቸው ነገሮች በጣም ይደሰታሉ! ገና ሁለት ወይም ሦስት ገጾች እንዳጠኑ ብዙ ሰዎችን ለዘመናት ግራ ሲያጋቧቸው ለኖሩት ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ያገኛሉ:- እውነተኛው አምላክ ማን ነው? ዲያብሎስ ማን ነው? አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? እውነተኛውን ሃይማኖት ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? ብሮሹሩ እውነትን ቀለል ባለ መንገድ የሚያቀርብ ቢሆንም የሚያስተላልፈው መልእክት ኃይለኛ ነው። ብሮሹሩ ሽማግሌዎች ከጥምቀት እጩዎች ጋር የሚከልሱትን ቁልፍ ነጥቦች ይሸፍናል፤ እንዲሁም እውቀት በተሰኘው መጽሐፍ የተሟላ ጥናት ለማካሄድ እንደ መንደርደሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።
16 በተመላልሶ መጠየቅ ጊዜ ጥናት ለማስጀመር በቀላሉ እንዲህ ለማለት ትችላለህ:- “ጥቂት ደቂቃዎችን ብቻ አጥፍተው አስፈላጊ ለሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንደሚችሉ ያውቃሉ?” ከዚያም በብሮሹሩ ውስጥ ካሉት ትምህርቶች መግቢያ ላይ ከሰፈሩት ጥያቄዎች መካከል አንዱን ጠይቅ። ለምሳሌ በእድሜ ከገፋ ሰው ጋር የምትነጋገር ከሆነ እንዲህ ልትል ትችላለህ:- “ባለፉት ጊዜያት ኢየሱስ ሰዎችን እንደፈወሰ እናውቃለን። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ወደፊት ለታመሙ፣ ለአረጋውያንና ለሙታን ምን ያደርግላቸዋል?” መልሶቹ በትምህርት 5 ላይ ይገኛሉ። የሃይማኖት ዝንባሌ ያለውን ሰው “አምላክ ሁሉንም ጸሎቶች ይሰማል?” የሚለው ጥያቄ ሊማርከው ይችላል። መልሱ ትምህርት 7 ላይ ይገኛል። የአንድ ቤተሰብ አባላት “አምላክ ወላጆችና ልጆች ምን እንዲያደርጉ ይፈልጋል?” የሚለውን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ይፈልጋሉ። ትምህርት 8ን በሚያጠኑበት ጊዜ መልሱን ያገኛሉ። ሌሎቹ ጥያቄዎችም የሚከተሉት ናቸው:- “ሙታን ሕያዋንን ሊጎዱ ይችላሉን?” ትምህርት 11 ላይ ተብራርቷል፤ “ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሃይማኖቶች የኖሩት ለምንድን ነው?” ትምህርት 13 ላይ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፤ እንዲሁም “የአምላክ ወዳጅ ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብሃል?” በትምህርት 16 ላይ ተሸፍኗል።
17 ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን እርዳቸው፦ የውጭ አገር ቋንቋ ስለሚናገሩ የቤት ባለቤቶችስ ምን ለማለት ይቻላል? ከተቻለ በሚያውቁት ቋንቋ ቢማሩ የተሻለ ይሆናል። (1 ቆሮ. 14:9) የጉባኤ ጸሐፊያችሁ እንደነዚህ የመሰሉ አድራሻዎችን ሊያስተላለፍ አሊያም አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ዝግጅቶችን ሊያደርግ ይችላል።
18 ሳትዘገይ ተመላልሶ መጠየቅ አድርግ፦ ተመላልሶ መጠየቅ ከማድረግህ በፊት ምን ያህል ጊዜ መቆየት ይኖርብሃል? አንዳንድ አስፋፊዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ውይይት ካደረጉ በኋላ በቀጣዩ ወይም በሁለተኛው ቀን ተመላልሶ መጠየቅ ያደርጋሉ። ሌሎች ደግሞ ትንሽ ቆየት ብለው በዚያው ቀን ተመልሰው ይሄዳሉ! ይህ በጣም ቀርቦ ይሆን? አብዛኛውን ጊዜ የቤቱ ባለቤቶች ምንም ዓይነት ቅሬታ ያላቸው አይመስሉም። ብዙውን ጊዜ ይበልጥ ይሆናል የሚል አመለካከትና ድፍረት ማሳየት የሚኖርበት ለመጀመሪያ ጊዜ ያነጋገረው አስፋፊ ነው። የሚከተለውን ተሞክሮ ተመልከት።
