የተለየን መሆናችንን ማየት ይችላሉ
1 ባለፈው ዓመት ከ300,000 የሚበልጡ አዳዲስ ሰዎች ተጠምቀው ከእኛ ጋር ተቀላቅለዋል። እነዚህ ሰዎች የአምላክ ድርጅት ክፍል ለመሆን እንዲመኙ ያነሳሳቸው በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተመለከቱት ነገር ምንድን ነው? ከሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ የተለየን ሆነን የምንታየው ለምንድን ነው? አንዳንድ ግልጽ መልሶች ቀጥሎ ቀርበዋል:-
—በግል አመለካከታችን ከመመራት ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን በጥብቅ እንከተላለን:- ኢየሱስ ክርስቶስ እንድናደርግ በነገረን መሠረት ይሖዋ አምላክን “በመንፈስና በእውነት” እናመልካለን። ይህ ደግሞ ሃይማኖታዊ ውሸቶችን ማስወገድና በጽሑፍ ከሰፈረው የአምላክ ቃል ጋር መስማማት ማለት ነው።—ዮሐ. 4:23, 24፤ 2 ጢሞ. 3:15–17
—ሰዎች ወደ እኛ እንዲመጡ ከመጠበቅ ይልቅ እነሱ ወደሚገኙበት እንሄዳለን:- ክርስቶስ የሰጠንን የመስበክና የማስተማር ተልዕኮ ተቀብለናል፤ እንዲሁም እርሱ የተወልንን ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች የመፈለግ አርአያ እንከተላለን። እነዚህን ሰዎች በቤታቸው፣ በመንገድ ላይ፣ ወይም በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ለማግኘት እንጥራለን።—ማቴ. 9:35፤ 10:11፤ 28:19, 20፤ ሥራ 10:42
—ለሁሉም ሰው ያለ ክፍያ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንሰጣለን:- በየዓመቱ ከአንድ ቢልዮን የሚበልጥ ሰዓት በማሳለፍ ችሎታችንንና ጉልበታችንን አምላክ ለሰጠን አገልግሎት በነፃ እናውላለን። ምንም ሳናዳላ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እናስጠናለን።—ማቴ. 10:8፤ ሥራ 10:34, 35፤ ራእይ 22:17
—ሰዎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት የሚያስችል ጥሩ ሥልጠና አግኝተናል:- በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎችና በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ በሚቀርቡልን ትምህርቶች አማካኝነት ለሌሎች መንፈሳዊ እውቀት ለመስጠት የሚያስችለንን በዋጋ ሊተመን የማይችል ቀጣይ ቲኦክራሲያዊ ሥልጠና እናገኛለን።—ኢሳ. 54:13፤ 2 ጢሞ. 2:15፤ 1 ጴጥ. 3:15
—እውነትን በዕለታዊ ሕይወታችን ተግባራዊ በማድረግ በቁም ነገር እንይዛለን:- ለአምላክ ካለን ፍቅር የተነሳ ለውጥ በማድረግ አኗኗራችንን ከእርሱ ፈቃድ ጋር እናስማማለን። የክርስቶስ ዓይነቱ አዲሱ ሰውነት ሌሎች ወደ እውነት እንዲሳቡ ያደርጋቸዋል።—ቆላ. 3:9, 10፤ ያዕ. 1:22, 25፤ 1 ዮሐ. 5:3
—ከሌሎች ጋር በሰላም ለመኖርና ለመሥራት እንጥራለን:- አምላካዊ ባሕርያት ማዳበራችን ድርጊታችንንና አነጋገራችንን እንድንቆጣጠር ይረዳናል። ከሁሉም ሰዎች ጋር ‘ሰላምን እንሻለን፣ እንከተላለንም።’—1 ጴጥ. 3:10, 11፤ ኤፌ. 4:1–3
2 በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የሚመለከቱት የክርስቲያናዊ አኗኗር አርአያ ብዙዎች እውነትን እንዲቀበሉ ያነሳሳቸዋል። የእኛም አርአያነት በሚያውቁንና በሚመለከቱን ሰዎች ዘንድ ተመሳሳይ ውጤት እንዲኖረው እንመኛለን።