ከወንድሞቻችሁ ጋር በደንብ ተዋወቁ
1 መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ወዳጅ ከወንድም አብልጦ እንደሚጠጋጋ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ እንደማይደበዝዝ እንዲሁም በችግር ጊዜ ደራሽ እንደሆነ ይገልጻል። (ምሳሌ 17:17፤ 18:24) አንዳችን ከሌላው ጋር በደንብ ለመተዋወቅና ለመዋደድ ጥረት የምናደርግ ከሆነ በጉባኤ ውስጥ እንደዚህ ያሉ ወዳጆችን ለማግኘት አንቸገርም።—ዮሐ. 13:35
2 ስብሰባ ከመጀመሩ በፊትና ስብሰባ ካለቀ በኋላ ያሉት ጊዜያት ከወንድሞቻችን ጋር ለመተዋወቅ የሚያስችሉ ጥሩ አጋጣሚዎች ናቸው። ሞቅ ያለና የሚያስደስት ወዳጃዊ ጭውውት ማድረግ እንድትችሉ ቀደም ብላችሁ ወደ ስብሰባ ለመምጣት ወይም ስብሰባ ካለቀ በኋላ ቆየት ብላችሁ ለመሄድ ለምን ጥረት አታደርጉም? ተሞክሮ ያካበቱ በእድሜ የገፉትንም ሆነ ወጣቶችን ወይም ዓይን አፋርነት የሚያጠቃቸውን ጨምሮ ከተለያዩ ወንድሞች ጋር ለመነጋገር ጥረት አድርጉ።
3 ጭውውቱን ራስህ ጀምር፦ ለወንድሞችህ የተለመደ ሰላምታ በመስጠት ብቻ አትወሰን። በመስክ አገልግሎት ያጋጠመህን አንድ ተሞክሮ፣ በቅርቡ ከወጣ መጽሔት ላይ ያነበብከው አንድ ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ወይም ስላለቀው ስብሰባ የሚገልጽ ሐሳብ በመሰንዘር ውይይት መጀመር ትችላለህ። ስለ ራሳቸው ተሞክሮና ስለተማሯቸው ነገሮች እንዲናገሩ አደፋፍረህ ጥሩ አዳማጭ በመሆን ስለ ወንድሞችህ ብዙ ነገር ልታውቅ ትችላለህ። አንድ ሰው ይሖዋን እንዴት እንዳወቀ መጠየቁ ብቻ ስለ እርሱ ብዙ ነገር እንድታውቁ ሊረዳችሁ ይችላል። አንዳንዶች በሕይወታቸው እምነት የሚያጠነክሩ ተሞክሮዎችን ያሳለፉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ብዙዎች ሊገምቱት ከሚችሉት በላይ በሆነ ችግር ውስጥ ይገኙ ይሆናል። ይህንን ነገር መገንዘባችን እንደ አንድ እውነተኛ ወዳጅ የሌሎች ችግር የሚገባንና በሚያስፈልጋቸው ነገር የምንደግፋቸው እንድንሆን ይረዳናል።
4 አንዳችሁ የሌላው ወዳጅ ሁኑ፦ አንዲት እህት ልጅዋ በሞት ከተለየቻት በኋላ ስለ ትንሣኤ ተስፋ የሚጠቅሱትን የመንግሥቱን መዝሙሮች መዘመር አስቸጋሪ ሆኖባት ነበር። እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “አንድ ቀን ከመተላለፊያው ባሻገር በነበረው መደዳ በእኔ አቅጣጫ ተቀምጣ የነበረች እህት ሳለቅስ አየችኝ። አጠገቤ መጥታ እቅፍ አድርጋኝ የቀሩትን የመዝሙሩን ስንኞች አብራኝ ዘመረች። ልቤ ለወንድሞችና ለእህቶች ባለኝ ፍቅር ተሞላ፤ እርዳታ የምናገኘው ሌላ የትም ሳይሆን በመንግሥት አዳራሽ በመገኘት መሆኑን ስለተገነዘብኩ ወደ ስብሰባዎቹ በመምጣታችን የደስታ ስሜት ተሰማኝ።” አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ወንድሞቻችንን በማጽናናትና በማንኛውም ጊዜ ማበረታቻ በመስጠት ወዳጆቻቸው መሆናችንን ማስመስከር ይኖርብናል።—ዕብ. 10:24, 25
5 ይህ አሮጌ ዓለም ይበልጥ የሚደቁስ እየሆነ በሄደ መጠን ከወንድሞቻችን ጋር በደንብ ለመተዋወቅ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። በዚህ መንገድ ልባዊ ማበረታቻ መለዋወጡ ለሁሉም በረከት የሚያስገኝ ይሆናል።—ሮሜ 1:11, 12