ሁሉም ‘ቃሉን ከልብ መቀበል’ አለባቸው!
1 በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እያጠኑ ነው። እነዚህ ሰዎች ለዘላለም ሕይወት ብቁ ሆነው እንዲገኙ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ንስሐ ገብተው እንደተጠመቁት 3,000 ሰዎች ‘ቃሉን ከልብ መቀበል’ አለባቸው። (ሥራ 2:41) ታዲያ ይህ ዛሬ በእኛ ላይ ምን ኃላፊነት ይጥልብናል?
2 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ለይሖዋ የማደርን ባሕርይ እንዲያዳብሩ መርዳት ይኖርብናል። (1 ጢሞ. 4:7-10 NW) ይህንንም ለማድረግ ይቻል ዘንድ የሰኔ 1996 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ አንቀጽ 20 ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰጥቶ ነበር:- “በጥናቱ ወቅት ለይሖዋ ባሕርያት ያለውን አድናቆት ለመገንባት የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች ለማግኘት ሞክር። ስለ አምላክ የሚሰማህን የራስህን ውስጣዊ ስሜት ንገረው። ተማሪው ከይሖዋ ጋር ሞቅ ያለ የግል ዝምድና ስለ መመሥረት እንዲያስብ እርዳው።”
3 የሚገጥመን ፈታኝ ሁኔታ፦ ብዙ ሰዎች የሐሰት ሃይማኖት ካሳደረባቸው ተጽዕኖ የተነሣ በአኗኗራቸው እምብዛም ለውጥ ማድረግ ሳያስፈልጋቸው በአነስተኛ ጊዜና ጥረት ብቻ በሚያቀርቡት አምልኮ ይረካሉ። (2 ጢሞ. 3:5 NW) እያንዳንዳችንን የሚገጥመን ፈታኝ ሁኔታ እውነተኛ አምልኮ የአምላክን ቃል መስማት ማለት ብቻ እንዳልሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን እንዲገነዘቡ መርዳት ነው። የተማሩትን ነገር በሕይወታቸው ውስጥ ሊሠሩበት ይገባል። (ያዕ. 1:22-25) በግል ሕይወታቸው ውስጥ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው አድራጎት የሚፈጽሙ ከሆነ ከዚያ ‘የመመለስና’ እርሱን ለማስደሰት ትክክል የሆነውን ነገር የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው መገንዘብ ይኖርባቸዋል። (ሥራ 3:19) የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ‘መጋደልና’ ለእውነት የጸና አቋም መያዝ ይኖርባቸዋል።—ሉቃስ 13:24, 25
4 ስለተለያዩ ሥነ ምግባር ዘርፎች በምትወያዩበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችሁ እነዚህን ነገሮች እንዴት እንደሚመለከታቸው እንዲሁም በአኗኗሩ ላይ ለውጥ ማድረግ እንዳለበት ከተገነዘበ ምን ማድረግ እንደሚኖርበት ጠይቁት። ትኩረቱን እውነትን እንዲያውቅ እየረዳው ባለው ድርጅት ላይ እንዲያደርግና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ እንዲገኝ እርዱት።—ዕብ. 10:25
5 ስናስተምር የተማሪያችንን ልብ የመንካት ግብ ይኑረን። አዲሶች የአምላክን ቃል ከልባቸው ተቀብለው እንዲጠመቁ መርዳት ስንችል ደስታ እናገኛለን።—1 ተሰ. 2:13