የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህን ልብ ለመንካት ጣር
1 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ የሚማረውን ነገር እንዲሠራበት ትፈልጋለህን? በሚያገኘው እውቀት እንዲጠቀም ከተፈለገ የተማረውን የሚሠራበት መሆን አለበት። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ የተማረውን እንዲሠራበት ከፈለግህ ልቡን መንካት መቻል አለብህ። በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ የሰጠው የሚያነቃቃ ንግግር 3,000 የሚያህሉ ሰዎችን ‘ልብ ነክቷል።’ ‘ቃሉን በሙሉ ልብ የተቀበሉት’ እነዚህ ሰዎች በዚያው ቀን ተጠምቀዋል። (ሥራ 2:37, 41) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህን ልብ ለመንካት የምትችለው እንዴት ነው?
2 በደንብ ተዘጋጅ፦ ምክንያቱን እያስረዳህ ከተማሪው ጋር ለመወያየት ጊዜ እስክታጣ ድረስ ብዙ ትምህርት ለመሸፈን አትሞክር። የምታጎላቸውን ነጥቦቸ አስቀድመህ ወስን። ነጥቦቹ እንደገቡህና ጥቅሶቹን በሚገባ ለማብራራት እንደምትችል እርግጥኛ ሁን። በአስተዳደጉና ከዚህ በፊት በነበረው አስተሳሳብ ምክንያት በተማሪው አእምሮ ውስጥ ምን ጥያቄዎች ሊነሡ እንደሚችሉ አስቀድመህ አስብ። ከተማሪህ ጋር በሚገባ የምትተዋወቅ ከሆነ ይህ እውቀትህ ለእርሱ የሚስማማ ማብራሪያ ለማዘጋጀት ያስችልሃል።
3 የኢየሱስን የማስተማር መንገድ ተከተል፦ ኢየሱስ ከባድ ነጥቦችን ቀለል አድርጎ ለመግለጽና ተማሪዎቹ ትርጉሙና ስሜቱ እንዲገባቸው ሲል በምሳሌዎች ይጠቀም ነበር። (ሉቃስ 10:29-37) አንተም በተመሳሳይ የምትጠቀምባቸውን ምሳሌዎች ቀላልና ከተለመደው የኑሮ ገጽታዎች የተወሰዱ በማድረግ እንዲሁም ለተማሪው ሁኔታዎች እንዴት እንደሚሠሩ በማሳየት ግሩም ትምህርቶችን በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ ልብ ውስጥ ለመቅረጽ ትችላለህ።
4 ብዙ ጊዜ ኢየሱስ ያደርግ እንደነበረው ጥያቄዎችን መጠየቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ልብ ለመንካት በጣም ይረዳል። (ሉቃስ 10:36) ይሁን እንጂ ተማሪው መልሱን ከመጽሐፉ አንብቦ ቢመልስ በዚህ አትርካ። በፊት ወዳላሰበው መደምደሚያ እንዲደርስ የአስተሳሰብ አቅጣጫውን ዞር ለማድረግ በመሪ ጥያቄዎች ተጠቀም። በተጨማሪም እንዲህ ማድረግህ ተማሪው የማሰብ ችሎታውን እንዲያዳብር ይረዳዋል። በትምህርቱ ላይ ተማሪው በግሉ ያለውን እምነት ለማወቅ የአመለካከት ጥያቄዎችን ጠይቅ። ከዚያም በየትኛው አቅጣጫ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ለማወቅ ትችላለህ። ከዚያም በዚያ በኩል ለመርዳት ትችል ይሆናል።
5 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እድገት የማያደርግ ከሆነ ምክንያቶቹን ለማወቅ መጠያየቅ አለብህ። ይህም ከመደበኛው የጥናታችሁ ጊዜ በተጨማሪ በሌላ ጊዜ ሄዶ መጠየቅን ሊጨምር ይችላል። ርምጃ ለመውሰድ የሚያመነታው ለምንድን ነው? ያልገቡት አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ነጥቦች ይኖሩ ይሆን? በአኗኗሩ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ለማድረግ አይፈልግምን? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ‘በሁለት ሐሳብ ለማነከስ እየሞከረ’ ከሆነ እንዲህ ማድረጉ የሚያስከትለውን አደጋ እንዲገነዘብ እርዳው።—1 ነገ. 18:21
6 ሐዋርያው ጳውሎስ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ማስተማር ሕይወት አድን ሥራ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። ሁሉም ክርስቲያኖች ‘ዘወትር ለትምህርታቸው የሚጠነቀቁ’ እንዲሆኑ የመከረውም ለዚህ ነው። (1 ጢሞ. 4:16) መጽሐፍ ቅዱስን የምታስጠናቸው ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስና በዓለም ስላሉት ሁኔታዎች አጠቃላይ የሆኑ እውነታዎችን ከማወቅ የበለጠ ነገር እንዲያገኙ ያስፈልጋል። ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት መቻል አለባቸው። በተጨማሪም ከይሖዋና ከኢየሱስ ጋር ሞቅ ያለ የግል ዝምድና እንዲያዳብሩ እርዳታ እንዲያገኙ ያስፈልጋል። እምነታቸውን በሥራ ለማሳየት ሊገፋፉ የሚችሉት እንዲህ ያለውን እርዳታ ሲያገኙ ብቻ ነው። (ያዕ. 2:17, 21, 22) የተማሪው ልብ ከተነካ ይሖዋን በሚያስከብረውና የራሱን ሕይወት ለማዳን በሚያስችለው መንገድ ለመመላለስ ይገፋፋል። — ምሳሌ 2:20-22