የአውራጃ ስብሰባ ማሳሰቢያዎች
ጥምቀት፦ ቅዳሜ ጠዋት ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት የጥምቀት እጩዎች በተመደበላቸው ቦታ መቀመጥ አለባቸው። እያንዳንዱ ተጠማቂ ልከኛ ልብስና ፎጣ ይዞ መምጣት አለበት። ባለፉት ጊዜያት አንዳንዶች የለበሷቸው ልብሶች ተገቢ ያልሆኑና የተመልካቾችን ሐሳብ ወደ ሌላ የሚያዞሩ እንደሆኑ ተስተውሏል። የጥምቀት እጩው ሊለብሰው የሚያስበው ልብስ ውኃ ሲነካው ሰውነትን የሚያሳይ ወይም ሰውነት ላይ የሚለጠፍ መሆን አለመሆኑን አስቀድሞ ማየት ጥሩ ይሆናል። በተለይ ስስ የፖሊስተር ልብሶች ተስማሚ እንደማይሆኑ ታይቷል። ሽማግሌዎች አገልግሎታችን በተባለው መጽሐፍ ላይ የሚገኙትን ጥያቄዎች ከእጩ ተጠማቂዎች ጋር በሚከልሱበት ጊዜ እያንዳንዱ ተጠማቂ እነዚህን ነጥቦች የተገነዘበ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ተናጋሪው የጥምቀት ንግግርና ጸሎት ካቀረበ በኋላ የመድረኩ ሊቀመንበር መዝሙር እንዲዘመር ይጋብዛል። የመጨረሻው ስንኝ ከተዘመረ በኋላ አስተናጋጆች እጩዎችን ጥምቀቱ ወደሚከናወንበት ቦታ ይወስዷቸዋል። አንድ ሰው ራሱን መወሰኑን የሚያሳይበት የጥምቀት እርምጃ በግለሰቡና በይሖዋ መካከል ብቻ ያለ የግል ጉዳይ ነው። ስለሆነም ለፎቶግራፍ ለማመቻቸት ሲባል መዘግየት አይገባም።
ደረት ላይ የሚለጠፉ ካርዶች፦ እባካችሁ ስብሰባው በሚካሄድበት ከተማ በምትቆዩበት ጊዜ ሁሉ እንዲሁም ወደ እዚያ ስትሄዱና ስትመለሱ ለ1997 የተዘጋጀውን ካርድ ደረታችሁ ላይ ለጥፉ። እንዲህ ማድረጋችን ብዙውን ጊዜ ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት ያስችለናል። ደረት ላይ የሚለጠፉት ካርዶችና መያዣቸው በስብሰባው ላይ ስለማይገኙ በጉባኤያችሁ በኩል ማግኘት ይኖርባችኋል። ደረት ላይ የሚለጠፉትን ካርዶች ለእናንተና ለቤተሰቦቻችሁ ለመጠየቅ ስብሰባው የሚጀመርበት ቀን እስኪደርስ ድረስ አትጠብቁ። የወቅቱን በቅድሚያ የተሰጠ የሕክምና መመሪያ/የሕክምና ባለሙያዎችን ከኃላፊነት ነፃ የሚያደርገውን ሰነዳችሁን መያዝ አትርሱ።
መስተንግዶ፦ የማረፊያ ቦታ የሚፈልጉ ወንድሞች ስማቸውን፣ እድሜያቸውን፣ የተጠመቁበትን ቀንና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮችን ለጉባኤው ጸሐፊ መንገር የሚገባቸው ሲሆን እርሱም ከአውራጃ ስብሰባው አንድ ወር ቀደም ብሎ ለአውራጃ ስብሰባው የመስተንግዶ ክፍል ይልከዋል። እነዚህ ማረፊያዎች የሚዘጋጁልን የአውራጃው ስብሰባ ለሚደረግባቸው ቀናት ብቻ እንጂ ከስብሰባው በፊት ወይም በኋላ ለእረፍት ወይም ለሌላ ጉዳይ እንዳልሆነ ልናስታውሳችሁ እንወዳለን።
የፈቃደኝነት አገልግሎት፦ በስብሰባው ወቅት ከሚኖሩት የሥራ ክፍሎች በአንዱ ውስጥ ለማገልገል ጊዜ ልትመድቡ ትችላላችሁን? ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ቢሆንም እንኳ ወንድሞቻችንን ማገልገሉ ትልቅ እገዛ ከመሆኑም ሌላ ለእኛም ከፍተኛ እርካታ ያመጣልናል። በዚህ ረገድ እርዳታ ማበርከት የምትችሉ ከሆነ በስብሰባው ቦታ ለሚገኘው ለፈቃደኛ አገልግሎት ማስተባበሪያ ክፍል አስታውቁ። ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ከወላጆቻቸው ወይም ኃላፊነት ሊወስድ ከሚችል ሌላ ትልቅ ሰው ጋር በመሆን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ።
የማስጠንቀቂያ ምክር፦ ችግር ሊያስከትሉ ለሚችሉት ነገሮች ንቁ በመሆን በመጠባበቅ ከጥንቃቄ ጉድለት የሚመጡ ችግሮችን ማስወገድ እንችላለን። ብዙዉን ጊዜ ሌቦችና አንዳንድ ይሉኝታ የሌላቸው ሰዎች ከአካባቢያቸው ርቀው በመጡ ሰዎች ላይ ዝርፊያ ይፈጽማሉ። የመኪናዎቻችሁ በሮች ሁልጊዜ መቆለፋቸውንና መኪናውን ሰብሮ ለመዝረፍ የሚጋብዝ ከውጭ ሊታይ የሚችል ነገር ትታችሁ አለመሄዳችሁን አረጋግጡ። ሌቦችና ኪስ አውላቂዎች በብዛት በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ ዓይናቸውን ይጥላሉ። ውድ ዋጋ ያላቸውን ማናቸውንም ነገሮች መቀመጫችሁ ላይ ትታችሁ መሄዱ ጥበብ አይሆንም። ዙሪያችሁ ያለው ሁሉ ክርስቲያን ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አትችሉም። ሌሎች ለምን እንዲፈተኑ እናደርጋለን? ከውጭ የገቡ ሰዎች ልጆችን አባብለው ለመውሰድ ሙከራ እንዳደረጉ የሚገልጹ ሪፖርቶች ደርሰውናል። ልጆቻችሁን በማንኛውም ጊዜ ከዓይናችሁ አታርቋቸው።