“የአምላክ የሕይወት መንገድ” ከተባለው የአውራጃ ስብሰባ ተጠቅመናል
1 ከጥቂት ወራት በፊት “የአምላክ የሕይወት መንገድ” በተሰኘው የ1998 የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እቅዶችን ስናወጣ ነበር። አሁን ግን በድርጅቱ ቲኦክራሲያዊ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ ትዝታ ጥሎ አልፏል። በእነዚያ አስደናቂ ስብሰባዎች ላይ ባገኘናቸው የተትረፈረፉ መንፈሳዊ ምግቦች ከፍተኛ ደስታ አግኝተናል።
2 የዚህ ዓመቱ የአውራጃ ስብሰባ ብሔራት አቀፍ በመሆኑ በእርግጥም ስሜት ቀስቃሽ ነበር። “በሚስዮናውያን መስክ ያለው የአገልግሎት እንቅስቃሴ” ከሚለው እንዲሁም በሦስቱም ዕለት ከቀረበውና ከዓለም ዙሪያ የተገኙ ሪፖርቶች ከቀረቡበት “በመከሩ ሥራ እየታየ ያለውን እድገት የሚገልጹ ሪፖርቶች” ከሚለው ክፍል አስደሳች ተሞክሮዎችን አዳምጠናል።
3 አዲስ የወጡ ግሩም ጽሑፎች፦ ዓርብ ዕለት የቀረበው የመጨረሻ ንግግር እውነትን የማያውቁ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ለሚያነሱት “ከሞት በኋላ ሕይወት አለ?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። ይህ ስሜት ቀስቃሽ ንግግር የተደመደመው ስንሞት ምን እንሆናለን? የሚል ርዕስ ያለው አዲስ ብሮሹር መውጣቱን በማብሰር ነበር። እስካሁን ሁላችንም ይህንን ብሮሹር አንብበነው ስለሚሆን ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ሰዎች እውነቱን እንዲገነዘቡ በመርዳትና የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ያጡትን በትንሣኤ ተስፋ አማካኝነት በማጽናናት በኩል ያለውን ዋጋማነት ተገንዝበን መሆን አለበት።
4 የቅዳሜ የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም የተጠናቀቀው “የፈጣሪ ባሕርያትና መንገዶቹ” በሚለው ንግግር ነበር። ይህ ንግግር በእርግጥ አንድ ፈጣሪ እንዳለ በማያሻማ መንገድ አረጋግጦልናል። ይህን ሐቅ ሌሎች እንዲገነዘቡት በምናደርገው ጥረት እኛን ለማገዝ ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? የሚል መጽሐፍ (በእንግሊዝኛ) ወጥቷል። መጽሐፉ እኛ ራሳችን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት እንዲሁም ስለ ባሕርያቱና ስለ መንገዶቹ ያለንን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ የሚረዳን ቢሆንም በተለይ ከፍተኛ ትምህርት ኖሯቸው በአምላክ መኖር የማያምኑ ሰዎችን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
5 በዚህ ስብሰባ ላይ ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተሰኘ አዲስ መጽሐፍም አግኝተናል። ይህ መጽሐፍ ደስተኛ ቤተሰብ ለመምራት የግድ አስፈላጊ የሆኑ አራት ነጥቦችን ጎላ አድርጎ ይገልጻል:- (1) ራስን መግዛት፣ (2) የራስነትን ሥልጣን መቀበል፣ (3) ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግና (4) ፍቅር። የቤተሰብ ደስታ በተሰኘው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈሩትን ምክሮች በሥራ ላይ የሚያውሉ ቤተሰቦች ሁሉ በቤታቸው ውስጥ አምላካዊ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋሉ። ሌላው ያገኘነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለው መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን እንዲገነዘቡና በአምላክ የሕይወት መንገድ መጓዝ እንዲጀምሩ የሚረዳ ነው። እነዚህን አዳዲስ መጻሕፍት ለማንበብና በቤተሰብ ደረጃ አንድ ላይ ሆናችሁ ለማጥናት ጊዜ መድቡ። በመስክ አገልግሎትም ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም ትችሉ ዘንድ ከሁለቱም መጻሕፍት ይዘት ጋር በሚገባ ተዋወቁ።
6 ልብ የሚነካ የአቋም መግለጫ፦ የአውራጃ ስብሰባው የመደምደሚያ ንግግር ሁላችንም ‘በይሖዋ መንገዶች መጓዛችንን መቀጠላችን’ ምን ያክል አስፈላጊ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገልጿል። በአቋም መግለጫው ውስጥ በግለሰብ ደረጃ የአምላክ የሕይወት መንገድ የላቀ መሆኑን ዘወትር በመደገፍም ሆነ በማራመድ ረገድ ያለንን ቁርጥ አቋም መግለጻችን በእርግጥም የሚገባ ነበር! (ኢሳ. 30:21) ከዚህ ውሳኔ ጋር ተስማምተን መኖር ቁርጥ አቋማችን መሆን አለበት። “የአምላክ የሕይወት መንገድ” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ በመገኘታችን በመንፈሳዊ ምንኛ ተነቃቅተናል!