ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉ የበላይ ተመልካቾች—የአገልግሎት የበላይ ተመልካች
1 የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ በጉባኤው ክልል ውስጥ ለሚከናወነው የወንጌላዊነት ሥራ መስፋፋት ጋር የሚዛመዱ ጉዳዮችን በትኩረት ይከታተላል። በዚህም መንገድ ምሥራቹን እንድንሰብክ የተጣለብንን ኃላፊነት ለመፈጸም እንድንችል በመርዳት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ቀናተኛ ወንጌላዊ እንደመሆኑ መጠን ከመስክ አገልግሎት ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ነገሮች ቀዳሚ ሆኖ ያደራጃል። ጥሩ ችሎታ ያለው አስተማሪ እንደመሆኑም አስፋፊዎች በግለሰብ ደረጃ በአገልግሎት ያላቸውን ውጤታማነት ከፍ እንዲያደርጉ እገዛ ያደርጋል።—ኤፌ. 4:11, 12
2 ይህ ሽማግሌ ጽሑፍ፣ መጽሔትና የአገልግሎት ክልል እንዲሰጡ የተመደቡትን የጉባኤ አገልጋዮች ሥራ በቀጥታ ይቆጣጠራል። በየወሩ በቂ መጠን ያላቸው ጽሑፎች፣ መጽሔቶችና የአገልግሎት ቅጾች መኖራቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት። በዓመት አንድ ጊዜ የአገልግሎት ክልል መዝገቡን በማገላበጥ እንዳናንኳኳቸው የተነገሩንን ቤቶች አድራሻ በሙሉ ሰብስቦ ብቃት ያላቸው ወንድሞች እነዚህን ቤቶች እንዲያንኳኩ ይመድባል።
3 የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ በንግድ ቦታዎች፣ በመንገድ ላይና በስልክ የሚሰጠውን ምሥክርነት ጨምሮ የተለያዩትን የስብከት ዘርፎች እንቅስቃሴ የመከታተል ኃላፊነት አለበት። የበዓል ቀናትን ጨምሮ ሳምንቱን በሙሉ የመስክ አገልግሎት ስብሰባዎች የሚደረጉበት አመቺ ዝግጅት ለማድረግ ንቁ ነው። ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንቅስቃሴውም ልባዊ ትኩረት ይሰጣል። በአገልግሎታቸው አዘውታሪ ላልሆኑት ወይም አገልግሎት ላቆሙት መንፈሳዊ እርዳታ የሚሰጥበትን መንገድ ያፈላልጋል። አቅኚዎች ስለሚያከናውኑት ሥራ ከልብ የሚያስብ ሲሆን አቅኚዎች ሌሎችን ይረዳሉ የተባለውንም መርሐ ግብር በበላይነት ይከታተላል።
4 የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ አባል እንደመሆኑ መጠን በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖች ላይ ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ሐሳብ ያቀርባል። የእናንተን የመጽሐፍ ጥናት ቡድን በሚጎበኝበት ጊዜ በዚያ ለመገኘትና አብራችሁት በአገልግሎት ለመካፈል ጥረት አድርጉ።
5 ሁሉም የጉባኤው አባላት የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ የሚሰጠውን መመሪያ በፈቃደኝነት መቀበል ይኖርባቸዋል። ይህም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ያለንን ውጤታማነት ከፍ የሚያደርገው ከመሆኑም ሌላ በአገልግሎታችን ትልቅ ደስታ እንድናገኝ ያስችለናል።