ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቷል
1 ጳውሎስ ቀናተኛ የምሥራቹ ሰባኪ ስለነበር ይበልጥ ምሥራቹ ሊሰበክላቸው ወደሚገቡ ክልሎች እየሄደ ያገለግል ነበር። ከእነዚህም አንዱ የኤፌሶን ከተማ ነበር። በኤፌሶን ከተማ ባደረገው የስብከት ሥራ አመርቂ ውጤት አግኝቶ ስለነበር ለክርስቲያን ወንድሞቹ “ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቶልኛል” በማለት ሊጽፍ ችሏል። (1 ቆሮ. 16:9) ጳውሎስ በዚህ ክልል ማገልገሉን በመቀጠሉ ብዙ የኤፌሶን ሰዎች አማኞች እንዲሆኑ ረድቷቸዋል።—ሥራ 19:1-20, 26
2 በዛሬው ጊዜም ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቶልናል። በየዓመቱ የአገልግሎት ክልላቸውን በሙሉ አጣርተው መሸፈን የማይችሉትን ጉባኤዎች እንድንረዳ ግብዣ ቀርቦልናል። በዚህ መንገድ የምናበረክተው አስተዋጽኦ በአንዳንድ ቦታዎች ያለውን የምሥራቹ አገልጋዮች እጥረት ሊያቃልል ይችላል።—ከ2 ቆሮንቶስ 8:13-15 ጋር አወዳድር።
3 የምሥራቹ አገልጋዮች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ትችላለህ? ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረህ ማገልገል የምትችልበትን ሁኔታ በጸሎት አስበህበት ታውቃለህ? በምትኖርበት ከተማ ውስጥ ያለ ጉባኤ መርዳት ትችል ይሆናል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ስለ ጉዳዩ አነጋግረህ ምን ሐሳብ እንደሚሰጥህ ለምን አትሰማም? አለበለዚያም በራስህ የጉባኤ ክልል ውስጥ ማንም ሊረዳቸው ያልቻለ መስማት የተሳናቸው ወይም የውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪዎች የሆኑ ብዙዎች ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል። እነርሱን መርዳት እንድትችል ቋንቋቸውን ለመማር ጥረት ማድረግ ትችላለህ? ከዚህም በተጨማሪ በአቅራቢያህ ያለ በሌላ ቋንቋ የሚጠቀም ቡድን ወይም ጉባኤ ‘ተጨማሪ ሠራተኞች ወደ መከሩ እንዲልክ የመከሩን ጌታ ሲለምን’ ቆይቶ ይሆናል። (ማቴ. 9:37, 38) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካለ እርዳታ ለመስጠት ትችላለህ?
4 ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያን ቤተሰቦች በመከሩ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ ሲሉ ወደ ሌሎች አገሮች ሄደዋል። በዚህ ሥራ ለመሳተፍ ወደ ሌላ አገር የሄዱ አንድ ባልና ሚስት ይህን ለማድረግ የተነሳሳነው “ይበልጥ እርዳታ መስጠት በምንችልበት ቦታ ይሖዋን ለማገልገል ስለፈለግን ነው” ብለዋል። በዚሁ በአገራችን ውስጥ ሌላ ቦታ ሄደህ የማገልገል ፍላጎቱ ካለህና የምትችል ከሆነ ወይም ሌላ አገር ሄደህ ለማገልገል ብቁ ከሆንህ በመጀመሪያ የወጠንከውን ሐሳብ ከጉባኤህ ሽማግሌዎች ጋር ተነጋገር።
5 የምሥራቹ አገልጋዮች ይበልጥ የሚያስፈልጉት የት እንደሆነ ለማወቅ ማኅበሩን መጠየቅ ከፈለግህ ፍላጎትህን በደብዳቤ በግልጽ በማስፈር ለጉባኤህ የአገልግሎት ኮሚቴ ስጥ። ኮሚቴው የራሱን አስተያየት አክሎ ደብዳቤውን ለማኅበሩ ይልከዋል። ያም ሆነ ይህ ሥራ የሞላበት ትልቁ በር ክፍት እስከሆነ ድረስ ሁላችንም በይሖዋ አገልግሎት ሥራ የበዛልን ሆነን እንቀጥል።—1 ቆሮ. 15:58