አረጋውያን መስበካቸውን አያቋርጡም
1 ብዙ ሰዎች በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ መደበኛ ከሆነው ሰብዓዊ ሥራቸው ጡረታ ወጥተው በቀረው የሕይወት ዘመናቸው ጭንቅ የሌለበት ኑሮ ለመምራት ያስባሉ። ብዙ እንደሠሩና አሁን ማረፍ እንደሚገባቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። ወይም በቀረው የሕይወት ዘመናቸው እየተደሰቱ ለመኖር ይፈልጉ ይሆናል።—ሉቃስ 12:19
2 እኛ ራሳችንን ለይሖዋ የወሰንን አገልጋዮቹ እንደመሆናችን መጠን ስለ ሕይወት ያለን አመለካከት ከዚህ የተለየ ነው። ከአምላክ አገልግሎት ጡረታ መውጣት እንደሌለ እናውቃለን። ‘የዘላለም ሕይወትን ስለምንጠባበቅ’ አመለካከታችን ብሩህ ነው። (ይሁዳ 21) ለብዙ ዓመታት የተከማቸ እውቀትና ተሞክሮ የአንድን ሰው ግንዛቤና ጠለቅ ብሎ የመረዳት ችሎታ ሊጨምርለት ይችላል። ይህም የበለጠ ጥበበኛና ሚዛናዊ እንዲሆን እንዲሁም ለሕይወት የጠለቀ አድናቆት እንዲያሳይ ሊያደርገው ይችላል። እነዚህ ባሕርያት አንድን ሰው የምሥራቹ አገልጋይ በመሆን ለሚያከናውነው አገልግሎት በጣም ይጠቅሙታል።
3 እርጅና በአካል የመድከም ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የግለሰቡን አስተሳሰብም ይጨምራል። ረዥም ጊዜ ለመኖር የምታስብ ከሆነና በአመለካከትህም ወጣት ሆነህ ለመቆየት ጥረት የምታደርግ ከሆነ በሁለቱም አቅጣጫ ሊሳካልህ ይችላል። አረጋውያን መንፈሳዊ እውቀታቸውን በማሳደግና ይህንኑ ለሌሎች ሰዎች በማካፈል ሕይወታቸውን አስደሳች ሊያደርጉት ይችላሉ።—1 ቆሮ. 9:23
4 ሕያው ምሳሌዎች፦ ሰማንያ ስድስት ዓመት የሆናት አንዲት እህት እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “እውነትን ከሰማሁበት ጊዜ ጀምሮ ያለፉትን 60 ዓመታት ሳስብ በልቤ ያለው የሚያጽናና የአምላክ ተስፋ ይጠነክራል። አዎን፣ ከታማኞቹ ጋር ታማኝ ሆኖ የሚገኘው ይሖዋ የተትረፈረፈ ደስታ እንድናጭድ እያደረገን ነው።” (መዝ. 18:25 NW) አንድ በዕድሜ የሸመገለ ወንድም የሚስቱን መሞት ሲሰማ ከባድ ድንጋጤ ላይ እንደወደቀና ከዚያ በኋላም ጤንነቱ በጣም እንደተቃወሰ ያስታውሳል። እንዲህ ብሏል:- “ሆኖም ይገባኛል በማልለው የይሖዋ ደግነት ከበሽታዬ በደንብ ላገግም በመቻሌ ከሁለት ዓመታት በኋላ በአቅኚነት አገልግሎት ልካፈል ችያለሁ። የስብከት እንቅስቃሴዬን ከፍ ካደረግሁ በኋላ ጤንነቴ በመሻሻሉ ይሖዋን በጣም አመሰግነዋለሁ!”
5 ብዙ አረጋውያን ጤንነታቸውና ጉልበታቸው እስከፈቀደላቸው ድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በስብከታቸው ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ ማድረጋቸው እንዴት የሚያስመሰግን ነው! “አምላኬ፣ ከታናሽነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤ እስከ ዛሬም ተአምራትህን እነግራለሁ” በማለት በደስታ የሚናገሩበት ጥሩ ምክንያት አላቸው።—መዝ. 71:17