የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ የትዳር ጓደኞችን መርዳት
1 የትዳር ጓደኛሞች በእውነተኛው አምልኮ ተሳስረው ማየት በጣም ያስደስታል። ሆኖም በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ የእውነትን መንገድ የተቀበለው ከሁለቱ የትዳር ጓደኛሞች አንዱ ብቻ ነው። ምስክር ያልሆኑ የትዳር ጓደኞችን ልንረዳቸውና ከጎናችን ሆነው ይሖዋን እንዲያመልኩ ልናበረታታቸው የምንችለው እንዴት ነው?—1 ጢሞ. 2:1-4
2 ውስጣዊ ስሜታቸውን መረዳት፦ ምንም እንኳ ምስክር ያልሆኑ አንዳንድ የትዳር ጓደኞች ተቃዋሚዎች ቢሆኑም አብዛኛውን ጊዜ ችግሩ የግዴለሽነት ወይም ነገሩን በትክክል ያለመረዳት ጉዳይ ነው። አማኝ ያልሆነው ወገን እንደተተወ ሊሰማው አሊያም በትዳር ጓደኛው ወይም ጓደኛዋ አዲስ መንፈሳዊ ፍላጎት ቅናት ሊያድርበት ወይም ሊያድርባት ይችላል። አንድ ባል “ብቻዬን ቤት ውስጥ ስቀር ፈጽሞ እንደተጣልኩ ሆኖ ይሰማኝ ነበር” በማለት ያስታውሳል። አንድ ሌላ ባል ደግሞ “ባለቤቴና ልጆቼ ትተውኝ እንደ ሄዱ ሆኖ ይሰማኝ ነበር” ብሏል። አንዳንድ ባሎች በሃይማኖት ምክንያት ቤተሰባቸውን እያጡ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። (መጠበቂያ ግንብ 16-111 ገጽ 20-3 ተመልከት።) ይህን ለማስወገድ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሚቻል ከሆነ ባልየው በጥናት ፕሮግራሙ ወቅት ከሚስቱ ጋር እንዲሆን ማድረግ የተሻለ ነው።
3 ተባብራችሁ ሥሩ፦ ምስክር የሆኑ አንድ ባልና ሚስት ተባብረው በመሥራት ባለትዳር የሆኑ ሰዎችን ወደ እውነት እንዲመጡ በመርዳት ረገድ ተሳክቶላቸዋል። እህት ከሚስትየው ጋር ጥናት ከጀመረች በኋላ ወንድም ባልየውን ሄዶ ያነጋግረዋል። በዚህ መንገድ ተጠቅሞ ባል የሆኑትን ጥናት በማስጀመር ረገድ ብዙውን ጊዜ ይሳካለታል።
4 ተግባቢዎችና ወዳጃዊ መንፈስ ያላችሁ ሁኑ፦ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ቤተሰቦች በእውነተኛው አምልኮ አንድ ላልሆኑ ቤተሰቦች ትኩረት በመስጠት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላሉ። አንዳንዴ ወዳጃዊ በሆነ መንፈስ እየሄዱ መጠየቅ፣ የይሖዋ ምሥክሮች አፍቃሪዎችና ለሌሎች ደህንነት የሚያስቡ መሆናቸውን ምስክር ያልሆነው የትዳር ጓደኛ እንዲገነዘብ ሊረዳው ይችላል።
5 አልፎ አልፎ ሽማግሌዎች፣ ምስክር ያልሆኑ የትዳር ጓደኞችን ለመርዳት በቅርብ ጊዜ ውስጥ የተደረጉትን ጥረቶች በመመርመር ይሖዋን ወደ ማምለክ ደረጃ እንዲደርሱ ምን ተጨማሪ ነገር ማድረግ እንደሚቻል ሊወያዩ ይችላሉ።—1 ጴጥ. 3:1 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