የሙሉ ጊዜ ምሥክር ነህን?
1 ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ አዎን የሚል ነውን? ምንም እንኳን ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ አገልጋዮች ሁሉ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መሳተፍ ባይችሉም ሁላችንም ራሳችንን የይሖዋ የሙሉ ጊዜ ምሥክሮች እንደሆንን አድርገን መመልከት አለብን ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ አይደለምን? ራሳችንን እንዲህ አድርገን መመልከት እንዳለብን የተረጋገጠ ነው።
2 የትርፍ ጊዜ ክርስቲያን መሆን አይቻልም። ኢየሱስ ስለ አባቱ ሲናገር:- “እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና” ብሏል። (ዮሐ. 8:29) ተመሳሳይ ስሜት የነበረው ጳውሎስም “ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” ሲል አጥብቆ አሳስቦናል። (1 ቆሮ. 10:31) ከዚህ የተነሳ ሁላችንም ራሳችንን የሙሉ ጊዜ የይሖዋ ምሥክር አድርገን መቁጠር አለብን። ራሳችንን በዚህ መንገድ መመልከታችን በማንኛውም እንቅስቃሴያችን ላይ በጎ ተጽእኖ ያሳድራል።
3 ማስረጃዎቹን መርምር፦ የሰውነት አያያዛችን፣ አነጋገራችንና ጠባያችን በእርግጥ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ለሌሎች ሰዎች ሊጠቁም ይችላል። በመስክ አገልግሎት ወይም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በምንገኝበት በማንኛውም ጊዜ ልከኛ የሆነ አለባበስ፣ የሚያንጽ ንግግርና ተገቢ የሆነ ጠባይ አስፈላጊ መሆኑን አንዘነጋም። ትምህርት ቤት ስንሄድም ሆነ፣ ተቀጥረን በምንሠራበት ቦታ ወይም ስንዝናና በምናደርገው ማንኛውም ነገር በይሖዋ የጽድቅ አቋሞች እንደምንኖር ማሳየት ይኖርብናል።
4 ኢየሱስ “በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። . . . መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 5:14-16) በምናደርገው በማንኛውም ነገርና በየትኛውም ጊዜ ይህ በእኛ ላይ መንጸባረቅ አለበት። ባለንበት ቦታ ወይም እየሠራን ባለነው ሥራ በማሳበብ ምሥክርነቱን ከመስጠት ወደኋላ የምንል ከሆነ ‘ይሖዋን የማገለግለው ሙሉ ጊዜ ነው ወይስ አልፎ አልፎ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልገናል። ማንኛውንም አጋጣሚ በመጠቀም ለሌሎች ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች መናገር አለብን።
5 “የሙሉ ጊዜ ምሥክር ነህን?” ለሚለው ጥያቄ በሚያስተጋባ ድምፅ “አዎን!” የሚል መልስ በምንሰጥበት ጊዜ ይሖዋን እንደምናስከብርና እንደምናስደስት እናስታውስ።