19 አንድ ቀን አንድ የ13 ዓመት አስፋፊ ከቤት ወደ ቤት እያገለገለ ሳለ ሁለት ሴቶች አብረው ሲሄዱ ተመለከተ። ሰዎችን በተገኙበት ቦታ ሁሉ እንድናነጋግራቸው የተሰጠውን ማበረታቻ በማስታወስ ሴቶቹን በመንገድ ላይ ቀርቦ አነጋገራቸው። እነርሱም ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት አሳዩ። በተጨማሪም ሁለቱም እውቀት የተሰኘውን መጽሐፍ ወሰዱ። ወጣቱ ወንድም አድራሻቸውን ተቀብሎ ከሁለት ቀን በኋላ ተመልሶ አነጋገራቸው። ከዚያም ከእያንዳንዳቸው ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ።
20 አንድ ግለሰብ ለእውነት ፍላጎት በሚያሳይበት ጊዜ በዚያም ሆነ በዚህ ተቃውሞ እንደሚደርስበት እርግጠኛ ልንሆን እንችላለን። ለመጀመሪያ ጊዜ ውይይት ካደረግን በኋላ ወዲያው ተመልሰን መሄዳችን ከዘመዶቹ፣ ከቅርብ ወዳጆቹና ከሌሎች የሚደርስበትን ተጽእኖ መቋቋም እንዲችል ጥንካሬ ይሰጠዋል።
21 በሕዝብ ማዘውተሪያ ስፍራዎች የምናገኛቸው ሰዎች ያሳዩትን ፍላጎት ማሳደግ፦ አብዛኞቻችን በመንገድ ላይ፣ በሕዝብ መጓጓዣዎች፣ በገበያ፣ በመናፈሻና በሌሎችም ሥፍራዎች እንሰብካለን። ጽሑፍ ከማበርከታችንም በተጨማሪ ፍላጎታቸውን ማሳደግ ይኖርብናል። ይህን ዓላማ በመያዝ አነጋግረነው ፍላጎት ያሳየ የእያንዳንዱን ሰው ስም፣ አድራሻና ከተቻለም የስልክ ቁጥር ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይህን መረጃ ለማግኘት አንተ እንደምታስበው ይህን ያህል አስቸጋሪ አይደለም። ውይይታችሁን ወደ ማጠናቀቁ አካባቢ ስትደርሱ የማስታወሻ ደብተርህን አውጥተህ “ይህን ውይይታችንን መቀጠል የምንችልበት መንገድ ይኖር ይሆን?” ብለህ ጠይቅ። ወይም “ይጠቅምዎታል ብዬ ያሰብኩት አንድ ርዕስ ባነብልዎት ደስ ይለኛል። እቤትዎ ወይስ መሥሪያ ቤትዎ ላምጣልዎ?” ብለህ ጠይቅ። አንድ ወንድም “ስልክ ቁጥርዎ ስንት ነው?” ብሎ ይጠይቃል። በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ከሦስት ሰዎች በስተቀር ሁሉም የስልክ ቁጥራቸውን ለመስጠት ፈቃደኞች እንደነበሩ ጽፏል።
22 ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ለማግኘትና ያሳዩትን ፍላጎት ለማሳደግ ስልክ ተጠቀም፦ አንዲት አቅኚ ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ በሚደረግባቸው ሕንጻዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ለማግኘት በስልክ ትጠቀማለች። በተመሳሳይ መንገድ ተመላልሶ መጠየቅ ታደርጋለች። ለመጀመሪያ ጊዜ ስታነጋግራቸው እንዲህ ትላለች:- “አንተዋወቅም። መጽሐፍ ቅዱስ የያዛቸውን ትምህርቶች ለማካፈል አካባቢዎ የሚኖሩ ሰዎችን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እያደረግሁ ነው። ጥቂት ጊዜ ካለዎት . . . ላይ የሚገኘውን ተስፋ ባነብልዎት ደስ ይለኛል።” ጥቅሱን ካነበበች በኋላ እንዲህ ትላለች:- “ይህ ጊዜ መጥቶ ማየት ብንችል አስደሳች አይሆንም? ይህን ስላነበብኩልዎ ደስ ብሎኛል። እርስዎም እንደ እኔ ከተሰማዎት እንደገና ደውዬ በሌላ ጥቅስ ላይ ውይይት ብናደርግ ደስ ይለኛል።”
23 በስልክ ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ጊዜ ቀደም ሲል ስላደረጉት ውይይት የቤቱን ባለቤት ካስታወሰች በኋላ ክፋት በሚወገድበት ጊዜ ነገሮች ሁሉ ምን መልክ እንደሚኖራቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ልታነብላቸው እንደምትፈልግ ትነግራቸዋለች። ከዚያም ከቤቱ ባለቤት ጋር አጠር ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ታደርጋለች። እስካሁን ባደረገቻቸው በርካታ የስልክ ውይይቶች 35 ሰዎች እቤታቸው እንድትመጣ ሲጋብዟት ሰባት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ጀምራለች!
