“አዎንታዊ አመለካከት በመያዝ ምሥራቹን ማቅረብ”
1 ሁላችንም ከምናከናውነው ተግባር በተለይም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ደስታና እርካታ ማግኘት እንፈልጋለን። እንደዚህ ያለውን እርካታ እንድናገኝ የሚረዳን ምንድን ነው? አንዱ ነገር ምንም በማያስቆጨው ሌሎችን የመርዳቱ ሥራ ራሳችንን ስናስጠምድ አዎንታዊ አመለካከት መያዛችን ነው። (ምሳሌ 11:25 NW) አቀራረባችን በምንናገረው ነገር ላይ ከልብ እንደምናምን የሚያሳይ መሆን አለበት። ከልባችን አውጥተን የምንናገር ከሆነ በነገሩ ላይ የጸና እምነት ያለን መሆኑ ጉልህ ሆኖ ይታያል። (ሉቃስ 6:45) አቀራረባችንን ቀደም ብለን መለማመዳችን በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ስንነጋገር የበለጠ የመተማመን ስሜት እንዲያድርብን ያደርጋል። ይህም የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው ወይም ወጣትነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት የተሰኙትን መጻሕፍት በየካቲት ወር በምናበረክትበት ጊዜ ጉልህ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች አዎንታዊ አመለካከት ይዞ ምሥራቹን በማቅረብ ረገድ ጠቃሚ ሆነው ልታገኛቸው ትችላለህ።
2 ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ ብዙውን ጊዜ በር የሚከፍቱልን ወጣቶች ናቸው። እንዲህ ማለት ትችላለህ:- “ወጣት እንደመሆንህ መጠን ከአንተ ጋር ለመነጋገር አጋጣሚ ስላገኘሁ ደስ ብሎኛል። አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ አንተ ያሉ ወጣቶችን በቀጥታ የሚመለከት ነገር ተናግሯል። [መክብብ 12:1ን አንብብ።] ይህ ጥቅስ የወደፊቱ ሕይወታችን አስደሳች እንዲሆን ከፈለግን በወጣትነታችን አምላክን ልናስታውሰው እንደሚገባ ያሳያል። አንድ ወጣት ፈጣሪያችን ስለሆነው አምላክ ማሰብ እንዳለበት ይሰማሃልን? ይህ የሚያመጣልን ደስታ ይኖራልን? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] እስቲ በዚህ መጽሐፍ ላይ የተሰጠ አንድ ሐሳብ ላሳይህ።” ገጽ 191ን ገልጠህ አንቀጽ 15 ላይ ያሉትን የመጀመሪያዎቹን ሁለት ዓረፍተ ነገሮች አንብብ። ከዚያም ወደ አርዕስት ማውጫው ተመለስና ከርዕሶቹ መካከል ጥቂቶቹን አሳየው።
3 አንዳንድ አስፋፊዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱና ሲመለሱ ወጣትነትህ የተባለውን መጽሐፍ ለወጣቶች በማበርከት ረገድ ተሳክቶላቸዋል። ልክ እንደ መጽሔቶች በመንገድ ላይ ምሥክርነትም በሰፊው ሊበረከት ይችላል። በተጨማሪም አስተማሪዎችንና በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ የአስተዳደር ሠራተኞችን ቀርቦ ማነጋገር ይቻላል። በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚማር አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር በዴስኩ ላይ ወጣትነትህ የተባለውን መጽሐፍ አንድ ቅጂ በማስቀመጥ በሁለት ወር ውስጥ 75 ቅጂዎች ማበርከት ችሏል።
4 በሩን የከፈቱልን ዐዋቂዎች ወይም በዕድሜ የገፉ ሰዎች ቢሆኑስ? አብዛኞቹ ሰዎች በጣም የሚያስቡላቸው ልጆች፣ የወንድም ወይም የእህት ልጆች አለዚያም የልጅ ልጆች አሏቸው። መጽሐፉን ራሳቸው እንዲያነቡት ሐሳብ ከማቅረብ በተጨማሪ ወጣት ለሆኑ ዘመዶቻቸው በስጦታ መልክ ሊያበረክቱት እንደሚችሉም በዘዴ ልንጠቁማቸው እንችላለን።
5 የቤተሰብ ኑሮ በተባለው መጽሐፋችን ላይ ያሉትም አንዳንድ ክፍሎች የወጣቶችን ስሜት ይማርካሉ። ከእነዚህም መካከል በምዕራፍ 2 ላይ በተለይ “በመጀመሪያ ራስህን እወቅ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ያለውን አንቀጽ 7 ወይም “አቻነት” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ያሉት አንቀጽ 13, 15 እና ከ19-21 እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው።
6 “የቤተሰብ ኑሮ” በተባለው መጽሐፍ የምትጠቀም ከሆነ እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “በጊዜያችን ቤተሰብን እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮች ባለፉት ትውልዶች አይታወቁም ነበር ቢባል አይስማሙም? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ይህ የሆነው ለምን ይመስልዎታል? [ለማለት የፈለገውን ነገር እንደገባህ ግለጽ። ከዚያም 2 ጢሞቴዎስ 3:1-3ን አውጥተህ አንብብ።] ‘ለወላጆቻቸው የማይታዘዙና ፍቅር የሌላቸው’ የሚሉት ሐረጎች በጊዜያችን ያሉትን የብዙ ሰዎች ሁኔታ በትክክል ይገልጻሉ። ሆኖም እነዚህ ችግሮች እንደሚከሰቱ የተናገረው አምላክ ራሱ ቤተሰብን ይበልጥ ለማቀራረብ የሚያስችል አስተማማኝ ምክር ጭምር ሰጥቶናል።” በገጽ 2 ላይ የሚገኘውን “የመጽሐፉ አዘጋጂዎች” የሚለውን አንቀጽ አንብብ።
7 አዋቂዎች የቤተሰብ ኑሮ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ብዙ ጠቃሚ ነጥቦች ያገኛሉ። የአርዕስት ማውጫውን አሳያቸው። ምዕራፍ 8 እና 10 ወላጆችን የሚረዱ ሐሳቦች ይዘዋል። ከ4-6 ያሉት ምዕራፎች ችግሮችን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ያሳያሉ። እርግጥ ነው፣ ይህን ስናደርግ ዘዴኛ መሆን አለብን። ምናልባት የቤቱ ባለቤት የጋብቻ ችግሮችን በተመለከተ ለሌሎች ምክር እንዲሰጥ ተጠይቆ ምን ብሎ እንደሚናገር ግራ ገብቶት ሊሆን ይችላል። የቤተሰብ ኑሮ በተባለው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ግን አምላክ የጋብቻ መሥራች እንደመሆኑ መጠን ላገቡ ሰዎች የሰጠውን በጣም አስፈላጊ የሆነ ጥበባዊ ምክር ሊያገኝ ይችላል። በተጨማሪም አዎቂዎች ስለ ጋብቻ ወይም ስለ ማግባት የሚያስቡ ወጣት ዘመዶቻቸውን ለመርዳት ከ2-6 ባሉት ምዕራፎች ሊጠቀሙ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ የራሳቸውን ልጆች ለማስተማር በምዕራፍ 12 መጠቀም ይችላሉ።
8 ‘ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ’ እንደመሆናችን መጠን አዎንታዊ አመለካከት ይዘን ምሥራቹን የምናቀርብበት በቂ ምክንያት አለን። (1 ቆሮ. 3:9) እንዲህ ያለውን አመለካከት ይዘን መቀጠላችን የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከት ያስገኝልናል።