24 በንግድ ቦታዎች ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ክትትል አድርግ፦ ከሱቅ ወደ ሱቅ የሚደረገው ምሥክርነት መጽሔት ከማበርከት ሌላ ብዙ ነገሮች ማድረግን ይጨምራል። ብዙ የሱቅ ባለቤቶች ለእውነት ልባዊ ፍላጎት አላቸው፤ ይህን ፍላጎታቸውን ማሳደግ ይገባል። በአንዳንድ ሁኔታዎች እዛው በሱቃቸው ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ወይም ጥናት እንኳን ሳይቀር ማድረግ ይቻል ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ አንተና ፍላጎት ያሳየው ሰው በምሳ እረፍት ወይም በሌላ አመቺ ሰዓት ላይ መገናኘት ትችሉ ይሆናል።
25 በንግድ ቦታዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር እንዲህ ልትል ትችላለህ:- “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን እንዴት እንደሚከናወን ለማሳየት የሚፈጀው 15 ደቂቃ ብቻ ነው። የሚመችዎ ከሆነ ጥናቱ እንዴት እንደሚጠና ባሳይዎ ደስ ይለኛል።” ከዚያም ያልከውን ደቂቃ ሳታሳልፍ ጥናቱ እንዴት እንደሚመራ አሳየው። በንግድ ቦታዎች አካባቢ ረዘም ላለ ጊዜ ውይይት ለማድረግ የማይቻል ከሆነ በባለ ሱቁ መኖሪያ ቤት ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ጥሩ ሊሆን ይችላል።
26 ምንም ዓይነት ጽሑፍ ባታበረክትም እንኳ ተመላልሶ መጠየቅ አድርግ፦ ጽሑፍ ተበረከተም አልተበረከተ መጠነኛ የሆነ ፍላጎት ላሳየ ሰው እንኳ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ተገቢ ነው። እርግጥ የቤቱ ባለቤት ለመንግሥቱ መልእክት ምንም ዓይነት ፍላጎት እንዳላሳየ ግልጽ ከሆነ ሌላ ሰው ማነጋገር የተሻለ ነው።
27 አንዲት እህት ከቤት ወደ ቤት በምታገለግልበት ጊዜ ጥሩ የወዳጅነት ስሜት ካላት ይሁን እንጂ ፈጽሞ መጽሔት ለመውሰድ ከማትፈልግ ሴት ጋር ተገናኘች። አስፋፊዋ “ለረዥም ቀናት ስለ እርሷ ሳወጣ ሳወርድ ከቆየሁ በኋላ እንደገና ላነጋግራት ወሰንኩ” ስትል ጽፋለች። በመጨረሻ እህት ጸለየችና በድፍረት የሴትዮዋን በር አንኳኳች። የቤቱ ባለቤት ወደ ቤት እንድትገባ ስትጋብዛት በጣም ተደሰተች። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ፤ በቀጣዩ ቀንም ዳግመኛ አጠኑ። ከጊዜ በኋላም የቤቱ ባለቤት ወደ እውነት መጣች።
28 ብዙ ሥራ ለማከናወን ቀደም ብለህ እቅድ አውጣ፦ በየሳምንቱ ተመላልሶ መጠየቅ የሚደረግበት የተወሰነ ቀን መመደብ ጥሩ እንደሆነ ሐሳብ ተሰጥቷል። ጥሩ እቅድ ማውጣት በዛ ያሉ ሥራዎችን ለማከናወን ያስችላል። ከቤት ወደ ቤት በምትሠራበት አካባቢ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ዝግጅት አድርግ።
29 ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጀመር በኩል የተሳካላቸው ወንድሞች ለሰዎች ልባዊ ስሜት ማሳየትና ለመጀመሪያ ጊዜ ውይይት ከተደረገ በኋላ ባሉት ጊዜያት ስለ ሰዎቹ ማሰብ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል። በተጨማሪም ለውይይት የሚሆን ማራኪ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕስ ማዘጋጀትና ለመጀመሪያ ጊዜ ውይይት አድርገን ከመለያየታችን በፊት ተመላልሶ መጠየቅ በምናደርግበት ጊዜ ውይይት ለማድረግ የሚያገለግል መሠረት መጣል አስፈላጊ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ፍላጎታቸውን ለማሳደግ ሳይዘገዩ ተመልሶ መሄድ ጠቃሚ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማስጀመር ግብ ዘወትር በአእምሮ መያዝ ይገባል።
30 ተመላልሶ መጠየቅ በማድረጉ ሥራ ስኬታማ ለመሆን ከሁሉ የበለጠው አስፈላጊው ባሕርይ ድፍረት ነው። ድፍረት እንዴት ሊገኝ ይችላል? ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹን ለማወጅ “በአምላካችን ደፈርን” ብሎ በተናገረ ጊዜ መልሱን ሰጥቷል። በዚህ በኩል እድገት ማድረግ የሚኖርብህ ከሆነ ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልይ። ከዚያም ከጸሎትህ ጋር በመስማማት ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተከታተል። ይሖዋ ጥረትህን በእርግጥ ይባርክልሃል!
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ ስኬታማ መሆን የሚቻልበት መንገድ
■ ለሰዎች በግል ልባዊ አሳቢነት አሳይ።
■ ለውይይት የሚሆን አንድ ማራኪ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕስ ምረጥ።
■ ለቀጣዩ ጉብኝት መሠረት ጣል።
■ ተሰናብተህ ከሄድክ በኋላም ስለ ግለሰቡ አስብ።
■ ፍላጎት ያሳዩትን ተከታትሎ ለመርዳት ከአንድ ወይም ከሁለት ቀን በኋላ ተመልሰህ ሂድ።
■ ዓላማህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር መሆኑን አትዘንጋ።
■ ይህን ሥራ በድፍረት ለማከናወን እንድትችል ጸልይ።